Site icon ETHIO12.COM

በዚህ መሃል ግን አንድ ነገር ተከሰተ!!

ወ/ሮ አባይነሽ ጫኔ የደባርቅ ከተማ ቀበሌ 01 ነዋሪ ሲሆኑ በዚች ምድር ላይ 40 አመታትን ሲኖሩ ብዙ ችግርና መከራ አሳልፈዋል፡፡

የልጆቻቸው አባት ወታደር መልካሙ ታየ በውትድርና ህይወት ውስጥ በዘመናቸው አገራቸውን አገልግለው አብረው በኖሩባቸው አመታት ሁለት ሴት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን የ14 ዓመቷ የመጀመሪያ ልጃቸው መስታይት መልካሙ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የ 2 አመት ታናሿ ትዕግስት መልካሙ ደግሞ የ5ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡

ከአባታቸው መለየት በኋላ በብዙ ችግሮች መሃል ያለፈው የእነ ወ/ሮ አባይነሽ ጫኔ ቤተሰብ የእለት ጉሮሯቸውን ለመሙላት የድንች ቅቅል በመሸጥ መተዳደር ቢጀምሩም እናትዬው በደምግፊት ህመም ስለሚሰቃዩ በእንቅርት ላይ ሆኖባቸው ኑሮን ይገፋሉ፡፡

የተቀቀለው ድንች ከተሸጠ እሰየው ይላሉ ካልሆነ ግን ተካፍለው እራት ያደርጉታል፡፡ የዛሬ ማታን በልተው ቢያድሩም ቅሉ ነገ ግን ሃሳብ ጭንቃቸው ይሆንና ሌሊቱ በሃሳብ ይነጋል፡፡

ከቤቱ ሁለት ልጆች መካከል ታናሽቱ ተማሪ ትዕግስት መልካሙ በጣም ተግባቢ ብላቴና ስትሆን በልጅነት ባህሪዋም ፍጥንጥን እያለች ወደ ካምፕ እየሄደች የወታደር ደምበኞችን ያፈራች ሲሆን ስለ አባቷ ወታደር መሆን ስለቤተሰቡ ችግር ስለእናታቸው ህመም በተደጋጋሚ ለአዛኝ ወታደሮች ትናገራለች አውርታቸው ልትሄድ ስትልም ብስኩት ይሰጧትና አመስግናቸው ትሄዳለች፡፡

የቤተሰቡ ተደራራቢ ችግር ያሳዘናቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳዩን በተደጋጋሚ እየተነጋገሩበት በአንድ አጋጣሚ ለአመራሮች አደረሱት፡፡

በዚህ መሃል ግን አንድ ነገር ተከሰተ፡፡

በማይጠብሪ ግንባር የህወሓት የሽብር ሃይልን በመፋለም ላይ ለሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊታችንና ሌሎች የግንባሩ ሃይሎችን ለመደገፍ ከደጀኑ ህዝባችን ከተበረከቱ የእርድ ከብቶች መካከል አንዷ ላም ክበድ (እርጉዝ) ሆና ተገኘች፡፡

ላሟ የችግረኛ ቤተሰብ ተመርጦ ብትተላለፍስ ተብሎም ሃሳብ ተነሳ ፤ ተመከረ ተዘከረ ፤ የደባርቅ ከተማ አስተዳደር አመራሮችም የድሃ ድሃ ችግረኛ ቤተሰብ መርጠው እንዲቀርቡ ተነገረ፡፡የተመረጠውም የእነ ወ/ሮ አባይነሽ ጫኔ ችግረኛ ቤተሰብ ሆነ፡፡

እናትዬው ከደባርቅ ከተማ ሴቶች ጋር ሆነው ለመከላከያ ሰራዊታችን ፣ ለአማራ ልዩ ሃይል ፣ ሚሊሻና ፋኖ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ ከነበሩበት የቤቱ ታታሪ ልጅ ታዳጊዋ ትዕግስት ደግሞ የበሰለ ድንች በመሸጥ ላይ ከነበረችበት ሁለቱም ከያሉበት ተጠርተው ከማይጠብሪ ግንባር ሎጅስቲክስ አስተባባሪ ብ/ጄ ሰይድ ትኩየ እና ከሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለአለም ፈንታሁን እጅ ተቀበሉ፡፡ላሟም ለተቸገረው ቤተሰብ ተበረከተች፡፡

“የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ምን መሆን ትፈልጊያለሽ? ተብየ ስጠየቅ ፓይለት መሆን ነው የምፈልግ እልነበር፡፡” የምትለው የቤቱ ታናሽ ተማሪ ትዕግስት መልካሙ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በደባርቅና አካባቢው ለግዳጅ ከተሰማራው የመከላከያ ሰራዊታችን ጋር መቀራረብ የጀመረችው ታዳጊዋ “አሁን ፓይለት የመሆን ሀሳቤን ቀይሬያለሁ ትምህርቴን ስጨርስ ወታደር መሆን እና በቻልኩት ሁሉ ለህዝብ ማገልገልና ወታደሮች ለእኛ እንደረዱን እኔም ለህዝብ መርዳት እፈልጋለሁ፡፡” ትላለች፡፡

ላሚቷን ምን ታደርጊያታለሽ? ተጠየቀች….
“ትወልድልኛለች ከዚያ ወተቷን ከወታደሮች ጋር እንጠጣዋለን” በልጅ አንደበቷ ከልቧ ትናገራለች፡፡

ህዝብ ነው ሃያል ክንዳችን
ሰላም ልማት ነው ቋንቋችን
የማንጨበጥ ነበልባል እሳት ነን ለጠላታችን
ፍሙ ከርቀት ይፋጃል ብረት ያቀልጣል ክንዳችን፡፡

እያለ እዘመረ ህወሓታዊያን የሽብር አዝማቾችን ድባቅ እየመታ ከህዝብ የተበረከተለትን ድጋፍ ለህዝብ የሚደግፍ ህዝባዊ ሰራዊት ይሉታል ይሄ ነው፡፡

“ኢትዮጵያ ታሸንፋለች”

መላክ በቃሉ (ከግዳጅ ቀጣና)
ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ via ENDF Fb

Exit mobile version