Site icon ETHIO12.COM

በኢትዮጵያ የዴልታ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው -ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ

በኢትዮጵያ የዴልታ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ተናገሩ። ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በተለይ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት በቫይረሱ የሚያዙ፣ በፅኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎችን ቁጥርም እንዲያሻቅብ ማድረጉን ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዲኤታው ከትናንት ምሽቱ የዜና መፅሄት ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ ፣ ለዴልታ የኮሮና በቫይረስ ስርጭት መስፋፋት፣ የመከላከልና የጥንቃቄው ስራ መቀዛቀዝ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ህዝባዊ መሰባሰቦች መብዛታቸውና የህብረተሰቡ በሚፈለገው መጠን ክትባት አለመከተብም ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ነው ያሉት።

በትናንትናው እለት ብቻ 38 ሰዎችን በቫይረሱ ህይወታቸውን ሲያጡ ከ750 በላይ ሰዎች ደግሞ በፅኑ  መታመማቸውም ነው የተገለጸው። ከዚያም ባለፈ በ7 ቀናት ውስጥ 182 ሰዎች በማእከላት ውስጥ መሞታቸው ነው የተነገረው። የጥንቃቄው መዘናጋት በዚሁ ከቀጠለ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም ነው ሚኒስትር ዲኤታው የተናገሩት።

የሚፈራው ጉዳት እንዳያጋጥምም ህብረተስቡ ራሱን ከቫይረሱ ለመጠበቅ መወሰንና መተግበር ይገባዋል ፣ ክትባቱንም ሊወስድ ያስፈልጋል ነው ያሉት። የህግ አካላትም ለመመሪያው ተፈፃሚነት ክትትልና ቁጥጥር ሊያደርጉና ተቋማትም ለመመሪያው መተግበር የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በኮቪድ-19 ሳቢያ ከ156 ሚሊየን በላይ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል-ተመድ

በኮቪድ-19 ምክንያት አሁን ለይ ከ156 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ ) ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ÷ የኮሮና ቫይረሰ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ህጻናትላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አንስቷል፡፡

ሀገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ጋር ተያይዞም ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ለመሆን መገደዳቸው ተመላክቷል፡፡

አሁን ላይም  19 በሚሆኑ ሀገራት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤቶች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ እንዲዘጉ ተደርገዋል ፡፡

ይህን ተከትሎም ከ156 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡

ስለሆነም ሀገራት አስፈላጊውን የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ በማድረግ ትምህርት ቤቶችን ስራ ማስጀመር እንዳለባቸው ድርጅቱ አሳስቧል፡፡

Exit mobile version