Site icon ETHIO12.COM

ከፓለቲካ ጭምብል ወደ ሃገራዊ መነፅር

በላይ ባይሳ

ጋሽ አሜሪካ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያን እንደ ሸክላ በእጇ የሰራቻት እስኪመስል የሃገርን ሉዓላዊነት በሰብአዊ መብት ጥሰት ሰበብ እና በእርዳታ ስም ድብቅ የተንኮል እጇን በማርዘም ስትገፋ፤

ስለ ሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የዓለም-ዓቀፉ ማህበረሰብ በውገና ድርሰት እና በተሳሳተ ሱዛናውያን መረጃ እና የውሸት ትርክት የተዛባ ግንዛቤ መያዝ (ከዚህ ረገድ የፐብሊሲቲ ስራውን ከመስራት አንፃር የሃገሪቱ ሚድያዎች እና በየሃገሩ ያሉ አምባሳደሮች ብልጫ እንደተወሰደባቸውና ክፍተታቸው ሰፊ መሆኑ ልብ ይለዋል)

የፓለቲካ ርዕዮትንና የሃገርን ጥቅም በደንብ ያልለዩት ዱዝ “አዋቂዎቻችን” ደግሞ በደስታ ፌሽታ ሲፍከነከኑና ከበሮ ሲደልቁ፤

የግብፅ ድንፋታን እና የጎረቤት ሱዳንን ጭራ መቁላት እንዲሁም የጦርነት ትንኮሳ ስትመለከት፤

ለያዥ ለገናዥ አስቸግራ የነበረችው ትህነግ ቅሪት አካሏ ዛሬም አፈር-ልሶ ለመነሳት ሲውተረተር፣ ሲደነፍና የግጭት መርዝ ርጭት ሲያደርግ ስታይ፤

ሃገራችን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ 6ኛውን ምርጫ ለማድረግ ደፋ ቀና ስትል፤

የህዳሴውን ግድብ ለመሙላት ብሎም ለመጨረስ የመጨረሻው ምዕራፍ መቃረቡን ስታይ፤

ሃገሪቱ በግሽበትና በኑሮ ውድነት ተወጥራ የዜጎች ህይወት ሲፈተን፤

ሃገርን በመምራት ሃገሪቱን በሁለንተናዊ የእድገት ጎዳና ወደፊት ለመውሰድ በሚደረገው የፓለቲካ አማራጭ ውድድር የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከአቅም በታች ወርደው ጉንጭ አልፋ እና አንዳንዴም እንቶ-ፈንቶ የሆነ ውሃ የማያነሳ የወፈፌ እና የንቅል ሙሾ አውራጅ ዥልጥ የዕድርተኞች ፓርቲ ስብስብ (በጣት የሚቆጠሩ ጠንካራ የመከራከርያ ነጥብ እና በሃሳብ ልእልና የሚሟገቱትን አይመለከትም) ዲስኩር ስትሰማ፤

በተለያዩ ቦታዎች በዜጎች ላይ በተለይም በትግራይ ክልል የሰብአዊ እርዳታ ፈተና መሆንና የዜጎች ደህንነት አጣብቂኝ ውስጥ መውደቅ

አለማቀፍ የዲኘሎማስ ስራው እጅጉን ፈተና የበዛበት ትንቅንቅ ሲሆን፤

አለማቀፍ ሚድያዎች ሲኤንኤ, ቢቢሲ እና አልጀዚራ በተናበበ መልኩ የፈጣሪዎቻቸውን ህልም ለማሳካት የውገና ዘገባዎችን እና የጦርነት ድግስና የሰቆቃ ድምፅ ኦኬስትሬት ሲያደርጉ ስታይ፤

የምዕራባውያኑን ጥቅም እስካልነካ ድረስ በየትኛውም የሃገራችን ክፍል ተፈፅሞ የነበረና የሚፈፀም በደል አዓለም-ዓቀፍ ሚድያዎች በተለይም ሲኤንኤ, ቢቢሲ እና አልጀዚራ … ሌሎችም ብዙም እንደማያስጨንቃቸው በተደጋጋሚ ስታይ፤

ከጊዜ ወደጊዜ የሃገሪቱ የፓለቲካ አካሄድ ውስብስብነት እየጨመረ መሄዱን፤

የማህበራዊ ሚድያው በአብዛኛው በሚባል ደረጃ መረን የለቀቀ የጦርነት ነጋሪት መጎሰሚያ እና የውሸት አውድማ መሆኑ … ወዘተ ስታይኢትዮጵያችን ምን አይነት ከባድ ሁለንተናዊ ፈተናዎች ምዕራፍ ላይ መሆኗን ታጤናለህ። ስለዚህ ዜጎች የፓለቲካ ጭምብላቸውን አውልቀው ነገሮችን ሁሉ በሃገራዊ ጥቅም መነፅር መመልከት ግድ የሚልበት ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን መረዳት ተገቢ ይሆናል።ሊነጋ ሲል ይጨልማል የሚባለው ብሂል ይሁን? ይነጋል!

በላይ ባይሳ

ግንቦት 20/2013 ዓ.ም


Exit mobile version