Site icon ETHIO12.COM

ምግብ በመመረዝ ሶስት ሰዎች ገለዋል የተባሉ ተያዙ፤ ፍርፍሩን የበሉ ውሻና ድመት ሞተዋል

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ወረጃርሶ ወረዳ ምግብን በመመረዝ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ የሶስት ሰዎች ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ መምሪያ ምክትል ኃላፊ ኢንስፔክተር ታምሩ ባይሣ ዛሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤በወረጃርሶ ወረዳ አዋሬ ጐልጄ ቀበሌ ልዩ ስሙ በዳዳ ገብርኤል አካባቢ ነዋሪ የሆኑት የእነዚህ ሰዎች ህይወት ያለፈው ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ነው።

ህይወታቸው ያለፈው በዕለቱ ጠዋት ቁርሳቸውን ለጊዜው በውል ባልታወቀ ሁኔታ የተመረዘ የእንጀራ ፍርፍር በመመገባቸው ሳይሆን እንዳልቀረ አስረድተዋል።

ሟቾቹ የ50 እና 14 ዓመት እድሜ ያላቸው ሁለት ሴቶች እና የሶስት ዓመት ወንድ ህፃን ልጅ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከዚህም ሌላ ፍርፍሩን የበሉ ውሻና ድመት መሞታቸውን አመልክተዋል፡፡

ፖሊስ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑን ኢንስፔክተር ታምሩ አስታውቀዋል፡፡ የሟቾቹ አስክሬን ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ አቤት ሆስፒታል እና ተመርዟል የተባለው የምግቡ ናሙና ደግሞ ለብሔራዊ የሥነ-ምግብና መድሀኒት ምርምር ኢንስቲትዩት ተልኮ ውጤት እየተጠበቀ ነው ብለዋል፡፡

Exit mobile version