Site icon ETHIO12.COM

እናት አበበች ጎበና አረፉ

ደግዋ እናት አበበች ጎበና ዛሬ ጠዋት ህክምና ሲከታተሉ በቆዩበት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ማረፋቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አረጋግጧል።ክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና (እዳዬ) በኮሮና ተጠቅተው በጳውሎስ ሆስፒታል በጽኑ ሕሙማን ክፍል ሕክምና ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ዛሬ ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አበበች ጎበና በተለምዶ አባ ኮራን ሰፈር ቀበሌ 07 የእስላም መቃብርን ከሚያካፍለው የድሮ ጅረት (ወንዝ) ወደላይ ባስገነቡት የሕጻናት ማሳደጊያ ቢታወቁም፣ እናት አበበች ማንም ሳይደግፋቸው ወንዝ እየዋኘን ስንወጣ ሙልሙል ዳቦ አብልተው፣ የነጣውን ሰውነታችንን ቫዝሊን ቀብተውና ጸጉራችንን አውዝተው ወደ ቤታችን ይልኩን ነበር።

የነጭ እጅ ሳይዘረጋላቸው ወተት ይግቱን ነበር። ወደ ደረታቸው አስጠግተው እንደ ወላጅ እናት እየዳበሱ ያጎርሱን ነበር። ከአባባ ገብረህይወት ወፍጮ ከፍ ብሎ ከነ ሸምሱ ቅጠል መሸጫ ዝቅ ሲል ባለው የደጃቸው መግቢያ ቆመው ለበርካቶች ፍቅር ያድሉ ነበር። እጃቸው በዕርዳታ ሲሞላ አንዳንድ ስግብግቦች በመሰሪነት ወረዋቸው የነበረ ቢሆንም አምላክ አግዟቸው የጀመሩትን ደግ ተግባር ሳይሰናከሉ ከዳር አድርሰዋል። በጥቂቱ ጀምረው በዓለም ታውቀዋል።

በዚሁ ደግነታቸውና ታታሪነታቸው ክብርት ዶ/ር አበበች ጐበና ተብለዋል። ተመርቀዋል። ድግነታቸውን በሚገልጹ በርካታ ስም ተሞግሰዋል። አምረዋል። ግን ምንም ይባሉ ምን ” እማዬ” ስማቸው ነው። እማዬ ፋሽስት ኢጣልያ ጦር ሀገራችንን በ1928 ዓ.ም በወረረበት ወቅት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ በግራር ጃርሶ ወረዳ በቶርበን አሼ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ሸበል አቦ በተባለች የገጠር መንደር እንደተወለዱ አዲስ ዘመን መረጃውን አገላብጦ ዘግቧል።

በወቅቱ በነበረው ባህልና ልማድ ገና የ11 ዓመት ልጅ እንዳሉ ትዳር ለመያዝ ተገደዱ፡፡ ሆኖም የቀረበላቸውን የጋብቻ ጥያቄ በብቸኝነት በመቃወም ወደ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ በአዲስ አበባ ስራን ሳይንቁ ከግለሰቦች ቤት አገልግለዋል። የምርት ክፍል ኃላፊነት መሆን ችለዋል።

ክብርትዶ/ር አበበች(እዳዬ) በአዲስ አበባ እና ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ አብያተ ክርስትያናትን በማገልገል ከፍተኛ ድርሻና አበርክቶ ነበራቸው፡፡ በዚህም አጋጣሚ በ1972 ዓ.ም ለመንፈሳዊ ጉዞ በሄዱበት በሀገራችን ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮ ድርቅ ሳቢያ ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሁለት ህፃናትን በመያዝ አበበች ጐበና ህፃናት ክብካቤና ልማት ማህበርን መሰረቱ።

ክብርትዶ/ር አበበች(እዳዬ) ባለፉት 41/አርባ አንድ አመታት/ ብዙ መቶ ሺህ ህፃናትን ተንከባከበው ለቁም ነገር ያበቁ ሲሆን በተለይዩ ድህነት ቅነሳ ፐሮግራሞች ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ሰተዋል፡፡

በተለያዩ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መድረኮች ታላላቅ ሽልማቶችና እውቅናዎችን እንዲሁም ከጅማ ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ድግሪ በሰብአዊነት አግኝተዋል፡፡ ክብርትዶ/ር አበበች(እዳዬ) ድህነትን በተለይም የህፃናት ጉስቁልናን መቅረፍ የሚቻለው “በግለሰብ ደረጃ ለምፅዋት በሚወረወሩ ሽርፍራፊ ሳንቲሞች ሳይሆን በአንድነት በማበር እና ያለንን አቅም በማሳሰብ በችግር ላይ ያሉ ወገኖቻችንን በተለይም ሴቶችን ስናበቃ ነው” የሚል እምነት ነበራቸው፡፡

እኚህ እንቁ እናት በቅርቡ በኮሮና በሽታ ምክንያት በጳውሎስ ሆሰፒታል በጽኑ ህሙማን ክፍል ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ጠዋት በተወለዱ በ85 ዓመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡በክብርት ዶ/ር አበበች ጎበና ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሀዘን እንገልጻለን። ሃዘናቸውን ምትክ በመፍጠር እንድናስበው ጥሪ እናደርጋለን።

ዜናው ከአዲ ዘመን የተወሰደና ዝግጅት ክፍሉ የሚያውቀውን የጨመረበት ነው

Exit mobile version