ETHIO12.COM

“በእኛ ዘመንም የማናውቀውንና ያልወረስነውን የተበላሸ ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ አናስረክብም!” አቶ ላቀ አያሌው

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በደብረማርቆስ የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ የልዩ ኃይል ፖሊስ ምረቃ ፕሮግራም ላይ ያደረጉት ንግግር

ክቡር ዶክተር ይልቃል ከፋለ፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር፤
ክቡራን የልዩ ልዩ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በየማዕረጋችሁ፤


የተከበራችሁ በሚገጥሙን ችግሮች ሁሉ ፈጥኖ ደራሽ ባለሀብቶች፤
የተከበራችሁ የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደርን ወክላችሁ የተገኛችሁ ነዋሪዎች፤
የተከበራችሁና የተወደዳችሁ በዚህ ቦታ ለመሰባሰባችን ምክንያት የሆናችሁ የዛሬ ተመራቂ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊሶች፤
እንዲሁም የጀግኖቻችንን የምርቃት ፕሮግራም ለመታደም የተገኛችሁ እንግዶች፤
ክቡራትና ክቡራን፦

ከሁሉም በማስቀደም የአገራችንን አንድነት ለማጽናትና የሕዝባችንን ኅልውና በመስእዋትነታችሁ ለማስጠበቅ ወስናችሁ ወደ ደብረ ማርቆስ የፖሊስ ኮሌጅ ተማችሁ ወታደራዊና የፖለቲካ ሥልጠና ወስዳችሁ ዛሬ ለምረቃ የበቃችሁ የኢትዮጵያና የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆች፤ የነገ ባለታሪክ ጀግኖቻችን ፊት ቁሜ መልዕክት እንዳስተላልፍ ዕድል በማግኜቴ ደስታዬ እጥፍ ድርብ መሆኑን እየገለጽሁ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ለማለት እፈልጋለሁ።

ሁላችንም እንደምንገነዘበው በረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ዘመናት አንድነታችንና ሉዓላዊነታችንን የሚፈታተኑ የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች እንደነበሩና እንዳሉ ይታወቃል። ነገር ግን አያትና ቅድመአያቶቻችን በየዘመናቱ ራሳቸውን መስእዋት እያደረጉ ከዓለም አገራት መካከል በቅኝ ያልተገዛችና አንድነቷን የጠበቀች ነፃ አገርና ነፃ ሕዝብ ለትውልድ አስረክበውናል። በየጊዜው ኢትዮጵያ ያፈራቻች የቁርጥ ቀን ልጆች ለውስጥ ከፋፋይ ባንዳና ለውጭ ወራሪ ኃይል የጋራ ጥምረት እጅ ሳይሰጡ መተኪያ የሌለውን ሕይወታቸውን በጀግንነት እየከፈሉ አገር አስቀጥለዋል።

ዛሬም እንደትናንቱ ኢትዮጵያው ውስጥ የበቀለ፤ በኢትዮጵያውያን አንድነት ላይ አደጋ የጣለ፤ የአማራን ሕዝብ ሸቀንደኛ ጠላትነት የፈረጀ፤ ከትግራይ የወጣ ወራሪና ዘራፊ ኃይል የአማራና አፋር ክልሎችን በመውረር ንጹኃንን እየገደለ፥ ኃብትና ንብረቶቻቸውን እየዘረፈና እያወደመ እንዲሁም ሕዝቡን በግዞትና በባርነት በመያዝ ሰቆቃ እየፈፀመ፤ ይባስ ብሎም እንደለመደው ለማሞኜት ጠቤ ከእነገሌ ጋር ነው በማለት በአፈቀላጤዎቹ በኩል ሊነግረን ይሞክራል።

በመሆኑም ይህ ወራሪ ኃይልና የሴራ አባት «ባልበላው ጭሬ ልድፋው» በሚል እብሪት የወረራቸውን የክልላችን አካባቢዎች ሰው የሆነ ሁሉ የማይፈጽመውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት እየፈፀመ በመሆኑ፥ የዛሬ ተመራቂዎች ጀግኖቻችን ለእነዚህ አካባቢዎች መድረስ ተቀዳሚ ተግባራችሁ ነው ብዬ አስባለሁ።

እናንተ የዛሬ ተመራቂ ጀግኖቻችን በዘመኑ ትውልድ ስም የምትወስዱትን የቤት ሥራ የአያት ቅድመአያቶቻችንን መንፈስ በመላበስ የኢትዮጵያን አንድነት ማጽናትና የሕዝባችንን ኅልውና ማስጠበቅን በተገቢው ፍጥነትና ቦታ ፈጽማችሁ በግፍ ወረራ ለግዞትና ጉስቁልና የተዳረገውን ሕዝባችንን ነፃ በማውጣት ወደነበረበት ሰላም መመለስና በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ ለደረሰው የአገራችን አንድነት የዋስትናና አለኝታ ምሽግ እንደምትሆኑ አልጠራጠርም።

ምክንያቱም ተገደን የገባንበት የኅልውና ትግል ፍትኃዊና ምክንያታዊ ብሎም ሕዝባዊ መሰረት ያለው ስለሆነ የሕወኃትን ያረጀ ያፈጀ የከፋፍለህ ግዛ መርኅና ከስሁት ትርክት የሚመነጭ የጥላቻና የልዩነት ግንብ ከስሩ በመናድ የሕዝባችንን ኅልውናና ክብር እንዲሁም የአገራችንን አንድነት ማስጠበቅ ጊዜ የሚሰጠው አይደለም።

በመሆኑም የዛሬ ተመራቂ የአማራ ልዩ ኃይል ፖሊሶች ከሌሎች የፀጥታ መዋቅር ከሕዝባችን ጋር በመቀናጀት ለኢትዮጵያ አንድነትና ለአማራ ሕዝብ ቀንደኛ ጠላት የሆነውን ሕወኃትንና የመንፈስ ወራሽ ግብረ አበሮቹን በመደምሰስና እስከወዲያኛው በመቅበር፥ በመቃብሩም ላይ ለአንድነታችን ካስማ የሚሆን መሰረት በመጣል ለሕዝባችሁ የደስታ ብስራትን፥ ለጠላት ሞትና ውርደትን እንደምታሰሙን ሙሉ እምነት አለኝ።

ለክልላችን ሕዝብ በተለይም ለወጣቱ በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው የሕወኃትን ቆሞ የቀረ የፖለቲካ ማደናገሪያ ጆሮ ባለመስጠት እንዲሁም አንዴ በክልል አመራር በሌላ ጊዜ በፌዴራልና በሌሎች ከማሳበብ ወጥተን የአጀንዳ ቅደመተከተል ስናስቀምጥ ከሕዝባችን ኅልውና የሚቀድም ስለሌለ በዚህ አጀንዳ ላይ አንድ ሆነን ወደ ጠላት መትመም ይኖርብናል።

ምክንያቱም ነፃነትና ክብር የሚገኘው በወሬና በአሉባልታ ወይም ደግሞ እነገሌ ይታገሉልኝ በሚል ሳይሆን ራሱን መስእዋት በማድረግ የሚገኝ ነው። ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ የሚፃፈውም በራሳችን ደም ነው። ለዚህ ደግሞ የቀደሙ እናቶቻችንና አባቶቻችንን ገድል መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል። በመሆኑም ከአሁን በፊት ሥራቸው ኅያው የሆኑትን ጀግኖች በማንሳትና በመፎከር አሁን የመጣብንን የእናት ጡት ነካሽ ወራሪና ከፋፋይ ጠላት ሊመለስ አይችልም።

ስለዚህ ሁሉንም ሰበቦች ለጊዜው ወደጎን በመተው ይህን አገርአፍራሽ ጥቁር ፋሽስት በመረጠው ቋንቋ በማናገር ሕዝባችንን ከሞት፣ ስደት፣ መፈናቀልና ውርደት ለመታደግ እንድ ልብ መካሪ፥ አንድ ቃል ነጋሪ ሆነን በቅድሚያ በሀሳብ መግባባትና መወሰን፤ በመቀጠል መደራጀትና መታጠቅ፤ በሦስተኛም ያለንን ነገር ሁሉ ይዘን ወደ ጠላት መዝመትና ጠላትን መደምሰስ ግድ ይለናል።

ይህ ከሆነ አባቶቻችንና እናቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፥ ደማቸውን አፍስሰው ያቆዩኣትን አገር፤ የሕዝባችንንም ክብርና ከፍታ ዳግም እናድሰዋለን። በእኛ ዘመንም የማናውቀውንና ያልወረስነውን የተበላሸ ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ አናስረክብም፤ መሆንም የለበትም። መፍትሔውም «ሕዝቤ ሆይ፥ አመልህን በጉያህ፥ ስንቅህን በአህያህ ይዘህ ተከተለኝ» ብለው ጠላትን ድል ያደረጉበትን የእምዬ ምኒልክን አባባል ተግባራዊ ማድረግ ነው። ይኼ የክተት ጥሪ የተላለፈውም በጥቅምት እኩሌታ ነበር። ዛሬም ታሪክ ራሱን ደግሟልና፤ ሁላችንም ወደ ወሎ ምድር መዝመት ይኖርብናል።

በመጨረሻም በጀግናው በላይ ዘለቀ የትውልድ ቀዬ የተሰበሰቡትን የዛሬ ተመራቂ ጀግኖቻችን የኢትዮጵያና የአማራ የቁርጥ ቀን ልጆችን በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ፣ በስነልቦናና አካላዊ ብቃት አስታጥቃችሁ ለምረቃ ያበቃችሁ የወታደራዊና የፖለቲካ አሰልጣኞች እንዲሁም የኮሌጁ አመራሮች የጎደለውን ሞልታችሁ ሁሉንም ተግዳሮቶች ተቋቁማችሁ ለአገራችሁና ለሕዝባችሁ መልካም አሻራን አስቀምጣችኋል። በዚህም ልትኮሩ ይገባችኋል። የአጋር አካላትም ያልተቋረጠ ድጋፍ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በመሆኑም ሁላችሁንም በራሴና በክልሉ የሥልጠና አስተባባሪ ኮሚቴ ስም ከልብ የመነጨ አክብሮትና ምስጋና ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።

አመሰግናለሁ!

Exit mobile version