ETHIO12.COM

“ዝናብ አትገድቡ ተብለን በቀረብንበት መድረክ ‘ድል ተገኘ ‘ ብሎ መፈንጠዝ ነገሩ እንዳልገባን አመላካች ነው”

ባጭሩ ዶክተር ስለሺ ያሉት እናንተ ፍረደ ገምድሎች፣ ማፈር የማታውቁ፣ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንድንኖር የምትፈርዱ፣ ይህ ሁሉ ሳያንሳችሁ በማይገባን መድረክ ገተራችሁን፣ ሲሆን ግብጽ በበኩሏ ለምኜ ለምኜ የመጨረሻው ቦታ አድርሻለሁና ቀታዩን እርምጃዬን ህጋዊ አድርጉልኝ የሚል የትዕቢት ጥግ ነው ያሳየችው። ድሉ ምኑ ነው? በማይገባን ቦታ መዋላችን? ወጥመዱን መስበር ያስደንቃል። ግን ወጥመዱን ከመስበር በላይ ተኪዶ ማሰብ እነጂ ከሺ ወጥመድ አንዱ ተሰበረ ብሎ ማበድ ልክ አይድለም

ሱዳን እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ትመሰላለች። አቀራረቧም የተሸጠች ስለመሆኗ ያሳብቃል። የግብጹ የመስኖ ሚኒስትር ግን ጉንጩን የሞላው ትዕቢትና እያዞረ የሚናገረው ነገር ከፈንጠዝያ ይልቅ ” ዘብ እንቁም” የሚያሰኝ ነው።

በስብሰባው የተገኘው የመጨረሻ ውጤት ኢትዮጵያን የሚጠቅም ተብሎ እስክስታ መውረድ አግባብ አይመስለኝም። ዶክተር ስለሺ “እዚህ ምክር ቤት ተገኝቶ ያስረዳ የመጀመርያው የውሀ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም፤ ጉዳዩ ወደዚህ ምክር ቤት መምጣቱ በራሱ አግባብ አይደለም::ምክንያቱም እየገነባን ያለነው የውሀ ግድብ እንጂ የኒውክሊየር ማብላያ አይደለም፤” ሲሉ ነገሩን የገለጹት ሰዎቹ ሁሉ ኒኩሌር ማብላያ እንደማንሰራ እንደማያውቁ አስበው ሳይሆን፣ ጉዳዩ እዛ የደረሰበትን አንደምታ ለማንሳትና በውስጠ ብሂል ” እኛም አውቀናል” ለማለት ነው።

የድንቁ የኢትዮጵያ ልጅ የዶክተር የተጨመቁ አሳቦች

ግብጽ ተወካይዋን ወደ ኒውዮርክ ስትልክ ከቀን በፊት ለሱዳን ተወንጫፊ ሮኬቶች ወደ ካርቱም አከታትላ ልካ ነው። ይህ ከመሆኑ ሁለት ቀን በፊት ” ሳምሪ ” የሚባሉትና ማይካድራ ንጹሃንን አርደው ወደ ሱዳን የኮበለሉት ወንጀለኞችና ሚሊሻዎች በጥቅሉ 30 ሺህ የሚሆኑ ግብጽ ያስታጠቀቻቸው ” ታማኝ” ወታደሮች ከትህነግ ጋር ለመቀላቀል በወልቃይት በኩል ከውስጥ የሚከፈተውን ጥቃት እየጠበቁ እንደሆነ ተነግሯል። ይህ ብቻ አይደለም የግብጽ መኮንኖች ካርቱም ገብተዋል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ምንድን ነው?

ግብጽ የጸጥታው ምክር ቤት ይህን ጉዳይ እንደማያየው ጠንቅቃ ታውቃለች። ግን ሶስት ጊዜ የጎተተችን ለምን ይሆን? እስከ ሚገባኝ ” መክሬ ዘክሬ እምቢ ተብያለሁ፣ እስከ ጸጥታው ምክር ቤት ድረስ ደርሼ እርቅን ለምኛለሁና ልከፍት ያሰብኩትን ጦርነት ዓለም ድጋፍ ይስጥልን” የሚል ማስረጃ ለማሰባሰብ ነው።

የመስኖ ሚኒስትሩ ” በዲፕሎማሲና በድርድ እናምናለን” ካሉ በሁዋላ በመድረክ አዟዙረው የገለጹትን የብሪታቸውን ልክ ” ኢትዮጵያ ድርድሩን ገፍታለች የመጨረሻ እርምጃችሁ ምን ይሆናል” ሲል የአገራቸው ሚዲያ ለጠየቃቸው የመለሱት ህልማቸውን ፍንትወ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

የዲፕሎማሲ ኮተታቸውን ካሰሙ በሁዋላ ” … ካልሆነ የህልውና ጉዳይ ነው። አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን” ሲሉ የአገራቸውን ሕዝብ ሕልውና እንደሚታደጉ በግልጽ ተናግረዋል። ይህን ዓለም ዓቀፍ ዛቻ ነው ” አሸነፍን ” እያልን የምንዘፍነው።

ሲጀመር ” ዝናብ አትገድቡ” ተብለን እዛ መድረሳችን ምን ያህል ዓለም በበደል ዱላ እየቀተቀተን እንደሆነ የሚያሳይ ነው። “ለምን ግድብ ሰራችሁ” ዜጎቻችንን ለግርድና እንኳን አትበቁም እያሉ በጅምላ ለሚያግዙት እባጮች ዶከተር ስለሺ ያስተላለፉት መልዕክት ፍትህ በጎደለባት ዓለም መኖርን የሚፈታተን፣ ልብን የሚያም፣ መቼ ነው ተባብረን ከዚህ መከራ የምንወጣው በሚል ለመነሳት እልህ የሚያስቋጥር እንጂ ደረት አስገልብጦ ቃላት የሚያወራውር ባልሆነ ነበር።

” እናንት በጨለማ ስትጨናበሱ ኑሩ” ተብለን በእኛው ውሃ ችግራቸውን ባራገፉ የእስራኤል አለቅላቂዎች ሲፈረድብን ነገራችንን ሁሉ እርግፍ አድርገን ከድህነት የመውጫውን መንገድ የሚጢኝ ለማለት በውሰን ነበር። በተቃራኒው እየሆነ ያለው በልዩ የድል ስሜት መዝለል መሆኑ በግል ብዙም የሚያስኬድ አይመስልም።

ኢትዮጵያ ላይ የሚሆነው የመጨረሻው ድራማ በገባቸው ተቀጣሪዎቻቸውና መጨረሻው ሳይገባቸው ተቀጣሪዎቹ ገዝተዋቸው አገር የሚያምሱትን ” እረፉ” ብሎ ለአገር ዘብ የሚቆምበት ወቅት እንደሆነ ይሰማኛል። ወገኖቻችን እንደሸቀጥ ከሳዑዲ በራችን ላይ ሲደፉ ብሄር ተለይቶ ወይም ዘራቸው ተቆጥሮ አይደለምና ይህ የማያንገበግባችሁ፣ እልህ ውስጥ የማይከታችሁ ረጋ በሉና አስቡ።

ዶክተር ስለሺ ያቀረቡት ንግግር ዓለም የፍትህ ሚዛኗን ኢትዮጵያ ላይ ባታዞር ኖሮ አዳራሹ ምንኛ በእንባ በታጠበ ነበር። እንደ ጆን ባይደን ኢትዮጵያ ላይ በውክልና ለአረመኔዎቹ ታዛዥ ባይሆኑ ኖሮ ችጋራቸውን በራሳችን ውሃ ያራገፉት ባልደነፉብን ነበር። ዶክተር ስለሺ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ማዕረግ ላቀረቡት ሪፖርት ክብር ይሁንላቸው። ለረዷቸውና ላገዟቸውም እንደዛው። ከዚህ በዘለለ እሳቸው ” ይህን አሉ” እያልን ጥቅስ በመጠቀስ አጉል መገልፈጥና መዝለል ዋጋ የለውም። ሌል ስለሺን መሆን እንጂ!! የምክር ቤቱን ስብሰባ ጥሩ አድርጎ የዘገበው ኢዜአን ከታች ያንብቡ።

ከጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ መልስ …

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ እየተካሄደ ያለው የሶስትዮሽ ድርድር መቋጫ እንዳያገኝ ግብጽና ሱዳን የተለያየ ምክንያት በመፍጠር እያደናቀፉት ይገኛል። ጉዳዩን በአደራዳሪነት እየመራ ያለውን የአፍሪካ ህብረትን በመናቅ ወደ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጸጥታ ምክር ቤት እስከመውሰድ ደርሰዋል። ትናንት በዚሁ ጉዳይ ላይ የመከረው የጸጥታው ምክር ቤት “እኔጋ የሚደርስ አይደለምና የአፍሪካ ህብረት ይመልከተው” የሚል አቋም በመያዝ ድርድሩን ለአፍሪካ ህብረት ትቶታል።

በጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያን ሃሳብ በመድረኩ ተገኝተው ያቀረቡት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከውሳኔው በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል። የጋዜጣዊ መግለጫ መድረክ ያስተዋወቁት በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከውስጥ በሚፈልቅ የደስታ ሳቅ ታጅበው “እንደሚሰማኝ የአረብኛ መገናኛ ብዙሃን በከፍተኛ ደረጃ በዚህ መግለጫ ላይ ፍላጎት ይኖራችኋል” ብለዋል። እዚህ አብራችሁን በመገኘታችሁ በድጋሚ አመሰግናለሁ፤ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ማብራሪያ ይሰጣሉ” ብለው መድረኩን ከመልቀቃቸው በፊት እውነትን ስለመናገር አጽንኦት ሰጥተዋል።

በተለይም በቋሚነት የግብጽና የሱዳን እንደራሴ የሚመስል ዝንባሌ ያላቸው ጋዜጠኞች ጥያቄያቸውን በስነ ስርዓትና በጥንቃቄ እንዲሰነዝሩና የሚጠቀሙበት ቃላት ተገቢ እንዲሆን ምክር በመለገስ ጭምር መድረኩን ለክቡር ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ሰጥተዋል።

መድረኩን የያዙት ሚኒስትሩ በመግለጫው ለታደሙ ጋዜጠኞች ምስጋና አቅርበው አንዳንድ ጉዳዮችን በማንሳት በኋላ ላይ ለጥያቄና መልስ ጊዜ እንዳላቸው በመግለጽ ማብራሪያ አቅርበዋል።

“ለምክር ቤቱ (የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት) እንደተናገርኩት ምናልባትም እኔ የመጀመርያው የውሃ ሚኒስትር ሳልሆን አልቀርም የውሃን ጉዳይ (የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብን) በተመለከተ ማብራርያ በመስጠት፡፡ ይህም ያልተገባና ያልተለመደ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደምታምነው መድረኩ በግድቡ ላይ ለመወያየት መጠራቱ የምክር ቤቱን ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ አስረድተናል፡፡

“ስለግድቡ የተወያየንባቸውን ጉዳዮች ላስታውሳችሁ እና የኑክሌር ማብላያ አይደለም የምንገነባው፡፡ ይህ ደግሞ የመጀመርያ ጉዳይ ነው፡፡ በአፍሪካ ሆነ በአለም በኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ ዙሪያ አለም እጅግ ብዙ ልምዶች አሉት እና የምንገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት የሚያስችል ውሃ የሚይዝ ግድብ ነው፡፡ ውሃው ተርባይኖቹን መትቶ ኤሌክትሪክ ካመነጨ በኋላ ውሃው ወደታችኛው ተፋሰስ አገሮች መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡

“በርግጥ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመርያው የህዝብ ፕሮጀክት ነው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን ግድብ ለመገንባት እና የኤሌክትሪክ ብርሃን ለማየት አዋጥተዋል፡፡ 65 ሚሊዮን ህዝብ በጭለማ ውስጥ ይኖራል፡፡ ናይል የሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ቢሆንም በተፋሰሱ አገሮች ያሉት ግማሽ ቢሊዮን ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ኢትዮጵያ በየአመቱ 77 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ታመነጫለች፡፡ በርግጥ 85 በመቶ የሚሆነው የናይል ውሃ ከኢትዮጵያ ነው የሚመነጨው፡፡ በዚህ ልክ ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ ግብፅና ሱዳን መልካም ትመኛለች፡፡ አብረን በትብብር በመቀጠል የሰላምና የጋራ ተጠቃሚነት ፍላጎት አለን፡፡ ግድቡ ይህንን መርህ የሚከተል ለቀጠናዊ ትብብር መጠናከር ውሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ 77 ከመቶ ህዝብ ከ30 አመት በታች ነው፡፡ ከ100 ሺህ በላይ ህዝብ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋም ይመረቃል፤ 30 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ፡፡ ይህ ህዝብ ያለውን ፍላጎት ማሟላት ለኢትዮጵያ አስገዳጅ ሁኔታ ነው፡፡

በመጨረሻም ኢትዮጵያ ስምምነት ላይ በመድረስ ታምናለች፡፡ ድርድሩም በመልካም ሁኔታ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ትሰራለች፤ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ደርሰናል፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ ህብረት በድርድር ውጤት ለማምጣት ትክክለኛው አካል በመሆኑ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ድርድሩን ያስቀጥላል በማለት ንግግራቸውን በዚሁ ቀጠሉና መድረኩን ለጥያቄ ክፍት አደረጉ፡፡

አምባሳደር ታዬ በመድረኩ መግቢያ ላይ ጥርጣሬያቸውን በመግለፅ የአረብኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙሃን ልዩ ፍላጎታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

የመጀመርያውን እድል ያገኘው የስካይ ኒውስ አረብያ ጋዜጠኛ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ በጥያቄው የግብፅና ሱዳንን ፍላጎት ማንፀባረቁ አልቀረም፡፡ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ “የሶስቱን አገሮች የሚያስደስት መፍትሄ የሚመነጨው ተደራዳሪ አካላት ለመፍትሄው ስንሰራ እንደሆነ ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማምጣት እየሰራን እንገኛለን፡፡ በፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፤ ስምምነት ላይ ለመድረስ እንሰራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጡ፡፡

ቀጣዩ ጋዜጠኛ በተመሳሳይ የሱዳንና የግብፅን የተለመደ ክስ በማንፀባረቅ ኢትዮጵያ ለመወንጀል የሞከረ ጥያቄውን ሰነዘረ፡፡ ሚኒስትሩ በተለመደ የተረጋጋ መንፈስ ኢትዮጵያ ሁሌም ለድርድርና ለመፍትሄ ጥረት የምታደርግ መሆኗን አመላክተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉንም ነገር በጠረጴዛ ዙርያ ለመፍታት የምታደርገውን ጥረት እነማን እያደናቀፉ እንደሆነ በግልፅ ቋንቋ አስረድተዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ የድርድር መድረኮች ግብፅና ሱዳን ሂደቱን ማደናቀፋቸው እና ኢትዮጵያ ደግሞ አንድም መድረክ ያለማደናቀፏን አብራርተዋል፡፡

“መፍትሄው በእጃችን እንደሆነ አሳይተናል ነገር ግን ተደራዳሪዎቹ ይንን አይፈልጉም” ብለዋል፡፡


በዚህ አጋታሚ የዩቲዩብ ገጼን ላይክና ሰብስክራይብ ታደርጉ ዘነዳ አደራ እላለሁ

ቀጣዩ ጠያቂ ደግሞ ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌሎች ግድቦች ስለመገንባትዋ አንስቷል፡፡ ጭራሽ ጉዳዩን ከሉአላዊነት ጋር በማያያዝ የኢትዮጵያ የልማት አጀንዳ ተቃውሞውን በይፋ አውጥቶታል፡፡

ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ “ኢትዮጵያ የመጪ ጊዜ ፍላጎት አላት፤ የወቅቱ ፍላጎት አላት፡፡ የወቅቱ ፍላጎቷ እንደሚታወቀው 65 ሚሊዮን ህዝብ ከኤሌክትሪክ ሃይል ወጪ ነው፡፡ ወደታችኛው ተፋሰስ አገሮች ስንሄድ ደግሞ 100 በመቶ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ደግሞ አንዱ መፍትሄ ነው፡፡ የመጠጥ ውሃ የወሰድን እንደሆነ 25 ሚሊዮን ህዝብ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ተጠቃሚ አይደለም፡፡ ስለዚህ ውሃ መጠጣት አለብን፡፡ የምግብ ምርት ዋስትናችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ወደሌላ የአለም ክፍል እየተሰደድን ልንቀጥል አንችልም፡፡ በቂ ምርት ማምረት አለብን፣ ውሃ ማቅረብ አለብን፣ ኤሌክትሪክ ሃይል ማቅረብና የስራ እድል መፍጠር አለብን” ሲሉ አስደማሚ ምልሽ ሰጥተዋል፡፡

የአልጀዚራው ጋዜጠኛ በበኩሉ የግድቡ የውሃ ሙሌትን በተመለከተ ጠየቀ፡፡ የሙሌቱ ነገር እንዲዘገይ ስለሚደረግበት ሁኔታ፤ በፈገግታ ጥያቄውን ያደመጡት ሚኒስትሩ አጥጋቢ መልስ እንደሚሰጡ ከሁኔታቸው ያስታውቃል፡፡

“ይህንን ጥያቄ በማንሳትህ በእውነቱ አመሰግናለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት በናይል ተፋሰስ ላይ የሚገኙ ሁሉም ግድቦች ተሞልተዋል፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የዝናብ ነው፡፡ ሐምሌ፣ ነሃሴና መስከረም የዝናብ ወቅትና ውሃ የሚገኝበት ነው፡፡ ጎርፍ ሁሉ የሚከሰትበት ጊዜ ነው፡፡ ግድቡ ደግሞ ሊከሰት ከሚችለው ጎርፍ የሚጠብቅ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከኢትዮጵያ አንፃር ስናየው እኛ 77 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለናይል እናዋጣለን፡፡ 13 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ግድቡን የገነባነው በአፍሪካ ጎልቶ የሚታይ ጌጥ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ውሃ እንዲሞላበትና እንድንጠቀምበት ነው፡፡ ስለዚህ ሙሌቱ ምክንያታዊ ነው፡፡ በግድቡ ሁኔታ ላይ መመካከርና ወደ ውሳኔ መድረስ እንደሚገባ እናምናለን፡፡ በተለይም በድርቅ ወቅት ላይ” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች በበዛ ድርቅ እንዳይጎዱ በግድቡ በሚያዘው ውሃ በትብብር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። ግድቡ ማንንም ሊጎዳ እንደማይችልም አረጋግጠዋል፡፡

ቀጣይ ጋዜጠኛ ደግሞ ሌሎች አገሮች ድጋፍ በማድረግ ረገድ ፍላጎታቸውን ቢያሳዩ ኢትዮጵያ እንዴት ታስተናግዳለች የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡

ሚኒስትሩ “ምንም ችግር የለብንም፡፡ ማንኛውም አካል ከመፍትሄ ጋር ከመጣ እንቀበላለን፡፡ በግልም ሆነ በቡድን ለድጋፍ የሚመጣ አጋራችንን እንቀበላለን፡፡ ሰላማዊ አማራጭን ለመቀበል ዝግጁ ነን፡፡ አለም በግድብ ግንባታ የዳበረ ልምድ አለው፡፡ በአውሮፓ በሺዎች የሚቆጠሩ ግድቦች አሉ፣ አሜሪካ፣ አፍሪካ የሚገርም ልምድ አላቸው፡፡ አፍሪካ የተፋሰስ ልማት ላይ ጥሩ ተሞክሮ አለ፡፡ የኒጀርና የሊምፖፖ የዛምቤዚ ልምድ አለ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተሞክሮ ቀምረን በሰላም መቀጠል የሚቻልበትን ሁኔታእንፈጥራለን” ሲሉ አስደማሚና አጥጋቢ ምላሽ ሰጥተዋል።

የመጨረሻ ጠያቂ ጋዜጠኛ ግብጽና ሱዳን ድርድሩ በጸጥታው ምክር ቤት መሆን አለበት የሚል አቋም ቢይዙ መፍትሄው ምንድነው ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄም አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

“የጸጥታው ምክር ቤት ለድርድሩ ተገቢ ቦታ አይደለም” የሚል፤ “ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ይህ ጉዳይ ለምክር ቤቱ የቀረበ የመጀመሪያው የውሃ ልማት ጉዳይ ነው” ብለዋል።


Exit mobile version