ETHIO12.COM

በእነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ አስር አለቃ መሳፍንት ጥፋተኛ ተባለ

ጄነራል ሰዓረ መኮንን

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ሰዓረ መኮንን እና ጓደኛቸውን ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን በመግደል ወንጀል ተከሶ የነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ጥፋተኛ መባሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገልጸ።

ውሳኔውን አርብ ግንቦት 27/2013 ዓ.ም የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሦስትኛ የጸረ ሽብርና የሕገመንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ በጀነራል ሰዓረ መኮንን መኖሪያ ቤት ውስጥ ግድያውን በመፈጸም የተከሰሰው አስር አለቃ መሳፍንት ጉዳይን የተመለከተው ችሎት ተከሳሹ የሰፊ የወንጀል ድርጊት አካል ሆኖ ወንጀሉን መፈጸሙን አመልክቷል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መረጃ መሰረት የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈበት ተከሳሹ አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ በአማራ ክልል የቀድሞ የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ በነበሩት በብርጋዲየር ጀነራል አሳምነው ጽጌ በተመራ ሰፊ ከባድ የወንጀል ድርጊቶች ሴራ ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር አመልክቷል።

በዚህም ተከሳሹ በዚሁ ሴራ ውስጥ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ሰዓረ መኮንን እንዲገድል እንዲሁም ሌላ ግለሰብ ደግሞ ምክትል ኤታማዦር ሹም የነበሩትን ጀነራል ብርሃኑ ጁላን እንዲገድል ተልዕኮ ሰጥቷቸው እንደነበር ተገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለውም ግንቦት 15/2011 ዓ.ም ምሽት ሦስት ሰዓት ላይ አስር አለቃ መሳፍንት ባሕር ዳር ከተማ የተፈፀመውን ጥቃት ሲሰማ “ተኩሶ ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን በመግደል ለማምለጥ ሲሞክር ተከቦ በቁጥጥር ስር ውሎ” ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱን ገልጿል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ሦስትኛ የጸረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በክሱ ላይ የቀረበውን የግራ ቀኝ ክርክርና ማስረጃ ከመዘነ በኋላ ነበር ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት የቅጣት አስተያየት ለመስማት ለሰኔ 11/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የተገደሉት ኤታማዦር ሹሙ፤ ለረጅም ዓመታት በኃላፊነቱ ላይ የቆዩትን ጄነራል ሳሞራ የኑስን ተክተው የአገሪቱ ሠራዊት አዛዥ ከሆኑ ብዙም አልቆዩም ነበር።

በጥቃቱ ወቅት በአጋጣሚ በጄነራሉ ቤት የተገኙት ጓደኛቸውና የቀድሞ የሠራዊቱ አባል ጀነራል ገዛኢ አበራም በተፈጸመባቸው ጥቃት ተገድለዋል።

ዐቃቤ ሕግ የዚሁ ሴራ አካል ነው ባለው ድርጊት በዚያው ዕለት ምሽት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ በባሕር ዳር የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትን ዶ/ር አምባቸው መኮንንና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮቻቸው ላይ ግድያ መፈጸሙ ይታወሳል። BBC amaharic


Exit mobile version