ETHIO12.COM

‘‘በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ዜጎች ምግብ የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አስተዳደሩ ግዴታውን ይወጣል”

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩ ሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ምግብ የማግኘት የዜግነት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው አስተዳደሩ ግዴታውን እንደሚወጣ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ተስፋ ብርሃን አራተኛው የምገባ ማዕከል ሥራ ጀመረ።

በልደታ ክፍለ ከተማ የተገነባው አራተኛው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል ትናንት በይፋ አገልግሎት መስጠት በጀመረበት መርሐ ግብር ላይ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች እንደገለጹት፤ ነዋሪዎች ምግብ ማግኘት የዜግነት መብታቸው ሲሆን፤ መንግሥትም ምግብ የማቅረብ ግዴታ ተጥሎበታል።

እነዚህ የምገባ ማእከላት እውን እንዲሆኑ በጎ አሳቢ ግለሰቦችና ተቋማት ትብብር ማድረጋቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ አዳነች፤ ይህም በከተማው የሚስተዋለውን የማህበራዊ ችግሮች በአብሮነት በመተባበር ማቃለል እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል። ችግሮቻችንን የምናቃልለው ስንተባበርና ስንተጋገዝ ነው ብለዋል።

ማዕከሉ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር በቀን ከሁለት ሺ በላይ ተመጋቢዎችን ለመመገብ የሚያስችል አቅም እንዳለው ጠቁመው ፣ በማዕከሉ ተጠቃሚ የሚሆኑትም አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት ያለባቸው፣ በእጅጉ የኢኮኖሚ ውስንነት ያለባቸውና በገቢ እራሳቸውን ያልቻሉ ነዋሪዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ስላሴ ዋለልኝ፤ በልደታ ክፍለ ከተማ በተገነባው የምገባ ማዕከል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ህይወትን በመግፋት ላይ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍና በምግብ እንዳይቸገሩ ለማድረግ የተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በክፍለ ከተሞች ብዛት ያላቸው የምገባ ማዕከሎች መገንባታቸው በየአካባቢው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚረዳ አመልክተው፣ በከተማው ውስጥ ከአካባቢ ወደ አካባቢ የሚደረገውን ፍልሰት ለመግታት እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።

የማዕከሉ ተጠቃሚዎች ከምገባው በተጨማሪ የክህሎት ማሣደጊያ ፣ የሥራ ፈጠራ ስልጠና፣ የስነ ልቦና ምክር፣ እገዛና ህክምና እንደሚያገኙም ጠቁመዋል። ተጠቃሚ ዜጎች እነዚህን እድሎች ተጠቅመው የራሣቸውንና የሀገራቸውን እድገት ለማፋጠን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

በማዕከሉ የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ተካ አስናቀ፣ ዜጋን ማሰብ ለሀገር ማሰብ ነው። አሁን ያገኘነው አገልግሎት አብሮ የመኖርን ትርጉም። መርሐ ግብሩ ምግብ ለማግኘት ጎዳና ወጥቶ የሀገር ገፅታን የሚያበላሽና በልመና የሚተዳደሩ አዛውንቶች፣ ህፃናትና ወጣቶችን ይታደጋል ብለዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የምንገኝ ዜጎች የእለት ጉርስ ከማሰብ ባለፈ ልማትና እድገትን፣ አንድነትንና የአገር ሰላምን እንድናስብ አድርጎናል። ተስፋ ሰንቀን የተሻለ ዜጋ ለመሆን እንድንጥር ባለሃብቶችና መንግስት ተባብረው ባደረጉት ተግባር ደስተኞች እንደሆኑ አስታውቀዋል።

ሙሳ ሙሀመድ


Exit mobile version