Site icon ETHIO12.COM

“የትህነግ ርዝራዦች ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስ በቁጭት ተነሳስተናል”አቶ ደስታ ሌዳሞ

የአሸባሪው ትህነግ ርዝራዦችና ደጋፊዎች በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያን ለማዋረድና ሰላሟን ለማናጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስና ለመመከት ተነሳስተናል ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ለሀገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ለተሰናዳው ለሲዳማ ክልል ልዩ ኀይል አባላት ትናንት ማምሻውን በሀዋሳ ከተማ የሽኝት ሥነ ስርዓት ተካሂዷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ እንዳሉት ትህነግ ዜጎች በተባበረ ክንድ ከስልጣን ቢያስወግዱትም ተመልሶ ለመምጣት በሚያደርገው ጥረት ሀገሪቱን እየተፈታተናት ይገኛል።

“አሸባሪ ቡድኑ የመንግሥትን የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ በንጹሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት በማያዳግም ሁኔታ ማስቆም ያስፈልጋል” ብለዋል።

“በተለይ ቡድኑ የኢትዮጵያን ከፍታ ከማይወዱና ሀብቷን በእጅ አዙር ከሚጠቀሙ ከጎረቤትና ኃያላን ሀገራት ጋር በመተባበር እያደረሰ ያለውን ፈተናና መዳፈር ሁሉም ዜጋ በቁጭትና በጋራ ለመቀልበስና ለመመከት ልንነሳሳ ይገባል” ብለዋል።

በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በጋራ በመመከት እና አንድነታችንን በማፅናት የሕዝባችንን ክብር ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

“የሀገሪቱን ዳር ድንበር ለማስጠበቅና ለማስከበር የሲዳማ ልዩ ኀይል ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር ለመሰለፍ ቁርጠኛ አቋምና ወኔ በመሰነቅ ተነሳስቷል” ብለዋል።

ርእሰ መስተዳድሩ ለልዩ ኀይሉ ባስተላለፉት መልእክት “የጥንት አባቶቻችንን ፈለግ በመከተል በፍጹም ጀግንነትና በልበ ሙሉነት በድል እንደምትመለሱ በመተማመን በክብር ሸኝተናችኋል” ብለዋል።

“የክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ከጎናችሁ ነው” ሲሉም አረጋግጠዋል።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል ወቅቱ ለሚፈልገው ሀገራዊ ተልዕኮ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።

በተለይ የሲዳማ ሕዝብ ለ27 ዓመታት ሲጨቁነው ከነበረው ትህነግ አገዛዝ ተላቆ የራሱን ክልል በመሰረተበት ማግስት በሀገራችን ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት ልዩ ኃይሉ መነሳሳቱ የሀገር አለኝታነቱን እንደሚያስመሰክር ተናግረዋል።

“የጁንታው ቅጥረኛ የሆኑ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀን አፍራሽ ሚና ሲጫወቱ እያየን እንገኛለን” ያሉት ኃላፊው “ቅጥረኞችን ለማሳፈርና የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበር ልዩ ኃይሉ የበኩሉን ዋጋ እንደሚከፍል በግልጽ አሳይቷል” ሲሉም ተናግረዋል።

ለግዳጅ የተሰማራው ልዩ ኃይል አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ቦጋለ ገላልቻ ልዩ ኃይሉ ተልዕኮውን ለመወጣት ከነ ሙሉ ትጥቁ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ግዳጁንም በዲሲፕሊን፣ በደስታና በሞራል ለመፈጸም ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል።

ከልዩ ኃይል አባላት መካከል ምክትል ሣጂን ማንአለብሽ ሁሴን ሀገራዊ ጥሪውን በደስታ መቀበሏን ገልጻ ግዳጇንም ጠላትን በማንበርከክ በጀግንነት ለመወጣት ጉጉት እንዳደረበት ተናግራለች።

እሷን ጨምሮ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ሀገራዊ ጥሪውን በታላቅ ወኔና ደስታ ተቀብለው ለመዝመት ያላቸው መነሳሳት ከፍተኛ መሆኑንም መግለጿን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version