ETHIO12.COM

ግደይ እናመሰግናለ! አትሌቲክስ በልዩ ታክስ ፎርስ ይመርመር

ግድይ የኢትዮጵያ ልጅ ነሽ። ትግራይ የሰጠችን ምርጥ ነሽ። ባንዲራሽን እንደምትረግጪና ባደባባይ እንደምታረክሺ ” እንግዴዎች” ሲያወሩ ነበር። በልመና በሚኖሩበት ምድር ተሰብስበው “ኢትዮጵያ ትፈርሳለች። እናፈርሳታለን” ሲሉ፣ አንቺ ግን ዓለም እያየ፣ ሕዝብ እያየ ባንዲራሽን ከፍ አድርገሻል። ይህ ለኢትዮጵያ ከወርቅ በላይ ነው። አንቺ ራስሽ ወርቃሽን ነሽ። እናመስግናለን። ገና ከፊትሽ ብዙ ድል አለሽ። ገና ታበሪያለሽ። ገና ስምሽ ከፍ ያላል። በዚህ ሙቀት እንድትሮጪበት የተመረጠልሽ ዘዴ ቢያሳፍረንም፣ ባንቺ ታላቅ ድል ኮርተናል። እናመሰግናለን!!

ሲፋን በኖርዌይ ቲቪ በቀጥታ በሰጠችው ቃለ ምልልስ እንዲህ አለች። “የመጨረሻውን ሁለት መቶ ሜትር ምን እንደሆነ አላውቀውም ነበር። ሲያልቅ ስቼ ነበር። እንዲህ ዓይነት ውድድር በህይወቴ አድርጌ አላውቅም” ይህን ስንሰማ ግደይ የተነገራት የስህተት ምክር ያስቆጫል። ሲፋን የመጨረሻውን ዙር እንዴት እንደሮጠች እንደማታውቅ ተናግራለች። እናም ግደይ አቅሟን ሰብስባ አራት ዙር ሲቀር አክርራ ጀምራ ልክ ዶክተር ወልደ መስቀል እንደሚያደርጉት 800 ወይም 400 ሜትር ላይ ብትወጣ ሲፋን ከ200 ሜትር በላይ ልትከተላት አትችልም ነበር። ምክንያቱም በተደጋጋሚ ውድድር ስለደከመች። በውድድሩ እንደታየው ግደይ ጉልበት ጨርሳ መጨረሻ ላይ መጨመር አለመቻሏ ነው ወርቅ ያሳጣት። ሌላው ደግሞ ተመሳሳይ አቅም ያለው ወገን ተወዳዳሪ አልተዘጋጀላትም።

Sifan Hassan has two medals, one race left in Olympic treble bid
ሲፋንን የዘመኑ ምትሃተኛ አትሌት ናት

ሲፋን ሃሰን ተርብ ናት። ብልጥ ናት። አትቀመስም። ጥሩ አሰልጣኝ እንዳላት ጥርጥር የለውም። “አትሌቲክስ የቡድን ስራ ነው” እያሉ ለሚያታልሉን የቁጩ ባለሙያዎች መልስ ናት። በሶስት ወድድር ሜዳሊያ ያገነች የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጀግና ናት። አዳማ የተወለደችው ሲፋን 28 ዓመቷ ነው። ላለፉት አስራ ዓምስት ዓመታት ሆላንዳዊ ሆና ኖራለች። አክርታቸዋለች። እየመረረንም ቢሆን ብቃቷን ከማድነቅና የገፏትን ቀመኞች ከመርገም ውጪ ሌላ አማራጭ የለም። ጀዝመኛ፣ እንደፌሮ የከረረች ጅማታም፣ የዘመኑ ምታተኛ ሯጭ ናት።

ቃል ኪዳን ገዛኸኝ ተወልዳ ያደገቸው አዲስ አበባ ሲሆን 30 ዓመቷ ነው። ለባህሬን ነው የምትሮጠው። በትክክል ምክንያቱ ባይታወቅም ተገፍታ ስለመገፋቷ ጥርጥር የለም። የግደይን የከረረ አሯሯጥ ተቋቁማ፣ ሲፋንን በመከተል ውድድሩን በሁለተኛነት ጨርሳለች። ምርጥ ብቃት አሳይታለች።

ግደይ ለተሰንበት 23 ዓመቷ ነው። ምርጥ አቋምና ችሎታ ያላት አትሌት ናት። ግደይ ስህተት ተመክራ ወደ ውድድር መግባቷ ጎድቷታል። ብቻዋን እንደመራች አክርራ እንድትጨርስ የመክሯት አሰልጣኞ ወራዶች ናቸው። ግደይ ውድድሩን እንደ ኮረንቲ አግላ ጨዋታውን በሙሉ አበላሽታዋለች። ያቋረጠች አትሌት ውድድሩ እየተደረገ በኖርዌይ ቴሌቪዥን “ምን ነካሽ?” ስትባል። ” ልጅቷ እየበረረች ነው” አይነት ይዘት ያለው መልስ ነው የመለሰችው።

25 ዙር ያለውን የአስር ሺህ ሜትር ሩጫ፣ እንደ ሲፋን አይነት ኢንዱራንስ ያላት ሯጭ ባለችበት ሜዳ ላይ 20 ዙር በመምራት እንድትጨርስ መምከር እብደት ነው። ግደይ ይህን ውድድር ወርቅ አግኝታ ማሸነፍ ትችል ነበር።

“ስሜን ተወው” ያለኝ ታዋቂ አትሌት፣ ልክ ስደውልለት ” ደግሞ ምን ፈለክ” አለና ” የእብድ ምክር መክረው የልጅቷን ሩጫ አበላሹባት። ሲፋን ተደራራቢ ሩጫ ስለሮጠች ዙሩን አክርሪባት ተብላ ነው። ስህተት ነው። ግደይ አቅሟን አደራጅታ አራት ዙር ሲቀረው ብትወጣ ሁሉም ነገር ይቀየር ነበር” ሲል ማዘኑንን አጫውቶናል። በርካታ ጥቆማ ስጥቶናል። ለቀጣይ የአሰልጣኞች ስልጠና መመርመር አለበት። አትሌቶችን መስማትም ያስፈለጋል። በፈለጉት አሰልጣኝ እንዲሰለጥኑ ሊፈቀድ እንደሚገባ የጠቆመንን ለጊዜው ማንሳት ግድ ነው።

አብዛኞቹ አስለጣኞች እንግሊዘኛ አይችሉም። “ኬንያ ሄደን የከፍተኛ ደረጃ አስለጣኝነት ዲፕሎማ አገኘን ” እያሉ አትሌቲክሱን እያቦኩት ነው። እንግሊዘኛ የማይችል ሰው በምን ተምሮ ብቃቱን ገነባ? ተብሎ አይጠየቅም። ስራ አስፈጻሚው የሚመራው በሩጮች መሆኑ ከአስተዳደር መርህ ጋር የሚተዋወቁ አልሆኑም። ሌሎቹም ነጋዴዎች ወይም ስለ ሩጫ የሚያውቁ አይደሉም። ተቀጣሪ የሚባሉትም ለከርሳቸው ሲሉ ስራ አይሰሩም። በጥቅሉ መቆጣጠርም አልተቻለም።

ዱቤ ጅሎ ያበሰበሰና የገደለው ቤት ዛሬ አትሌት ሳይጠፋ በአሰራር ችግር እዚህ ደርሷል። በአትሌቶች የግል ችሎታ ላይ እየተንጠለተሉ ራሳቸውን “ልዩ አሰለጣኝ” ያደረጉ ሃይ ሊባሉ ይገባል። በአንድ ወቅት ሻምበል ቶሎሳ “የቀነኒሳ ልዩ አስለጣኝ ነኝ” እያሉ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ ” ከቀነኒሳ ጋር አንድ መደብ ላይ ሲተኛ የነበረ፣ ከአንድ ላም የሚታለብ ወተት ሲጠጣ የነበረ፣ እኩል የገብስ እንጀራ ሲመገብ ያደገ፣ አንድ አይነት ውሃ ሲጠጣ የጎለመሰ፣ በኪሎ፣ በቁመት፣ በጥንካሬ ተመሳሳይ የሆነውን የናቱን ልጅ ታሪኩን ለምን ውጤታማ አላደረጉትም? ስልጠናው ሳይንስ እስከሆነ ለምን ብዙ ቀነኒሳዎች አልተፈጠሩም” በሚል ሲጠየቁ ” ይህ ዘመቻ ነው። የነ ዶክተር ወልደ መስቀል ክስ ነው” የሚል ቅጥ የሌለው መልስ መስጥታቸው አይዘነጋም።

የቶኪዮ ኦሊምፒክ ብዙ ነግሮናል። ከተራ የግለሰቦች ውዝግብና ከኈቱም ወገን የተገዙ ጋዜጣኞች እንደሚለቀልቁት ሳይሆን፣ መንግስት ገለልተኛ ታክስ ፎርስ አቋቁምና አስጠና። እንደ ዱቤ ጅሎ ያለ የስፖርት መሪ ፍጹም አቅም አልባ ካድሬ ነውና አባር። ብቃት ያላቸው የተማሩ ሰዎች በሜሪት ስፖርቱን ይምሩት። “ስለ ሮጥን መሪ ነን” የሚለው አዲሱ አባዜም ይጠና። ኦሊምፒክ ኮሚቴም ቢሆን እንደሚወራው ባይሆንም ችግር አለበትና ይቆንጠጥ። አገርና ክብርን በማይነካ መልኩ ይገሰጽ። በዚህ ዙሪያ በስፋት ዘገባ ይኖረናል።

ቃል ኪዳን በአገሯ መለያ እንዲህ ነበር ስትቀዝፍ የነበረው

Exit mobile version