Site icon ETHIO12.COM

“ሕወሓት ከጅምሩ አጥፊ ቡድን ነው” ብ/ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ

ሕወሓት ከጅምሩ ለጥፋት የተሰለፈ አጥፊ ቡድን ነበር ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንን የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ንጋቱ ገለጹ። የትግራይ ሕዝብ “በመንግስት የተወሰደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ መልኩ መቀበል አለበት” ሲሉም ብርጋዴር ጄኔራሉ ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን በትግራይ ክልል የተወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ወታደራዊ እይታ ምን መልክ እንደነበረው ይናገራሉ። ብርጋዴር ጄኔራሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እርሳቸው የኢትዮጵያን ሰራዊት የተቀላቀሉት በ1953 ዓ.ም እንደነበር ይጠቅሳሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ የጦር መኮንኑ በታንከኛ ምድብ በምስራቁ ጦርነት በኦጋዴን ቶጎ ጫሌ ግንባር በተደረገ ውጊያ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ ግንባሮች ተሳትፈዋል።

በአሜሪካና በሩሲያ የተለያዩ ጦርነት ተኮር ሥልጠናዎችን የወሰዱት ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን፤ የኢትዮጵያ ጀግኖች የጦር ሜዳ ውሎ ላይ ያተኮሩ ሁለት መዕሀፍት ጽፈዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት፤ የደርግ መንግስት ባጋጠሙት የተለያዩ ችግሮች ‘ወንበዴው የሕወሓት’ ቡድን አዲስ አበባን እስከሚቆጣጠር ድረስ አገራቸውን በውትድርና አገልግለዋል። በመጨረሻም በ’ሕወሓት’ ቁጥጥር ስር ውለው ለአስር ዓመታት ያለ ፍርድ አዲስ አበባና ከዙሪያዋ ከሚገኙ እስር ቤቶች እስከ መቀሌ ተወስደው ታስረው፤ ተሰቃይተዋል።

ሕወሓት ከጅምሩ ለጥፋት የተሰለፈ አጥፊ ቡድን እንደነበረም ብርጋዴር ጄኔራል ዋስይሁን ይናገራሉ። ከፍተኛ የጦር መኮንኑ በውትድርናው ዓለም ያካበቱትን ልምድ ጠቅሰው፤ በሕወሓት የሚመራው ቡድን የመከላከያ ሰራዊትን ማጥቃቱን ሲሰሙ እጅግ ማዘናቸውን ይገልጻሉ።

ከዚያም በኋላ በአገር መከላከያ ሰራዊት ሲወሰድ የቆየው ወታደራዊ እንቅስቃሴ የአገር ሉዓላዊነትን ያስከበረ ተግባር እንደሆነም መስክረዋል። ይህ ባይሆን ኖሮ የቡድኑ ‘እብሪተኝነት’ በከፍተኛ ሁኔታ ኢትዮጵያን ዋጋ ያስከፍል እንደነበረም በማስታወስ፤ በዚህ ወቅትም የአገር መከላከያ ሰራዊት ክልሉን ለቅቆ መውጣቱ ተገቢ እርምጃና የሚደገፍ ነውም ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብም ይህንኑ በፌዴራል መንግስት በኩል የተወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ በበጎ መልኩ መቀበል እንዳለበት ነው ያብራሩት። በቀጣይም የቡድኑ አባላትና ታዛዦቻቸው በመንግስት የተሰጠውን እድል የማይቀበሉ ከሆነ “አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብለዋል።

ከፍተኛ የጦር መኮንኑ የእስራኤል ታዋቂ ጄኔራል ሞሼ ዳያንን ጠቅሰው፤ ”ሰላም፤ ፍቅር የማይገዛ ከሆነ ሀይል መጠቀም ያስፈልጋል” ሲሉ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ። ምንም እንኳን ይህ አካሄድ ባያዋጣም ቡድኑና ከቡድኑ ጋር ተያያዥneት ያላቸው አካላት ከቀድሞ ስህተታቸው መማር እንዳለበቸውም ነው የገለጹት።

Exit mobile version