Site icon ETHIO12.COM

የአሸባሪው ህወሓት አሰቃቂ ግፎች

አቶ ተስፋሁን ብጡል ውልደታቸውም እድገታቸውም ሰሜን ወሎ ወልድያ ከተማ ነው። የሰሜን ወሎ መናገሻ በሆነቸው ወልድያ ክፉውንም ደጉንም አይተዋል። ወልደዋል ከብደዋልም። በከተማዋ ጉባ ላፍቶ ወረዳ በህብረት ሥራ ማህበር የገንዘብ ብድርና ቁጥባ የቡድን ኃላፊ ሆነውም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አገልግለዋል። ከዚሁ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ሲደጉሙ ቆይተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሰሜን ወሎን በተለይ ደግሞ የወልዲያን ከተማን ለመያዝ ባደረገው ትንኮሳ ባደረባቸው ስጋት ባለቤታቸውን፣ የባለቤታቸውን አባት፣ እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸውን ትተው ሕፃናት ልጆቻቸውን ብቻ ይዘው ከሳምንት በፊት ደሴ ገቡ። ሁለት ሕፃን ልጆቻቸውን ይዘውም ደሴ ከሚገኙት እህታቸው ዘንዳ በጊዜያዊነት ተጠለሉ። ሆኖም እረፍት የነሳቸው ጉዳይ ቢኖር ወልድያ ጥለዋቸው የመጡት የቀሪ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ነው።

የመንግሥት ሠራተኛ እንደመሆናቸው መጠን እስካሁን ድረስ የሐምሌ ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸውና አሸባሪ ቡድኑ ተጨማሪ ቦታዎችን እንደሚቆጣጠር ብሎም የመንግሥት አመራሮችንም እንደሚገድል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ የሚያሰወራ በመሆኑ እርሳቸውም ልክ እንደሌላው ዜጋ ከስጋት አልተላቀቁም።

ስጋታቸው እንዲቀረፍ፤ በተለይ ደግሞ የቤተሰባቸውም ሆነ የሰሜን ወሎ ነዋሪ ህልውና እንዲረጋገጥ ደግሞ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ ሆነው ይህን አሸባሪ ቡድን ከያዘባቸው አካባቢዎች ጠራርገው እንዲያስወጡ ድምፃቸውን ያሰማሉ።

ይህ ድምፅ ታዲያ የአቶ ተስፋሁን ብቻ አይደለም። የበርካታ ኢትዮጵያውያን እንጂ። አዎ አሸባሪው ህወሓት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በፈፀማቸው አይረሴ ግፎች በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውም ተጥሷል፤ በዚህች ምድር  ለመኖር ያልተፈቀደላቸውም ለዘላለም አሸልበዋል። ግፍና መከራ የበዛባቸው ደግሞ አገራቸውን ለቀው እስከመሰደድ ደርሰዋል።

አሸባሪው ኃይል በሕዝባዊ እምቢተኝነት ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ተሰናብቶ ወደ መቀሌ ከተሸኘ በኋላ ከዚያም በሰሜን ዕዝ ላይ ታሪካዊ ክህደት ፈፅሞ በመከላከያ ሰራዊት ከተደቆሰ በኋላ ቆላ ተንቤን እስከወረደበት ጊዜ ድረስ በትግራይ ሕዝብና በሌሎችም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ በርካታ መከራዎችን አዝንቧል።

በምዕራብ ወለጋ በተለያዩ አካባቢዎች በአሸባሪው ኦነግ ሸኔ ዘርን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶችና የዜጎች መፈናቀል እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በጉሙዝ ታጣቂዎች በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ ለደረሱ ጥቃቶችና ከቤት ንብረት መፈናቀል የህወሓት ሽብር ቡድኑ የእጅ አዙር ድጋፍ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት አሸባሪ ቡድኑ በማይካድራ የፈፀመው ግፍ በዓለምአቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለ ቢሆንም በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነና የተጎጂ ቤተሰቦችን ቅስም የሰበረ ድርጊት ሆኖ አልፏል። ከዚሁ አስቃቂ ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘም ነፍሳቸውን ያተረፉና ካዳጉበትና ንብረት ካፈሩበት ቀዬ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የተመሙም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

ከስምንት ወር የሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በማድረግ በትግራይ ክልል በተለይ አርሶ አደሩ የክረምቱን ወቅት ተከትሎ እርሻ እንዲያርስ የጥሞና ጊዜ ሰጥቶ መቀሌን ለቆ ቢወጣም አጥፊው የህወሓት ቡድን ስምምነቱን በመጣስ በትግራይ አዋሳኝ በሚገኙ የአማራና አፋር አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር በርካቶች እንዲሞቱና እንዲቆስሉ፤ አብዛኞቹ ደግሞ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። የበርካታ ዜጎች ቤት ንብረትና የእርሻ መሬቶችም በጥቃቱ እንዲወድሙ ሆኗል።

መንግሥት ያስቀመጠውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመጣስ በአሸባሪው ቡድን በቀጠለው በዚሁ ጦርነት በተለይ በመጀመሪያው ሳምንት በአማራ ክልል ከቆቦ ከተማ ዙሪያ ከአላማጣ ወረዳ 829 ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በቀጣናው ግጭቱ እየተስፋፋ በመምጣቱም በዚሁ አካባቢ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። በሰሜን ወሎ ወልዲያም 150 ሺ ሰዎች በጥቃቱ ምክንያት ተፈናቅለዋል። በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ደግሞ 37 ሺ የሚሆኑ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ከሰሞኑም አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ጋሊኮማ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያ ላይ በከፈተው ጥቃት ከ240 በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ አልፏል። ከነዚህ ዜጎች ውስጥ 107ቱ ሕፃናት መሆናቸው ደግሞ የአሸባሪ ቡድኑን የጭካኔ ጥግ አሳይቷል። በዚሁ ክልል በዞን አራት ፋንቲ ረሱ አውራ በሚባለው አምስት ወረዳዎች ላይ 76 ሺ የሚሆኑ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው በአሸባሪው ቡድን ግፍ ተፈናቅለዋል። በአጠቃላይ በሽብር ቡድኑ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 700ሺ ደርሷል።

ይህ ሁሉ የአሸባሪው ቡድን ግፍ ያስመረራቸውና በቃኝ ያሉ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ የተነቃነቁ ኢትዮጵያውያን ታዲያ ከአገር መከላከያ ጎን በመሰለፍ አሸባሪ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ቆርጠው በመነሳታቸው በድል ላይ ድልን በመጎናጸፍ ላይ ይገኛሉ። ድሉ አይቀሬ በመሆኑም አቶ ተስፋሁን ብጡልን የመሳሰሉ ሰዎች በአገራቸው ተረጋግተው የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም

Exit mobile version