በ25 ሄክታር የባለሃብቶች አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች ተያዙ

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ወረዳ በ25 ሄክታር የባለሃብቶች አትክልትና ፍራፍሬ ማሳ ላይ ጉዳት በማድረስ የተጠረጠሩ 19 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር ሱልጣን በያን ለኢዜአ እንደገለጹት ተጠርጣሪዎቹ ትላንት አመሻሽ ላይ በማሳው ላይ ጉዳት አድርሰዋል ።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን በድርጊቱ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠረጠሩ 19 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑን ተናግረዋል ።

ፖሊስ ሌሎች በጉዳዩ የተጠረጠሩን በቁጥጥር ስር ለማዋል የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ ክትትል እያደረገ መሆኑን ገልጿል ።

“በባለሀብቶች የለማ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት በፀረ ልማት ሃይሎች ጉዳት ደርሶበታል” ሲሉ ዋና ኢንስፔክተር ሱልጣን አክለዋል ።

“ድርጊቱ ከህብረተሰቡ ባህልና እሴት ያፈነገጠ አሳዛኝ ክስተት ነው” ያሉት ደግሞ የሊበን ጭቋላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሀምሳሉ ቶሎሳ ናቸው።

“ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተቸገረ ባለበት ወቅት ይሄ መሆኑ ያሳዝናል” ያሉት አስተዳዳሪው የድርጊቱ ተዋናይና ፈፃሚዎች ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የፍትህና የፀጥታ አካላት እንዲሁም አስተዳደሩ ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ።

ህዝቡ የራሱንና የአካባቢውን ልማት በመንከባከብ ፀረ ልማት ሃይሎችን በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ኢዜአ

See also  የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕወሃት የሽብር ቡድን አባላት ሕንጻዎች በገለልተኛ አስተዳዳሪ ተይዘዉ እንዲተዳደሩ ወሰነ

Leave a Reply