Site icon ETHIO12.COM

24 ሠዓታት በወታደር ህይወትክፍል 5 – ወታደር ፣ በፍቅር የደመቀ – በህብር የረቀቀ

ከ1991 ዓ.ም ውጊያ በኋላ ለ1992 ዓ.ም የመጨረሻ ውጊያ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ ነበር። ሁሉም ሥፍራዎች ላይ ከውጊያ ያልተናነሱ ልምምዶች ተደርገዋል። የተራራ ላይ ውጊያ፣ የበረሃ ውጊያ፣ የሌሊትና የቀን በማለት ደም እንዲታቀብ ላብ ያለመጠን ፈስሷል።

በወቅቱ በታችኛው እርከን የነበረ ሠራዊት እና አመራር ( ይህንን ታሪክ የሚያወጋንን ጨምሮ ) በሚሰለጥንበት ግንባር ውጊያ እንደሚገባ ያስብ ነበር። ከተደጋጋሚ ክስተቶች በኋላ ይሄ እምነት ሙሉ በሙሉ ትክክል የሚሆን እንዳልሆነ ተረድቷል።አደረጃጃቱም ቋሚ አይደለም። የነበሩበት ኮር ፣ ክፍለ ጦርና ብርጌድ ተቀይሮ በወራት ውስጥ የሌላ ክፍል አባል ሊሆን ይችላል። ይሄ ደግሞ በውትድርና የአደረጃጀት ባህሪይ ነው። ምክንያቱም አደረጃጀት ታክቲክ እንጂ እስትራቴጂ አይደለምና።በውጊያ ጊዜ ቋሚ ካምኘም አይታሰብም።

አንድ የሚደነቅ ባህል ግን አለ። ሠራዊቱ ለቀናትም ሆነ ለሣምንታት የሚያርፍበት ወታደራዊ ቦታ ላይ መፀዳጃዎችን ይሠራል። የቋሚና ተንቀሳቃሽ ጥበቃ ሥፍራ ይለያል። የደረቅና እርጥብ ቆሻሻ መጣያ ጉድጓድ ያዘጋጃል። ተነስ ሲባል የቆፈረውን መድፈን እንጂ ለምን ለዚች አጭር ጊዜ ብሎ አይጠይቅም። ወታደራዊ ባህሉ አይፈቅድም። አድርግና አታድርግ ታምኖበት በየትኛውም ዓለም መደበኛ ሠራዊት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ባለታሪኩ የነበረበት ክፍል እንጉያ የተባለ አከባቢ የነበረውን ስልጠና ጨርሶ ለአዲስ አደረጃጀት ከአድዋ ተራሮች ግርጌ የምትገኝ ድብድቦ የተባለ ቦታ ሠፍሯል። በአዲስ አደረጃጀት አዲስ ስያሜም ይዟል።ከላይ እንደተጠቀሰው ጊዜያዊ መኖሪያ በየሻለቃ ፣ ሻምበልና የመቶው ይዟል።

የእርጥብና ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ መፀዳጀዎችና መመገቢያ የገላና እጅ መታጠቢያዎች እንዲሁም የእርድ ሥፍራዎች አዘጋጅቷል። እነዚህ ነገሮች ቀላል ጉዳዮች አይደሉም።ንፅህናቸውን የሚከታተሉ የህክምና ሙያተኞች በየደረጃው አሉ። በየዕለቱ ሲፀዱ ጉድለት የተገኘባቸው በየዕለቱ ደረጃ ይሰጣቸዋል።

ሠራዊቱ ደግሞ ኋላ መባልን ፈፅሞ አይወድም። ምክንያቱም በዚህ ምክንያት በዋናው ግዳጅ ከኋላ የሚሰለፍ ይመስለዋል።በዚህ ወቅት የፋሲካ በዓል ደርሶ ነበር። ሠራዊቱ ሐይማኖታዊም ሆነ ህዝባዊ በዓላትን ፋታ ሲያገኝ የማክበር ልማድ አለው። በርግጥ ሠራዊቱ ፋሲካም ሆነ ረመዳን ፣ አረፋም ሆነ ጥምቀትን የሚያከብረው በአንድ ዓይነት ስሜት ነው። ክፍፍል የሚባል ነገር የለም፡፡

በሠራዊቱ ውስጥ በዓላት በዋነኝነት የሚከበሩት የሠራዊቱን አንድነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ፤ ጓዳዊ ፍቅርና ቤተሰባዊነቱን የሚያጠናክሩ እሴቶችን ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ የተጠናና የታቀደ ነው።ወታደር በምንም ተዓምር ቤተሰቡን እያሰበ በበዓላት ወቅት አይቆዝምም። የሐይማኖትም ሆነ ብሔራዊ በዓላትን ሲያከብር የትም የማይገኝ በፍቅር የደመቀ በህብር የረቀቀ ብዝሃነት ውስጡ አለ። ይሄ ብቻ አይደለም።

በበዓላት ወቅት የምግብና መስተንግዶ፣ የጥበቃ፣ የስነፅሑፍ ወዘተ ኮሚቴዎች አሉ። ለምግብ ዝግጅት የሴት ጓዶች መኖርና አለመኖር የሚያሳስብ አይደለም። ወንዶች ባለው ነገር ተጠቅመው የሚያዘጋጁት በሼፎች ስብስብ የተዘጋጀ ይመስል ነበር።የሚቀርቡ የብሔሮች ብሔረሰቦች ዘፈንና ጭፈራዎች ድራማና ግጥሞች በሳቅ የሚያንፈራፍሩ ቀልዶችና ገጠመኞች በጡረታ አሊያም በሌላ ምክንያት ከሠራዊቱ የወጣን ሠራዊት ዕድሜ ዘመኑን የጦር ክፍሉን እንዲናፍቅ ያደርጉታል።

በበዓላትም ሆነ በተፈለገው ጊዜ ሠራዊቱን የሚያንፁ የክለብ ዝግጅት የሚያቀርቡ የመቶዎች ስያሜ አላቸው። አንዱ ከራስ በፊት ለሀገርና ለህዝብ ፣ ሌላው በማንኛውም ግዳጅ የላቀ ውጤት ፣ ምንጊዜም ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እና የተሟላ ስብዕና ይሰኛሉ።ስያሜዎቹ በዘፈቀደ የሚሰጡ ሳይሆን የሠራዊቱ ቁልፍ እሴቶች ናቸው። ተዘፍኖ ፣ ተመድርኮ ፣ ተገጥሞና ተናቦ ሲያበቃ የሚያሰርፁት የሚወክላቸውን እሴት ነው።

እነዚህ እሴቶችን ተጠቅሞ ሠራዊቱ የሠራቸው የሥርፀት ሥራዎች ዘረኝነትን የመጠየፍ ፣ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት የመመልከትና የማገለገል ጀግናና በአቋሙ የፀና ታማኝ የሀገር ብሔራዊ ዘብ መፍጠር ስለመቻሉ ተራኪው ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለውም።ለመሆኑ በዚህ የበዓል ዋዜማ ምን እውነት ተከሰተ ? ተራኪያችን ነገ በዚሁ ሰዓት ያስነብበናል ፡፡

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻፎቶግራፍ ዳዊት እንዳለ – መከለከያ ፌስ ቡክ


Exit mobile version