Site icon ETHIO12.COM

ሃውጃኖ፡ የራያው መብረቅ

በዚያ አስፈሪ ዘመን፣ እነዚያ አስጨናቂ የፖለቲካና የሴራ ጉንጉኖች ወቅት ሁሉም በቆፈን ታሥሮ፣ በፍርሃት ተወድሮ በስስ ልቡ ውስጥ ተደብቆ ነበር፡፡ የትውልድ ስብራት እና የኢትዮጵያዊነት መደብዘዝ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በተረጨው የጥላቻና የመገዳደል የፖለቲካ ሸማ ሽምን ውጤት፤ ቅይጥ ርዕዮት፡፡

ሕወሐት ሰሜን-ምዕራብ አማራ፣ ወልቃይትን እና ሰሜን-ምሥራቅ አማራ ራያን በልቡ አልሞ፣ በዘረፋ መዳፎቹ ለማጋበስ አቆብቁቦ ቆሞ ይሠራ ነበር፡፡ በተለይ የአማራን ሕዝብ በጡንቻ በመግዛት፣ የሕዝቡን መሬትም በመቀማት ግዛት ማስፋት ግቡ ነበርና ራያን አሰፈሰፈበት፤ ጥላውንም ጣለ፡፡

ግና የአማራ ማሕጸን በየአዝማናቱ አይነትፍ-አይመክንምና የራያው መብረቅ ይርጋ አበበ ወይም በትግል ሥሙ ሀውጃኖ ትሕነግን የእግር እሳት ሆነበት፡፡

በኢትዮጵያዊነቱም አይደራደርም፣ ላመነበት ሟች፣ ታግሎ አታጋይ፣ ተኩሶ መራዥ፣ ቆራጡ ሀውጃኖ አላማጣ-ራያ ተወልዶ ደርግን ለመጣል በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል በወቅቱ ወደተመሠረተው የሕወሐት ጥፍጥፍ ድርጅት ኢህዴን ተቀላቅሎ ይንቀሳቀስ ጀመር፡፡

የኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልም እስከመሆን ቢደርስምሪው የትህነግ ሐገር አፍራሽ ቡድን የሚያራምደውን ድብቅ ሴራ ፈጥኖ የተረዳው በመረዳቱ አጥብቆ መቃወም ጀመረ፡፡

ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰው፣ አማራዊ ማንነቱን እና የማንነቱ መብቀያ ርሻ የሆነውን ርስቱን አላስነካም ያለው የጀግናው ሀውጃኖ አካሄድ ያልተዋጠላቸው የትህነግ ቡድኖች ሀውጃኖን በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉት ጀመር፡፡ ሊያሳምኑትም ሞከሩ፤ከአቋሙ ንቅንቅ ሊልላቸው አልቻለም፡፡

በሀውጃኖ ፅኑ አቋም ያልተደሰቱት የትህነግ አባላት ከኢህዴን ማዕከላዊ ከሚቴ አባልነት እንዲታገድ አደረጉት፡፡ ከነበረው ከፍተኛ ወታደራዊ ኃላፊነትም አሳነሱት፡፡ በዚህ ማናለብኝነታቸው ሀሳቡን ሊቀይርላቸው፣ ከቆመበት የሀቅ ኮረብታ፣ የማንነት የዕውነት አምባ ፈቅ ሊል አልቻለም፡፡ እንዲያውም የህወሐትን ጉምቱ ባለሥልጣናትና የደሕንነት ሠዎች ፊት ለፊት ቀርቦ ‹‹ግንኙነታችን የድርጅት ከሆነ እኩል መሆን አለብን›› ይላቸው ነበር።

አስቀድመው የፈሩትና የተሸፈነውን አካሄዳቸውን ፈልፍሎ ያወቀ በመሆኑ ሟቹ መለስ ዜናዊ እና የዛሬው የፖለቲካ ማማሰያ አቀባይ ታምራት ላይኔ ሀገረሠላም ድረስ አስጠርተው ሊያሳምኑት ሞክረው የማይቆረጠም የብረት ቆሎ ሆኖባቸው ጥርስ ነከሱበት።

አካሄዳቸው የጋራ የሆነች ታላቅ ሀገር ለመምራት እንደማያስችልም በተደጋጋሚ ነገራቸው። ቢችሉ በመንገዳቸው እንዲሄድ ካልሆነ ግን ከመንገዳቸው ላይ እንዳይቆም ለማድረግ ወሰኑ። አማራጭ ሲያጡ ሊያስሩት ሞከሩ፤ ስለ አውነት አልታሰር አለ። በነበረው የተኩስ ልውውጥም ሀውጃኖ ተገደለ።

የራያ አማራ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖር ማድረግ፤ በፈለገው ጊዜ የሚታሰር፤ የሚገረፍ፤ የሚፈናቀል ሕዝብ እንደነበር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በተደጋጋሚ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ለምን ብሎ የጠየቀ ደግሞ ‹‹አካባቢውን ለቀህ ውጣ! ከመሬቱ እንጂ ከእናንተ ምንም የለንም›› እንደሚባሉም ዶክተር ሲሳይ የሀውጃኖን የትግል ጥያቄዎች አስታውሰው ይገለጻሉ፡፡

ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዳይማሩ ማድረግ ሌላኛው የሕወሓት ሥራ ነበር። የራያ አማሮች በአማርኛ ቋንቋ እንዳይናገሩ፣ እንዳይፅፉና ሌሎችም የመከራ ቀንበር ተጭኗቸውም ብዙ የመከራ ዘመናትን አለፉ። ሕዝቡ ታፍኖ የኖረ፤ ነፃነት የጠማው ሕዝብም እንዲሆን ተገደደ፡፡

ዳሩ የሀውጃኖ እና ዕልፍ የራያ አማራ ታጋዮች መራር ትግል ዳዋ አልለበሰም፣ ንፋስ አልበተነውም፡፡ የራያ አማራ በልጆቹ ትግል ከትህነግ ነጻ ወጥቶ ወደቀደመ ማንነቱ ተመልሷል፡፡ ማንነት አይሸጥምና ከግዞት ተላቆ በራሱ ማንነት ቆሟል፡፡

ይህ ያንገበገበው አሸባሪ ዛሬም እንደትናንት የራያን አማራ ለመጨፍጨፍ፣ ለመጨቆን እና ለመዝረፍ ቢቋምጥም የዛሬዎቹ ጃውሃኖዎች ተሰልፈው ቆመዋል፡፡ ራያን ለዳግም ባርነት ‹‹ ሒሳብ ሊያወራርድ›› የሚያሰላውን ሰላቶ ሊቀብሩት በሀውጃኖ ምህላ አስረዋል፤ ቃልኪዳን ቋጥረዋል፡፡

ሀውጃኖነት በመቃብር ያልተገታ፣ የትውልድ አደራ ውል ነውና ሐውጃኖ መብረቃዊ ኃይል ዛሬም በአላማጣ፣ በቆቦ፣ በወልድያ፣ በአላውኃ፣ በላልይበላ፣ በላስታ፣ በዋግ፣ በአንጎት፣ በመርሳ፣ በውርጌሳ፣ በኃይቅ፣ በሲሪንቃ፣ በአምባሰል፣ በቦረና፣ በመቅደላ በቃሉ፣ በኮምቦልቻ እና በተዋጊዎቹ በመነን ልጆች ልብ ውስጥ አለ፡፡

ቢወለድ ጀግና እንደ ሀው’ጃኖ
ጠላት ይወቃል ከአውድማ ዘግኖ

እየተባለ ትላንት እንደገነነ፣ ዛሬ ተከብሮ ነገን ሕያውነት ለትውልዱ አልብሶ አልፏል፤ ደመላሽነቱ ግን በፍጹም አያልፍም፡፡

Via AMC

Exit mobile version