Site icon ETHIO12.COM

“ወገን አለን አሁን ቁስላችን ጠግጓል ፣ ባይተዋርነት ያደረገው ሽንቁር ተደፍኗል” መከላከያ

“ህዝባችን ሆይ በወገናዊ ፍቅርህ ልባችንን ሞልተኸዋል፣በእንክብካቤህ ውስጣችንን በደስታ አረስርሰኸዋል፣ የማይነጥፍ የእናት ፍቅር ፣ የአባት አለኝታነት ፣ የወንድም ጥላ ከለላነትን፣እህትነትና እንስፍስፍነት ደጀኑ ህዝባችን አሳየን።በልተን የማንጠግብ የሚመስለው ደጉ ህዝብ አላይ በላይ አጎረሰን” ሲሉ ሻምበል አስቻለው ሌንጫ ገለጹ።

የአገር መከላከያ አፈግፍጎ ደጀን ወደሆነው ሕዝብ ሲጠጋ ያዩትን ያመለከቱት ሻምበሉ ሕዝቡን ” በሃሳብ ስሜቱ ፣ በአዕምሮ ልቦናው፣ ላፍታም ሳይለየን አብሮን እንደነበረ ያስመሰከረበት አቀባበል አስደምሞናል” ሲሉ አድነቀዋል። መገረማቸውን ገልጸዋል።

“ወገን የሌለን ይመስል፤በምድር ላይ ብቻችንን የቀረን ያስመሠለንን ፈተና አሁን ፈፅሞ ማስታወስ አንሻም” ሲሉ ከገጠማቸው ክህደት በላይ ደጀኑ ሕዝብ ያሳያቸውና የሰጣቸው ፍቅር ቁስላቸውን እንዳሻረው አመልክተዋል።

ሻምበሉ መገረማቸውን ከገለጹ በሁዋላ “የዚህን ፍቅር የሆነ ህዝብ ደስታ ለማጨንገፍ የዳዳ ፣ ክብር ኩራቱን ለማሳጣት የሞከረ ፣ ሰላሙን ሊያሳጣ ላሰበና ለተመኘ ከቶውኑም እንቅልፍ የለንም ፡ ሲሉ አደራቸው ግዙፍ፣ ጽናታቸው ከፍተኛ፣ ቁረኛነታቸው ወደር የሌለው መሆኑንን ገልጸዋል። ይህንን ካሉ በሁዋላ ስብራታቸው አቅፎና ደግፎ ለጠገነ ወገናቸው “አዎን በእጅጉ ኮርተናል” ሲሉ ክብር ሰጥተዋል።

“ህዝባችን ሆይ በወገናዊ ፍቅርህ ልባችንን ሞልተኸዋል፣በእንክብካቤህ ውስጣችንን በደስታ አረስርሰኸዋልና ፤ ባንተ የመጣን ብንምረው አይማረን ብለናል” ሲሉ ቃላቸውን አጉልተው አሰምተዋል። ቀጥለውም “ይብላኝ ለእነርሱ እንጂ ከዚያ ሁሉ መከዳት በኋላ በዕልፍ አዕላፍ ወገናችን የነፃና የእውነት ፍቅር ልባችን ሞቆ ወኔያችን ላይበርድ ግሏል” ብለዋል። ሻምበል አስቻለው ለመከላከያ ሰራዊት ህጋዊ ድረገጽ ያሰፈሩትን ሲያጠቃልሉ “የትኛውም ባንዳ ሆነ ባዳ በኢትዮጵያችን ከመጣ እሱን አያድርገን” ሲሉ ደጀን የሆነው ሕዝብ ጉያ ስር ከገቡ በሁዋላ ያለውን መንፈስ ገልጸዋል።

Exit mobile version