Site icon ETHIO12.COM

ከጤና ሙያ ጋር የተያያዙ ጥፋቶች የአስተዳደርና የፍትሐብሔር ኃላፊነት

  1. የሕክምና የሙያ ስህተት / Medical Malprctice /
    የህክምና የሙያ ስህተት የሚለዉ ፅንሰ ሀሳብ ወጥ የሆነ የሕግ ትርጉም አልተሰጠዉም፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ የህክምና ስህተት ማለት አንድን የህክምና ባለሙያ ባለዉ አቅምና ችሎታ የህክምና ሥራዉን በሚያከናዉንበት ጊዜ ለሚሰራዉ ሥራ ጥንቃቄ በጎደለዉ መልኩ ወይም ጥንቃቄ መዉሰድ ሲገባዉ ሊመጣ የሚችለዉን ጉዳት እያወቀ ወይም ማወቅ ሲኖርበት በታካሚዉ ላይ ጉዳት ማድረስ ነዉ፡፡ ታካሚዉና የህክምና ጤና ተቋሙ የህክምና ዉል በመፈጸም ግዴታ ሲያቋቁሙ ታካሚዎች በሚታከሙበት ጊዜ በታካሚዉ ላይ ሊመጣ የሚችለዉ ጉዳትና አዳጋ በመገንዘብ አካሚዉ ጥንቃቄ በጎደለዉ መልኩ ከተከናወነ ለሚደርሰዉ ጉዳት እንደዉሉ ያልተፈፀመ በመሆኑ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ1962 የወጣዉ የፍትሐብሔር ሕግ የጤና ባለሙያዉ የማዳን ዋስትና የለዉም እንደሚል በመጥቀስም የጤና ባለሙያ ለማዳን ዋስትና እንዲሰጥ እንደማይገደድ ተደንግጓል፡፡ ለዚህም ነዉ አንድ ታካሚ የሚጠበቀዉን የሕክምና ዉጤት አላገኘሁም በማለት የሕክምና ባለሙያን ለመክሰስ የማይችለዉ፡፡ የሕክምና ስህተት ሕግ ሀኪሞች ወይም ሌላ የሕክምና አገልግሎት ሰጪ አካላት የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በታማሚው ላይ በቸልተኝነት ለሚያደርሱት ጉዳት ያለባቸውን ተጠያቂነት የሚገዛ ሕግ ነው፡፡ ቸልተኝነት ከደረጃዉ ዉጪ ሕክምና መስጠት ወይም የታወቀ የሕክምና ሥነ-ሥርዓትን በጤና ባለሙያዎች የተለመደ አሰራር መሰረት አለመከተል ነዉ፡፡ አንድ የሕክምና ባለሙያ የሕክምና አገልግሎት ሲሰጥ በተመሳሳይ ጉዳይ ሌሎች የሕክማና ባለሙያዎች ሊያከብሯቸው ወይም ሊፈጽሟቸው የሚገባውን መደበኛ ጥንቃቄ (“standard of care”) ሊያከናውን ወይም ሊከተል ባለመቻሉ ምክንያት በታማሚው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያው ለጥፋቱ ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር የሕክምና ስህተት ሕግ ይባላል፡፡

1.1 የህክምና ስህተት ተፈጽሟል የሚባለዉ ምን ምን ሲሟላ ነዉ?

  1. ሐኪሙ ለታካሚዉ ሕክምና የመስጠት ግዴታ አለመወጣቱ፤
    አንድ የህክምና ባለሙያ ለአንድ ታካሚ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ግዴታ ያለበት መሆኑን ወይም ሕክምናዉን የሰጠዉ እርሱ መሆኑን በማረጋገጥ የህክምና ስህተት ተፈጥሯል የሚለዉን ጉዳይ ለመወሰን ከሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ነዉ፡፡ ይህ የሚሆነዉ የአካሚና ታካሚ ሕጋዊ ግንኙነት መኖሩ ሲረጋገጥ ነዉ፡፡

አንድ የህክምና ባለሙያ የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እስከተሰማራና የህክምና ተግባራትን የሚያከናውን እስከሆነ ድረስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት እና በዘርፉ ያሉትን የህክምና አሰራሮች ላይ እውቀትና ክህሎቱን በየጊዜው መገንባት አለበት፡፡ ለዚህም ነው ከሐኪም ቀዳሚ ግዴታዎች መካከል ዋነኛዉ በሚያከናዉነዉ ተግባር ብቁ ባለሙያ ሆኖ መገኘት ነዉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለተገልጋይ የሚሰጠዉ አገልግሎትና እንክብካቤ የዘር፣ የጾታ፣ የሃይማኖት ወዘተ… መድልኦ የሌለበትና ተመሳሳይነት ሊኖረዉ ይገባል፡፡

አንድ ሐኪም ተገቢዉን የሙያ ትጋትና ጥረት በማድረግ ጥንቃቄ የተሞላበት የህክምና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ መሰረት ሐኪሙ በህክምና ሙያዉ ጥበብ ወይም አሰራር መሰረት ማድረግ የሚጠበቅበትን እንዲሁም ከታካሚዉ ጋር በገባዉ የዉል ስምምነት ወይም በሕግ መሰረት የተጣለበትን ግዴታ ሳይወጣ ቀርቶ በታካሚዉ ላይ ጉዳት ካደረሰ እና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ የሕክምና ስህተት ፈጽሟል ለማለት ይቻላል፡፡ አንድ ሐኪም ከህክምና ሙያዉ አሰራርና ጥበብ ዉጭ የሕክምና አገልግሎት መስጠት አለመስጠቱ የሚረጋገጠዉ በተመሳሳይ ሙያ ላይ በተሰማሩ የሕክምና ባለሙያዎች ነዉ፡፡ ስለሆነም አንድ ሐኪም ግዴታዉን አልተወጣም ሊባል የሚችለዉ ከሕክምናዉ አሰራር ጥበብ ዉጭ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በታካሚዉ ላይ ጉዳት ካደረሰ ነዉ፡፡

  1. የመንስኤ (ምክንያት) እና የዉጤት ግንኙነት፤
    አንድ የህክምና ባለሙያ የህክምና ስህተት ፈጽሟል ለማለት እና በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በታካሚዉ ላይ የደረሰዉ የአካል ወይም የህይወት አደጋ የተፈጠረዉ በሐኪሙ ስህተት መሆን ይኖርበታል፡፡ በምክንያቱና በወጤቱ መካከል ግንኙነት አለ የሚባለዉ በነገሮች የታወቀ ወይም የተለመደ ሂደት የሀኪሙ ድርጊት ወጤቱን ለማስገኘት የሚችል ሆኖ ሲገኝ ነዉ፡፡ ይህ አይነቱ መርህ ወንጀልን ለማቋቋም እንደ አንድ መስፈርት የተቀመጠ ሲሆን በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 1 ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ስርአት የቅርብ ምክንያትን እንጂ የሩቅ ምክንያትን አይቀበልም፡፡ በሌላ በኩል ጉዳት ባይደርስም ነገር ግን የህክምና ባለሙያው መከተል ያለበትን የተለመደ ሥርዓት ባለመከተል የፈፀመው ተግባር ካለ የህክምና ስህተት የለም ማለት አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡
  2. ጉዳት መድረስ፤
    ጉዳት ደረሰ የሚባለዉ የህክምና ባለሙያዉ በቸልተኝነት ጉዳቱን ያደረሰ ስለመሆኑ ሲረጋገጥ ሲሆን አንድ ሀኪም ለታካሚዉ የሕክምና አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት ወይም ከዚያ በኋላ በታካሚዉ ላይ ጉዳት አድርሶ እንደሆነ ነዉ፡፡ ጉዳት ማለት ከቀላል የአካል ጉዳት እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችል እና በሀኪሙ ስህተት ምክንያት የተፈፀመ ማለት ነዉ፡፡ ለምሳሌ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በሚሰጥበት ወቅት አንድ ሐኪም ከህክምናዉ አሰራር ዉጭ ሕክምና በማድረግ በታካሚዉ ላይ የሚያደርሰዉን ጉዳት መጥቀስ ይቻላል፡፡
  3. በታካሚው ላይ የደረሰው ጉዳት ወደ ሚታወቅ ሌላ ጉዳት ያጋለጠው መሆንን ማረጋገጥ፣
    ምንም እንኳን የሕክምና ባለሙያው የሕክምና ስህተት ቢፈጽምም ወይም የፈጸመው ድርጊት በተመሳሳይ የሕክምና ባለሙያ መስፈርት ከደረጃ በታች ቢሆንም ስህተት የተፈጸመበት ታማሚ ጉዳት እንደደረሰበት እስካላረጋገጠ ድረስ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ይዞ ለመሔድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ፍርድ ቤቱ የሚሰጠው መፍትሄ በአንድ አጥፊ ምክንያት ጉዳት መድረሱን ማረጋገጥና የደረሰውን ጉዳት የሚክስ ውሳኔ የመስጠት ተግባር በመሆኑ ነው፡፡ ሆኖም በአስተዳደራዊ ጥፋት ረገድ በዲስፕሊን የህክምና ባለሙያውን ሊጠይቅ ይችላል፡፡

ምን ዓይነት ስህተቶች ናቸው የሕክምና ስህተት የሚባሉት ለሚለዉ ስህተቶች የሕክምና ስህተት የሚባሉት በተለያዩ ዘርፍ ውስጥ ሊወድቁ ይችላሉ፡፡

ከእነዚህም መካከል፡-•
 በምርምራ ወቅት ታማሚውን በተገቢዉ ሁኔታ አለመመርመር ወይም የታማሚውን ሁኔታ ለመመርመር መዘግየት፣
 የምርመራ ውጤቶችን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ለምሳሌ የኤክስሬይ ዉጤቶችን አሳስቶ ማንበብ ወይም መረዳት፣
 መድኃኒት ከመስጠት ጋር በተያያዘ ለምሳሌ ትክክል ያልሆነ፣ የተሳሳተ ወይም የሚጋጭ የመድኃኒት ትዕዛዝ መስጠት፣
 አንድ የሕክምና ሥነ ሥርዓት ያለውን ጉዳት ወይም ሥጋት ለታማሚው አለመንገር፣ አለማስረዳት ወይም አለማስጠንቀቅ፣
 ታማሚው ወይም የቅርብ ቤተሰቡ በግልጽ ፈቃዱን ሳይሰጥ በታማሚው ላይ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን መፈጸም፣
 የህክምና ስነ-ስርዓት ወቅት ስህተት መፈፀም ለምሳሌ በቀዶ ጥገና ወቅት ወይም ልጅ በማዋለድ ጊዜ ስህተት መፈፀም እና ሌሎችን ያካትታል፡፡

  1. ሕክምና ተቋማት እና የጤና ባለሙያዎች የአስተዳደርና የፍትሐብሔር ኃላፊነት፤
    2.1 አስተዳደራዊ እርምጃዎች፤
    አስተዳደራዊ እርምጃ ማለት አንድ ሠራተኛ በሚሰራዉ ጥፋት መሰረት በዲስፕሊን የሚጠየቅበት ሥርዓት ማለት ነዉ፡፡ የአስተዳደራዊ እርምጃ ዓላማ ሠራተኛዉ ከፈጸመዉ ጥፋት እንዲታረምና ብቁ ሠራተኛ እንዲሆን ለማስቻል ወይም የማይታረም ሆኖ ሲገኝ ከስራዉ በማሰናበት የሚወሰድ የመፍትሔ እርምጃ ነዉ፡፡ የዲሰፕሊን ጉድለት የፈፀመ ሠራተኛ እንደጥፋቱ ክብደት የቃል ማስጠንቀቂያ፣ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ከስራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ እንዲሁም ከስራ ማሰናበትን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት መንግስት ደረጃዉን ባልጠበቀ የጤና አገልግሎት እንዲሁም ብቃትና የሙያ ሥነ-ምግባር በጎደለዉ የጤና ባለሙያ ምክንያት በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለዉን የጤና ችግር ለመከላከል ይቻል ዘንድ የጤና አገልግሎቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተለያዩ ሕጎችን በማዉጣትና በተግባር ላይ በማዋል የቁጥጥር ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ አዋጅ ቁጥር 1112/2011 በአንቀጽ 48 አግባብ ባለዉ አካል የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ወይም የህክምና ሙያ ሥራ ፈቃድ የተሰጠዉ ማንኛዉንም ሰዉ ጤናን በተመለከተ አዋጆችን፣ ደንቦችን ወይም መመሪያዎችን በመተላለፍ ሲሰራ የተገኘ እንደሆነ የተሰጠዉ የህክምና ምስክር ወረቀት ወይም ፈቃድ ሊታገድ ወይም ሊሰረዝ እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 41 እና 90 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
    አንድ የጤና ባለሙያ የጤና አገልግሎት ለመስጠት አስቀድሞ በሙያው እውቅና ካለው ተቋም የሰለጠነ መሆኑ ተረጋግጦ እና ቃለ መሀላ እንዲፈፅም ይደረጋል፡፡ ይህን ተላልፎ የአሰራር ስርዓቱን ወይም የሥነ-ምግባር መመሪያዎችን ሲጥስ እርምጃ የሚወሰደዉ የጤና ስነ-ምግባር ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የምግብና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በሚያቀርበዉ የዉሰኔ ሀሳብ አማካኝነት ነዉ፡፡

የምግብ የመድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት የጤና ስነ-ምግባር ኮሚቴ የሚቋቋመዉ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አማካኝነት ሲሆን የስራ ድርሻዉም የሚቀርቡለትን ጉዳዮች አጣርቶ ጥፋት በፈፀሙ የጤና ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለባለስልጣኑ መስሪያ ቤት የዉሰኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ነዉ፡፡
የጤና ሙያ ሰነ-ምግባር ኮሚቴ አንድ የጤና ባለሙያ ከሕክምና ስነ-ምግባር ዉጪ በመስራት በተገልጋዩ ላይ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ ወይም ጉዳት ባያደርስም የስነ ምግባር መርሆችን ተላልፎ ከተገኘ ጉዳዩን አስመልክቶ ተገቢዉን ማጣራት በማድረግ በባለሙያዉ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡ ከእነዚህ ዉስጥም የሙያ ፈቃድ ማገድ ወይም እንደ ጥፈቱ ክብደት የሙያ ፈቃድ መሰረዝ፣ የገንዘብ ቅጣት መጣል፣ ከደረጃ ዝቅ ማድረግ፣ የቃል ወይም የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት፣ የደመወዝ ቅጣት መጣል እንዲሁም ሌሎች እርምጃዎችን ሊያካትት ይችላል፡፡

2.2 የጤና ባለሙያዎች የፍትሐብሔር ኃላፊነት፣
ማንኛዉም የጤና ባለሙያ ከምንም ነገር በላይ ለታካሚዉ ጤንነት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባዋል፡፡ የጤና ባለሙያዉ በሚሰጠዉ አገልግሎትም ሆነ በሚወስነዉ ወሳኔ ምክንያት ለሚከሰት ስህተት ወይም ጉዳት በሕግ አግባብ ተጠያቂነት አለበት፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ የህክምና ሙያዉ በሚፈቅደዉ መልኩ ታካሚዉን ማገልገል ይጠበቅበታል፡፡
የፍትሐብሔር ኃላፊነት ሲባል አንድ የጤና ባለሙያ ከተገልጋዩ ወይም ከታካሚው ጋር በሚያደርገዉ የዉል ስምምነት የሚፈጠር ወይም ከዉል ዉጪ በሆነ እና በሕግ በተደነገገ ጊዜ የሚመነጪ ኃላፊነት ነዉ፡፡ ይህ ዓይነት ኃላፊነት አጥፊዉ በገንዘብ ወይም ዋጋ ባለዉ ዕቃ ወይም ንብረት የሚቀጣበት ሥርዓት ነዉ፡፡ አንድ ሐኪም የሕክምናዉ ጥበብ ከሚፈቅደዉ ዉጪ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት በተገልጋይ ላይ ጉዳት ካደረሰ እንደነገሩ ሁኔታ ማለትም ከዉል ዉጪ ወይም ከዉል በሚመነጭ ኃላፊነት ጉዳት የደረሰበትን ተገልጋይ የመካስ ነዉ፡፡
3.3 የሕክምና ተቋማት የፍትሐብሔር ኃላፊነት፤
የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎቻቸዉ ለታካሚዎች የሕክምና አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት በታከሚዉ ላይ አካላዊ ብሎም ለሞት የሚዳርግ ጉዳት ሊያደርሱ ይቻላሉ፡፡ በዚህ ወቅት የሕክምና ተቋማት ለሚደርሰዉ ጉዳት ከህክምና በለሙያው ጋር በአንድነት በፍትሐብሔር ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከላይ እንዳየነዉ የፍትሐብሔር ኃላፊነት ስንል አንድ ሰዉ በዉል ወይም ከዉል ዉጪ ከሚመነጭ የሚኖርበት ኃላፊነትን የሚመለከት ሲሆን የሕክምና ተቋማትም ከታካሚዎቻቸዉ ጋር በሚያደርጉት የዉል ስምምነት ወይም ከዉል ዉጪ በሚያደርሱት ጉዳት የፍትሐብሔር ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡

3.3.1 የመንግስት የጤና የሕክምና ተቋማት ኃላፊነት፣
የመንግስት የጤና የሕክምና ተቋማት ሠራተኞቻቸዉ በተቋሙ ዉስጥ የሕክምና አገልግሎት በሚያገኙ ታካሚዎች ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ከዉል ወጪ ኃላፊነት አለባቸዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2126 መሰረት የመንግስት ሹም ወይም ሠራተኛ በራሱ ጥፋት በሌላ ሰዉ ላይ ጉዳት የደረሰ እንደሆነ በማናቸዉም ምክንያት ቢሆን ኪሳራዉን ለመክፈል ይገደዳል፡፡ ነገር ግን የተደረገዉ ጥፋት የመንግስቱን ስራ ሲሰራ የደረሰ የስራ ጥፋት የሆነ እንደሆነ የተጎዳዉ ሰዉ ኪሳራ ከመንግስት ላይ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ሠራተኛዉ ያደረገዉ ጥፋት የግል ጥፋቱ የሆነ እንደሆነ ግን መንግስት ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2127 የሥራ ጥፋት ምን ማለት እንደሆነ ያስቀመጠ ሲሆን ጥፋቱ እንደ ሥራ ጥፋት ሆኖ የሚቆጠረዉ ጥፋት አድራጊዉ በዚሁ ጥፋት ላይ የወደቀዉ በቅን ልቦና በስልጣኑና በሥራዉ ክፍል መልካም ያደረገ መስሎት የፈፀመ ሲሆን ነዉ፡፡ በቅን ልቦና ያልተሰራ ለመሆኑ ተቃራኒ ማስረጃ ያልቀረበ እንደሆነ የሹሙ ወይም የሰራዉ አሰራር በቅን ልቦና እንደተሰራ ይገመታል በማለት አስቀምጧል፡፡ በአንድ የመንግስት የጤና የሕክምና ተቋም ተቀጥሮ የሚሰራ የሕክምና ባለሙያ በተቋሙ ዉስጥ ሆኖ ታካሚዎችን በሚያክምበት ወቅት ጥፋት ከፈፀመ ኃላፊ ሊሆን የሚገባዉ የህክምና ተቋሙ ነዉ፡፡

ይኸዉም ጥፋቱ የተፈፀመዉ ከላይ በተገለፀዉ መሰረት በቅን ልቦና በስልጣኑና ለስራዉ ክፍል መልካም ያደረገ መስሎት የተፈፀመ ሲሆን ነዉ፡፡ የሕክምና ጥፋት ተፈጽሟል አልተፈጸመም የሚለዉን ጉዳይ አጣርቶ ትክክለኛ መረጃ ለፍርድ ቤት ወይም አግባብ ላለዉ አካል ሊሰጥ የሚችለዉ በሙያዉ በቂ ዕዉቀት፣ልምድ እና ክህሎት ያለዉ ባለሙያ መሆን ይገባዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ጥፋቱ የሐኪሙ ወይም የሰራተኛዉ ከሆነ የጤና የሕክምና ተቋሙ ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ ታካሚዉ ከተቋሙ የጉዳት ካሳ ተቀብሎ ከከሆነም መንግስት ጥፋት ከፈፀመዉ ሐኪም ወይም ሠራተኛ ላይ ለመጠየቅ መብት ይኖረዋል (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2126(2)፡፡የመንግስት የሕክምና ተቋማት ስለ ሠራተኞቻቸዉ ያለባቸዉ ኃላፊነት የሚመሰረተዉ ተቋሙ ከሠራተኛዉ ጋር የሥራ ቅጥር ዉል ስምምነት ፈጽሞ ከሆነብቻ መሆኑን ከላይ የተጠቀሱት የሕግ ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡ ነገርግን በሕክምና ተቋሙ የሥራ ቅጥር ዉል ሳይፈጽሙ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች የሚኖሩበት አጋጣሚ ስለሚኖር እነዚህ ሠራተኞች ( የሕክምና ባለሙያዎች) በታካሚዎች ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት እራሳቸዉ ተጠያቂ ናቸዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2134 መሰረት አንድ ሰዉ የተጠየቀዉን ሥራ በሚሰራበት ጊዜ ለሥራዉ ጥፋት ጥፋተኛዉ በሥራ ሰጪዉ ሥልጣን ስር ያልሆነ እንደሆነ ነፃነቱንም እንደያዘ መሆኑ ከታወቀ አሰሪዉ በኃላፊነት እንደማይጠየቅ አስቀምጧል፡፡ ስለሆነም በዚህ ወቅት ለሚደርሰዉ ጉዳት ኃላፊነት የሚወስደዉ በራሱ ሥልጣን የሚሰራዉ ሠራተኛ / Indepenent Contactor / ይሆናል፡፡ በራሱ ስልጣን የሚሰራዉ ሠራተኛ በታካሚዉ ላይ ለሚያደርሰዉ ጉዳት የሚጠየቀዉ በራስ ጥፋት በሌላሰዉ መብትና ጥቅም ላይ የሚደርስ ጉዳት (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027(1) እና 2031 (1) በሚለዉ ሕግ ነዉ፡፡

3.3.2 የግል የሕክምና ተቋማት ኃላፊነት፣
የሕግ ሰዉነት የተሰጣቸዉ የግል የጤና የሕክምና ተቋማት ሠራተኞች በታካሚ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ልክ እንደ መንግስት የጤና የሕክምና ተቋማት ሁሉ በፍትሐብሔር ተጠያቂ ናቸዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2129 መሰረት የሰዉነት መብት የተሰጣቸዉ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸዉ፣እንደራሴዎች፣ ወኪሎች ወ.ዘ.ተ የተሰጣቸዉን ስራ በሚያከናዉኑበት ጊዜ ኃላፊነትን የሚያስከትል ስራ የፈፀሙ እንደሆነ የፍትሐብሔር ኃላፊነት ያለባቸዉ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ አንድ የሕክምና ሠራተኛ ስራዉን በሚሰራበት ጊዜ ኃላፊነትን የሚያስከትል ጥፋት የሰራ እንደሆነ በፍትሐብሔር በኃላፊነት የሚጠየቀዉ አሰሪዉ ሲሆን ይህም የሚሆነዉ ጥፋቱ የደረሰዉ በመስራት ወይም ባለመስራት ሆኖ ስራን በመስራት ተፈፅሞ የሆነ እንደሆነ ነዉ፡፡ በመስራት ወይም ባለመስራት የደረሰዉ ጥፋት ሥልጣን በመተላለፍ ሆኖ ሰሪዉ እንዳይሰራ በግልጽ ተከልክሎ ቢገኝ እንኳ ጉዳት የደረሰበት ሰዉ ምክንያቱን ካላወቀ ወይም ሊዉቀዉ ይገባዉ ነበር የሚል ካልሆነ በስተቀር በፍትሐብሔር ኃላፊነት የሚጠየቀዉን ክልከላዉ ምክንያት ሆኖ ከኃላፊነት አያድነዉም (የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2131 (1) እና (2) ይመለከቷል፡፡ ስለሆነም የግል የጤና የሕክምና ተቋማት ከላይ በተገለጸዉ አግባብ ሠራተኞቻቸዉ በታካሚዎች ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ከዉል ወጪ ኃላፊ ይሆናሉ ማለት ነዉ፡፡ የተቋሙ የቅጥር ሠራተኞች ያልሆኑ ብዙ የጤና ባለሙያዎች በአንድ የጤና ተቋም ዉስጥ በተለይ ደግሞ በግል የጤና ተቋማት ዉስጥ የሕክምና አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ አለ፡፡ ለትርፍ ተቋቋሙ የግል የጤና ተቋማት አንዳንድ የሕክምና አገልግሎቶችን ለተገልጋዩ ኅብረተሰብ የሚሰጡት በራሱ ስልጣን በሚሰራ ሠራተኛ አማካኝነት ነዉ፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰጡ የሕክምና አገልግሎቶች በቂ የሕክምና ባለሙያና የሕክምና መሣሪያ በሀገሪቱ ዉስጥ በሌለባቸዉ ሲሆን ለአብነት ያህልም የፊዚዮትራፒስት፣ የራዲዮሎጂስት እና የኒሮሎጂስት ባለሙያዎች የሚሰጧቸዉን የሕክምና አገልግሎቶች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ወቅት በግላቸዉ የሕክምና አገልግሎት በተቋሙ የሚሰጡ ሠራተኞች በታካሚዉ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት የጤና ተቋሙ የፍትሐብሔር ኃላፊነት የለበትም፡፡ ምክንያቱም በሠራተኛዉ እና በጤና ተቋሙ መካከል የስራ ዉል ወይም የቅጥር ዉል ስምምነት የሌለ በመሆኑ ነዉ፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2134 መሰረት አንደሰዉ የተጠቀሰዉን ሥራ በሚሰራበት ጊዜ ለሰራዉ ጥፋት ጥፋተኛዉ በስራ ሰጪዉ ሥልጣን ስር ያልሆነ እንደሆነ ነፃነቱንም እንደያዘ መሆኑ ከታወቀ አሠሪዉ በኃላፊነት አይጠየቅም በማለት ይደነግጋል፡፡ ይህ አንቀጽ የሚደነግገዉ ስለ / Indepenent Contactors / በራሱ ሥልጣን ስለሚሰራ ሠራተኛ ሲሆን የጤና ተቋማት በዚሁ ሠራተኛ ጥፋት ምክንያት በተቋሙ ዉስጥ የሕክምና አገልግሎት በሚያገኙ ተገልጋዮች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ኃላፊነት አይኖርባቸዉም ፡፡ የጤና ተቋማት በራሱ ሥልጣን በሚሰራ ሠራተኛ በጤና ተቋሙ ተገልጋዮች ላይ ለሚደርስ ጉዳት የጤና ተቋማት ከዉል ዉጪ ኃላፊነት የለባቸዉም ሲባል ጉዳት የደረሰባቸዉ ተገልጋዮች የሕግ መፍትሔ የላቸዉም ማለት እንዳል ሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡.ምክንያቱም ጉዳቱ የደረሰባቸዉ የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ጉዳቱ የደረሰባቸዉ በራሱ ስልጣን በሚሰራ ሠራተኛ ከሆነ የጤና ተቋማቱን መጠየቅ የማይችሉ ቢሆንም አገልግሎቱን የሰጠዉን ሠራተኛ ግን በፍትሐብሔርም ሆነ በወንጀል ከመጠየቅ የሚከለክል ሕግ የሌለ በመሆኑ ነዉ፡፡ ይኸዉም በራሱ ሥልጣን በሚሰራ የሕክምና ባለሙያ በታካሚዉ ላይ ለሚደርሰዉ ጉዳት ከታካሚዉ ጋር የዉል ስምምነት ያለዉ ከሆነ በዉሉ መሰረት ተጠያቂ የሚሆን ሲሆን በሁለቱ መካከል የዉል ስምምነት ከሌለ ደግሞ ከዉል ዉጪ ኃላፊነት በራስ ጥፋት በሌላ ሰዉ መብትና ጥቅም ላይ የሚደርስ ጉዳት በሚለዉ የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2031(1) መሰረት ኃላፊ ይሆናል፡፡

Via attorney general

Exit mobile version