ETHIO12.COM

ትግራይ ሥርዓት አልበኝነት የሰፈነባት የስቃይ ማዕከል ሆናለች


ትግራይ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆች ወደ ጦርነት የሚጋዙባትና ሥርዓት አልበኝነት የሰፈነባት የስቃይ ማዕከል ሆናለች ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ የፖለቲካ ጉዳዮች ምክትል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ አለማየሁ ተናገሩ።

አቶ ተስፋዬ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ትግራይ ትምህርት ቤቶችና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እስር ቤት ሆነውባታል።

የኢትዮጵያን መንግስት ይደግፋሉ ተብለው የሚታሰቡ የሚታሰሩበት፣ ለአቅመ አዳምና ሄዋን ያልደረሱ ህፃናት ወደ ጦርነት የሚሰማሩባት የስቃይ ማዕከል መሆኗንም ተናግረዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ቆሞ እንደማያውቅና ቀድሞም የእነሱ አባል አልሆንም ያለን ማንኛውንም ግለሰብ ለደርግ ጥቆማ በመስጠት ያስገደለ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ቡድኑ ለብቻው የሚፈነጭባት፣ የሕዝብ እስር ቤትና የባርነት ቀንበር የተጫነባት ትግራይን መመስረት እንጂ በስልጣን ላይ እያለ ያልደገፈውን ሕዝብ የመደገፍ ዓላማ እንደሌለውም አስረድተዋል።

የቡድኑ አባላት የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ እንደማይደራደር ስለተረዱ ከተቀረው ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ ሊያጣላው ሲጥር እንደነበረም ነው አቶ ተስፋዬ የተናገሩት።

የቡድኑ አባላት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ፍልስፍና ያልነበራቸው የውጭ ሀይሎች ተልዕኮ አስፈፃሚ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

አሸባሪው ቡድን በስልጣን ላይ በነበረ ጊዜ “ግብጾች ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ይፈልጋሉ” ሲል ክስ ሲያቀርብ ቢቆይም አሁን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑን በግብጽ ሚዲያ መግለጹ በምን ያህል ቅዥት ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ከሌሎች ኢትጵያዊ ወንድሞቹ ጋር የመነጠል ድብቅ አጀንዳ ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የገለፁት አቶ ተስፋዬ፤ ቡድኑ በግብጽ ሚዲያ ያነሳው ሃሳብም ይህንኑ እኩይ ዓላማውን ያንፀባረቀበት እንደሆነም ጠቁመዋል። (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version