ETHIO12.COM

ለ30 ሰዓታት ያህል ያለማቋረጥ ተዋግተናል – ብ/ጀነራል ናስር አባ ዲጋ

ሰኔ 16 ቀን 2013

የክፋት አለቃው ህወሀት መራሹ ወንበዴ ቡድን በክፋት ሰይፉ ጉዳት ካደረሰባቸው የሰራዊት ክፍሎች መካከል ብ/ጀነራል ናስር አባዲጋ የሚመሩት የ8ኛ ሜካናይዝድ ክ/ጦር ይገኝበታል።

ሜካናይዝድ ክፍለ ጦሩ የደረሰበትን የክፋት ጥቃት ተቋቁሞ ሃይሉንና ትጥቁን በመያዝ እየተዋጋ ወደ ጎረቤት ሃገር ኤርትራ ከተሻገረ በኋላ እንደገና ሃይሉንና ትጥቁን አቀናጅቶ እየተዋጋ የገባ ክፍለ ጦር ነው።

እስከ ሽራሮ እየተዋጋ መጥቶም ፣ ከሰሜን ምዕራብ ግንባር ዳንሻ ጀምሮ እየተዋጋ ከመጣው ምዕራብ ዕዝ ጋር በመቀናጀት እስከ መቀሌ ከዛም ጁንታው ተበጣጥሶ በረሃ እስከገባበት ጊዜ ድረስ በውጤት እርቀቱ ሆኖ ከባድ ምት በማሳረፍ የነበረው ሚና በቃላት ከሚገለፀው በላይ ነው።

መቀሌን እንደተቆጣጠርን የሜካናይዝድ አዛዡን ብ/ጀነራል ናስር አባዲጋን አግኝቼ ስለ ጥቃቱ አናግሪያቸው ነበር። እሳቸውም የሚከተለውን ብለውኛል።

ሰራዊቱ የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈፀም ምሽግ ላይ በነበረበት ከጀርባው ቃላት በማይገልፀው ጭካኔ በጥይት ተመቷል, በሳንጃ ታርዷል። በውድቅት ሌሊት በተኛበት እጅ ወደ ላይ እያሉ ከልጁ እና ከሚስቱ እየነጠሉ በክፋታቸው በልተውታል። ድርጊቱ የሰው ልጅ ሆኖ ሰው ላይ የሚፈፀም አይደለም። በውትድርና አገልግሎት ዘመኔ እንደዚህ አይነት ክህደትም, ጭካኔም አይቼም ሰምቼም አላውቅም። ድርጊታቸው አረመኔያዊ ነው።

ለምሳሌ ታንክ ሾፌር በምንም አይነት ጭንቅላቱን አይመታም። ጠላት ከገባ ቦንብ ወርውሮ ታንክ ጋር ምድብተኛውን ያቃጥላል እንጂ። በነፍስ ወከፍ ጥይት ግን ጭንቅላት አይመታም። ይህን ያደረገ ውስጣችን የተደራጀ ጠላት ነው። የጠነከረብንም ውስጣችን የተደራጀው ጠላት ነው። በዚህም ብዙ ጎድተውናል። ነገሩ በጣም ዘግናኝ ነው።

ጥቃቱን የፈፀሙበት እለት መብራትና ኔትወርክ አጥፍተው ነበር። ሃሳባቸው በተኛንበት የቻሉትን ገድለው የቻሉትን ማርከው መሳሪያ መቀበል ነበር። ግን አልተሳካላቸውም። የመጣ መኪና ከ40 በላይ ነው። ለሰላሳ ሰዓታት ያክልም ያለማቋረጥ ተዋግተናል። ውጊያውን ማሸነፍ እንደማይችሉ ሲያውቁ ልዩ ሃይል ኮማንዶ ከቤተ መንግስት እናስመጣለን እያሉ ነበር። ይህም ጀግንነታችን አላስቆመውም።

መጨረሻ ላይ ሙሉ ሃይላችንን ይዘን ወደ ጎረቤት ሃገር ኤሪትራ ተሻገርን። እንደ ክፍለ ጦር እስታፍ ደግሞ 85 ፐርሰንቱ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ነበሩ – በተለይ በሀላፊነት ቦታ። ውጊያው ከነዚህ ጋርም በመሆኑ ነው የከበደን። ነገሩን ይፋ ሳያወጡ ውስጥ ለውስጥ ብዙ ነገሮችን ሰርተዋል። መገናኛ አካባቢ ትልቅ እንቅፋት ፈጥረዋል።

ግምጃ ቤትም ከፍተው አስታጥቀዋል።ንብረት ጫን አትጫንም ከፍተኛ ችግር ፈጥረዋል። የተሽከርካሪ ነዳጅ ለመሙላት ብዙ አስተጓጉለውናል። መጨረሻም ዝገግጅታችን ጨርሰን ወደ ጓል ባድመ ተንቀሳቀስን። ወደዛ እየሄድን እንደሆነ እኔ እና ኮሚቴዬ ነበር የምናውቀው። ኮሚቴዬ ግን የምናደርገውን ሁሉ ለጁንታው አለቆች ያሳውቅ ነበር። በጉዟችንም ብዙ እንቅፍቶች ተፈጥረዋል።

እንቅፋቶችን እያስወገድን ጓል ባድመ እንደደረስንም ከሌሎች አሃዶች ጋር መልሶ መቋቋም አድርገን እንዋጋለን ብለን ተነሳን። ከማዕከል ከመጡ አመራሮቻችን ጋር ተገናኝተን ስለ ሁኔታው ተነጋገርን። በጥቃቱ ሰራዊቱ እጅግ ተቆጥቷል። ፈጥነን ገብተን ለምን አንደመስስም የሚል ከፍተኛ ተነሳሽነት ፈጥሯል።

ለሰዎቹ የመጨረሻ ቅጣት ሞት ቢባል እንኳ ሞት ያንሳል። አንድ ሺ ጊዜ ቢሞቱም ቅጣት አይሆንም። ቤተሰብ ነበርን። አንድ ነበርን። ብዙ ነገሮችን አብረን አሳልፈናል። እኔ ወደ ትግራይ ምድር የገባሁት ከኢትዮ-ኤሪትራ ውጊያ ጀምሮ ነው። ያ ማለት ወደ ሃያ ሶስት ዓመት ያክል ሆኖኛል ማለት ነው። በዚህ ዓመት ውስጥ የሰራነው ቀላል አይደለም። ትግራይ ለማች የምትባለው በኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ነው። በወታደሩ ደሞዝ ጭምር ነው። በተለይ መከላከያን ይመለከታል።

ትግራይ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ተሸላሚ ነበረች። ማንም የተከለው አይደለም። 80 ፐርሰንት ሰራዊቱ በጉልበቱና በገንዘቡ የተከላቸው ችግኞች ናቸው። ብዙ ትምህርት ቤቶችና መንገዶች ሰርተናል። ከጀርባ ሊወጉን እየተዘጋጁ እንኳ ት/ቤት ገንቡልን የሚል ጥያቄ አንስተዋል። ለዚህ ግንባታ ነው ሰራዊት ቀስቅሰን ብር እየሰበሰብን የነበረው። ሽሬ ላይ ለሚኖሩ አካል ጉዳተኞች የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እስከ አራተኛ ፎቅ ድረስ ገንብተናል። ለዚህ ግንባታ ኮሚቴው እኔ ነኝ የነበርኩት። ሰራዊቱም ገንዘቡን ለማዋጣት አይሰስትም ነበር።

ሰራዊታችነ ከዓመት ዓመት ሙሉ ደመወዙን ወስዶ አያውቅም። ጥቃቱ የደረሰ ዕለት እንኳ በክልሉ በስፋት የተከሰተውን አንበጣ ለመከላከል ከህዝቡ ጋር ስራ ነው የዋልነው። በአጠቃላይ ለትግራይ እንደ ጫማ ሶል ሆነን ነው ስናገለግል የነበረው። አንድም ቀን እነሱን የሚጎዳ ነገር አስበንም አድርገንም አናውቅም።

ለእኛ ይህ አይገባም ነበር። ሰራዊቱን ያስቆጣውም ያነሳሳውም ይህ ነው። ሁሉንም አውዶች በጀግንነት ነው ሲፈፅሞ የነበረው። ውጊያው በአጭር ጊዜ የተቋጨውም ለዚህ ነው። በተገኘው ድል ደግሞ ከምናገረው በላይ ደስተኛ ነኝ። የሜካናይዝድ ክፍለ ጦሩ አባላትም እንደዛው። አሸናፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ነውና !

ታገል አልማው
ፎቶግራፍ ሽመልስ እሸቱ via defence force Fb

Exit mobile version