ETHIO12.COM

ሃያ አራት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፤ በኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ

ሃያ አራት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ የሰላም ጥሪ አቀረቡ። በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ አካላት፤ ግጭቶችን ያለ ቅደም ሁኔታ እንዲያቆሙ፣ ከግጭት አባባሽ ተግባራት እንዲቆጠቡ እና ለሰላማዊ መፍትሔዎች ራሳቸውን እንዲያስገዙም ጠይቀዋል።

የሰላም ጥሪውን ዛሬ ጷጉሜ 5፤ 2013 ያቀረቡት በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት መዘርጋት እና በግጭት አፈታት እና ሰላም ግንባታ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ናቸው። ድርጅቶቹ ጥሪውን ለማቅረብ የወሰኑት በአስር ምክንያቶች መሆኑን አስታውቀዋል። 

በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች እየተስፋፉ በርካታ አካባቢዎችን እያዳረሱ መሆናቸው ለጥሪው መቅረብ እንደ አንድ ምክንያትነት ተጠቅሷል። ግጭቶቹ የሚያስከትሉት ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎቹ እየተባባሱ፤ ወደ ሀገር ዐቀፍ እና ንዑስ አህጉራዊ ቀውስ ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ስጋትም ሌላኛው ምክንያት ነው።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያስከተለውን ጉዳት መገንዘባቸውን ባቀረቡት የሰላም ጥሪ ላይ አንስተዋል። ግጭቶቹ በኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሕዝብ ለሕዝብ አዳሪ ቂምና ቁርሾ እያፈሩ ሊመጡ የሚችሉ መሆናቸውን መመልከታቸው የሰላም ጥሪውን ለማቅረብ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆናቸው ጠቁመዋል። 

“ግጭቶችን በሰላም ለመፍታት የዕርቅ ባሕላዊና ማኅበራዊ አቅሞቻችንን ለመጠቀም እያደረግን ያለነው ሁለገብ ጥረት እስካሁን ሰላምን ሊያረጋጋጥልን አልቻለም” ያሉት ድርጅቶቹ፤ “በመሆኑም ሕዝባችንን ለዘመናት ደግፈው ያቆዩ ማኅበራዊ እሴቶቻችን ሳይቀሩ አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ለግጭቶቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አዳጋችነቱ እያደር እያሻቀበ በመምጣቱ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ የዳበሩ ከጦርነት ወጪ ግጭቶች የሚፈቱባቸው፣ ከጦርነት በኋላም ዕርቅ፣ ሰላምና ፍትሕ ማምጣት የሚችሉ፣ ረቂቅ ልምዶች ስላሉ፤ ለእነዚህ የሰላም እሴቶችና ተሞክሮዎች የፖለቲካ ልኂቃኑ ዕድል እንዲሰጡ፣ ሰላምን መገንባት የሚያስችል ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያመቻቹ” በሚል የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን ድርጅቶቹ አብራርተዋል። 

ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ፤ በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ አካላት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነውጠኛ ግጭቶች፣ ከግጭት አባባሽ ሁኔታዎች እና ከጦርነት ፕሮፓጋንዳዎች በመቆጠብ ለሰላማዊ ንግግሮች ራሳቸውን እንዲያስገዙም” ጠይቀዋል። በአንድ ጥላ ስር በመሰባሰብ የዛሬውን የሰላም ጥሪ ካቀረቡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ ሴታዊት ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት እና የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር ይገኙበታል።

 በሃሚድ አወል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

Exit mobile version