Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ክልል ረሃብ አለ? በረሃብ የሞተስ?

” … በረሃብ ሞቱ ተብሎ የተዘገበው ፍጹም ሃሰት ነው። የተጠቀስው ቦታ ድረስ ታዛቢዎች ሄደው አረጋግጠዋል። ዘጠና ከመቶ በትግራይ እርዳታ የሚሰጡት የውጭ ድርጅቶች ሆነው ሳለ እንዴት ለፖለቲካ መጠቀሚያ አናደርገዋለን? በዓለም መስፈት መሰረት ሶስቱ መለኪያዎች ሳይሙዋሉ ረሃብ አለ ማለት ይቻላል? የኢትዮጵያ ምላሽ ኣልባ ጥያቄ ነው። መግለጫ ብታዘጋጅ፣ ወስዳ ብታሳይ፣ ብታስተባብል ሚዲያዎች የማይሰሙዋት ኢትዮጵያ ምን ታድርግ? ቢቢሲ ይህን ዘግቡዋል

በትግራይ ክልል ረሃብ እንደሌለ የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ተናገሩ።

ረቡዕ ዕለት በትግራይ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ከጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ጋር ለጋዜጠኞች በተሰጠ ማብራሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር የሰብዓዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት በቅርቡ በትግራይ ክልል ያሉ ነዋሪዎች በረሃብ ቋፍ ላይ ናቸው የሚል መግለጫ ያወጣ ሲሆን የከፋው የ1977ቱ ረሃብ ሊደገም እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በትግራይ ክልል በረሃብ ሰዎች እየሞቱ ነው የሚለውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርትን በመጥቀስ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ምትኩ ምላሽ ሰጥተዋል።

በአንዳንድ ሪፖርቶች በኮረም ኦፍላ ወረዳ በረሃብ ሞተዋል ተብሎ የወጣ ሪፖርት እንዳለ ጠቁመው “ሐሰት ነው” ብለዋል ኮሚሽነሩ።

“አካባቢው ሰላማዊ ነው” ያሉት አቶ ምትኩ በትግራይ ክልል በሚሰሩ አንዳንድ ድርጅቶች ሆን ብሎ የተደረገ ነው በማለትም ወንጅለዋል።

በተጨማሪም “መንግሥት በክልሉ ውስጥ ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመ ነው” የሚሉ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ አካላት የወጡ ሪፖርቶችን ያጣጣሉት አቶ ምትኩ በአብዛኛው የትግራይ ክልል እርዳታ በመስጠት የሚንቀሳቀሱት አጋር ድርጅቶች ናቸው ብለዋል።

በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የአርዳታ ድርጅቶች አስፈላጊውን እርዳታ ለማቅረብ አቅሙም እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የፌደራሉ መንግሥት በአብዛኛው በምዕራብ ትግራይ ሁመራ፣ ማይካድራና ሌሎች አካባቢዎችን ጨምሮ በ40 ወረዳዎች ውስጥ በዋነኝነት የእርዳታ አቅርቦቱ ስርጭት እንደሚያከናውን አመልክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ረሃብ (ፋሚን) ብሎ ለማወጅ ሦስት ዓለም አቀፍ መስፈርቶች በአንድነት መሟላት እንዳለባቸው አቶ ምትኩ ጠቁመዋል ይህ ሁኔታ በትግራይ እንዳልተከሰተ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ መስፈርቶች ብለው የጠቀሷቸው በአንድ አካባቢ 20 በመቶ ቤተሰቦች የምግብ እጥረት ሲገጥማቸውና ለመኖር አሰቸጋሪ ሲሆን፣ ከ30 በመቶ በላይ ህፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ሲሰቃዩ እና ረሃብ ከአስር ሺህ ነዋሪዎች መካከል በየቀኑ ከሁለት ሰው በላይ ሲገድል የሚል ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ 20 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የምግብ እጥረት እንዳጋጠመው ነው ሪፖርቶች የሚያሳዩት ቢሉም “በክልሉ ምንም አይነት የምግብ እጥረት የለም ምክንያቱም 91.3 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በአምስት እርዳታ ድርጅቶች እየተረዱ ይገኛሉ” ብለዋል አቶ ምትኩ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ እርዳታ ኃላፊ ማርክ ሎውኮክ ባለፈው ሳምንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በትግራይ ክልል ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ እንደተጋለጡ በመግለጽ የከፋ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ ገብረ ህይወት በቅርቡ በሰጡት ቃለ መጠይቅ አርሶ አደሮች እንዳያርሱ ተከልክለዋል ያሉትም ጉዳይ በጋዜጠኞች የተነሳ ሲሆን ይህ ተፈፅሟል ወይ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ምትኩ በምላሹ “ሐሰት ነው” በትግራይ ክልል 70 በመቶ የሚሆነው አካባቢ ታርሷል ብለዋል።

አቶ ምትኩ ይህንን ያሉት የግብርና ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የተሻሻለ ዘርና ማዳበሪያም በክልሉ እንደተከፋፈለ በዚሁ አጋጣሚ አስረድተዋል።

ምክትል የትግራይ አስተዳደሩ ይህንን ቢናገሩም ከሚዲያ ጋር ለሁለተኛ ጊዜ በነበራቸው ቆይታ ይህንን ማስተካከላቸውን አቶ ምትኩ ለጋዜጠኞቹ ገልፀዋል።

የሰብዓዊ እርዳታን በተመለከተ

በክልሉ ውስጥ እስካሁን ለ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እርዳታዎች በመጀመሪያው ዙር፣ በሁለተኛውና በሦስተኛው ዙር ለ5.2 ሚሊዮን ሕዝብ እርዳታ መቅረቡን አቶ ምትኩ ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት ኮሚሽነሩ እንደሚሉት በ5.4 ቢሊዮን ብር የሚገመት 170 ሺህ 798 ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለክልሉ ተከፋፍሏል።

በመጀመሪያውና በሁለተኛው ዙር የተከፋፈለውን የምግብ ወጪ 70 በመቶ መንግሥት የሸፈነ ሲሆን ሰላሳ በመቶውን ደግሞ አጋሮች ሸፍነዋል ተብሏል።

በሦስተኛው ዙር ግን መንግሥትን ጨምሮ ስድስት አካላት ማለትም የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ወርልድ ቪዥን፣ ኬር ኢንተርናሽናል፣ ሪሊፍ ሶሳይቲ ኦፍ ትግራይ፣ ፉድ ፎር ሃንግሪ እርዳታ እያደረሱ እንደሚገኙም ተጠቁሟል።

እነዚህ የአጋር ድርጅቶች 84.9 በመቶ የትግራይ ወረዳዎችን በመሸፈን 91̄.3 በምግብ አቅርቦትና ስርጭት አያደረሱ እንደሚገኙም ተነግሯል።

መንግሥት በእነዚህ አካባቢዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ፣ እርዳታው እንዲሰራጭ ምቹ ሁኔታንም ለመፍጠር ከአጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አቶ ምትኩ ጠቁመዋል።

የተለያዩ የሰብዓዊ አርዳታ አጋሮች በክልሉ 5.2 ሚሊዮን ወይም ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ አስቸኳይ የሰብዓዊ አርዳታ ያስፈልገዋል ቢሉም አቶ ምትኩ በበኩላቸው ከነዚህ ውስጥ 1 ሚሊዮን 10 ሺህ 752 ሰዎች የሴፍቲ ኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ ናቸው፤ እንዲሁም 40 ሺህ 336 ደግሞ ኤርትራውያን ስደተኞች ናቸው ብለዋል።

እነዚህ የጠቀሷቸው ፕሮግራሞች “የራሳቸው ፈንድ አላቸው” አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ ከሚያስፈልጋቸውም ጋር በቅንጅት ሊታዩ እንደማይገባም ይናገራሉ።

ሆኖም አቶ ምትኩ በክልሉ እርዳታ ለማቅረብ ተግዳሮቶች እንዳሉ የጠቆሙ ሲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያና ተኩስ በመኖሩ የፀጥታውና የደኅንነት ሁኔታውን ስጋት ላይ መጣሉን ጠቁመው በዚህም የወታደሮች እጀባ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል አስቸኳይ መጠለያና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እጥረት ሌሎችም ችግሮችም እንዳሉ ጠቁመዋል።

“ምግብ ነክ ባልሆኑ ቁሶች እርዳታ ላይ ከፍተኛ የሚባል ክፍተት አለ” የሚሉት አቶ ምትኩ ለዚህም በዋነኝነት የሚያነሱት አጋሮች እየሸፈኑ ያሉትም 33 በመቶ ወጪውን መሆኑን ነው።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮችን በተመለከተ፤ አቶ ምትኩ በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች ሦስት አማራጮች የቀረበላቸው ሲሆን ሰላማቸው በተረጋገጡ አካባቢዎች ተፈናቃዮች በፈቃዳቸው ዓለም አቀፉን ድንጋጌ መሰረት ባደረገ መልኩ ወደመጡበት እንዲመለሱ፣ በሁለተኛ ደረጃ አካባቢያቸው ያልተረጋጋ ከሆነም የቅርብ ቤተሰብና ዘመዶች ካሏቸው ከእነሱ ጋር እንዲቆዩ፣ ሁለቱን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ በመጠለያዎች እንዲቆዩ የሚል ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በምዕራብ ትግራይ የተፈናቀሉ የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ ምላሽ የሰጡት አቶ ምትኩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት አርባ አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን አመልክተዋል።

እነዚህን ተፈናቃዮች የክረምት ወር ከመጀመሩ በፊት ወደመጡባቸው ቦታዎች ለመመለስ እቅድ የተያዘ ሲሆን ኮሚቴውም የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንቶችንም በአባልነት እንዳካተተ ተጠቁሟል።

በክልሉ የጤና ርዓትን በተመለከተ

በትግራይ የጤና ሥርዓቱን ወደነበረበት ለመመለስ የጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ ኤጀንሲዎች እየሰሩ ነው የተባለ ሲሆን ይህንንም ለማከናወን አንድ ግብረ ኃይል መሰማራቱን የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ተናግረዋል።

የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች ከብሔራዊ ተቋማት ተሰማርተው የክልሉን የጤና ቢሮ እየረዱ እንደሚገኙም ተገልጿል።

የክልሉን ጤና ሥርዓት ከመመለስ ጋር በተያያዘ ዋነኛ የተባለውም ሥራ የጤና ተቋማቱ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ 55 በመቶ የሚሆኑት ሆስፒታሎች እንዲሁም 52 በመቶ የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

አገልግሎት በሚሰጡ ሆስፒታሎችም ሆነ የጤና ማዕከላት 95 በመቶ የሚሆኑት የጤና ባለሙያዎች በየቀኑ አገልግሎት መስጠት መቀጠላቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ የቀሩት የጤና ተቋማት ላይ የደረሰባቸው ጉዳት ተግመግሞ መልሰው እንዲቋቋሙና አገልግሎት እንዲጀምሩ ከፌደራል መንግሥት በኩል ለ14 ሆስፒታሎችና 58 የጤና ማዕከላት ገንዘብ ተመድቧል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አስፈላጊ የሚባሉ የጤና ቁሳቁስ ግብዓቶች እንደ አልትራ ሳውንድ፣ ቬንትሌተር፣ ማይክሮስኮፖች መላኩን የገለፁት ሚኒስትሯ፤ እስካሁንም ባለው ከ310.8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች ወደ ክልሉ መላኩን አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በክልሉ ለጤና አገልግሎት አስፈላጊ ግብዓቶች 215 ሚሊዮን ብር ተመድቦ አገልግሎት ላይ እየዋለ ይገኛል ተብሏል።

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) መጋቢት ወር ላይ ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል በሚገኙ የህክምና ተቋማት ላይ ሆን ተብሎ ዘረፋ እና ጥቃት ተፈጽሟል ሲል ገልፆ ነበር።

ድርጅቱ በዚሁ መግለጫው አንዳንዶቹ ዘረፋዎች የተፈፀሙት በወታደሮች ጭምር ነው ያለ ሲሆን 13 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማት ብቻ በአግባቡ እየሰሩ ነው ማለቱ የሚታወስ ነው።

በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማትን አገልግሎት ከማስጀመር ጋር ተያይዞ ተንቀሳቃሽ የጤና የህክምና አገልግሎትን መመለስ ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ተቋማቱ በውስን ደረጃም አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በተለይም እናቶችና ህፃናት ላይ አተኩሮ የክትባትና ሌሎች የህክምና አገልግሎት በተለያዩ ወረዳዎች እየተሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በባለፉት ሁለት ወራት ከ75 ሺህ የሚበልጡ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ህፃናት ወደ ጤና ማዕከላትና ተንቀሳቃሽ የህክምና መስጫ ማዕከላት መምጣታቸውን ሚኒስትሯ ተቋማቱን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።

ከነዚህም መካከል 4 በመቶዎቹ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን አስፈላጊው የህክምና እንክብካቤና አገልግሎት አግኝተዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ በአጠቃላይ አገልግሎት በሚሰጡት የጤና ተቋማት 409 ሺህ የክልሉ ነዋሪዎች በባለፉት ወራት አገልግሎት እንዳገኙም ተገልጿል።

ክልሉ በርካታ የአምቡላንስ አገልግሎቶቹን ከማጣቱ አንፃር በአሁኑ ጊዜ ሚኒስቴሩን ጨምሮ ከሌሎች አካላት በተገኘ እርዳታ 58 አምቡላንሶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ 65 ጥገና ላይ ሲሆኑ ሌሎቹንም በተጨማሪነት ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል።

በተጨማሪም ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ አስፈላጊ የሚባሉ የጤና አገልግሎቶች በነፃ እየተሰጡ እንደሆነ ሚኒስትሯ ተናግረዋል። ይህንንም ለማገዝ በጤና ሚኒስቴር አማካኝነት ተጨማሪ ባለሙያዎችን በማሰማራትና ጊዜያዊ የጤና ማዕከላትን በማቋቋም እየተረዱ እንደሚገኙም ተነግሯል።

በዚህ ጦርነት የተደፈሩ ሴቶችን አስፈላጊ ህክምና ለመስጠት የሥነ አዕምሮ ህክምናን ጨምሮ የማማከር ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎች በስድስት ከተሞች ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በክልሉ የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የክልሉ የጤና ቢሮ ከ28 አጋሮች ጋር እየሰሩ ነው ቢባልም እንደዚያም ሆኖ በርካታ ችግሮች ተደቅነዋል ብለዋል።

Amharic BBC


Exit mobile version