Site icon ETHIO12.COM

“በእርግጥ አሜሪካ ስለአፍሪካ ትጨነቃለችን” ዘ ኒውዮርክ ታይም

በአሜሪካ ብሎም በመላው ዓለም በከፍተኛ ደረጃ ተነባቢነት ያለውበሚል ርዕስ ባሰፈረው ሃተታ የባይደን አስተዳደርን የተሳሳተ የውጭ ፖሊሲ ክፉኛ ተችቷል፡፡

ጽሑፉ በተለይ የባይደን አስተዳደር የአፍሪካን ስነልቦና በቅጡ መረዳት አለመቻሉን የተነተነ ሲሆን በዚህም ምክንያት በአሜሪካና አፍሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው ብሏል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ እንግሊዝን የመሳሰሉ የቀድሞ ቅኝ ገዢ አገራት እቅዳቸውን በአፍሪካ ላይ ለመተግበር የተጠቀሙበት ስልት ለዚያ ዘመን ስኬታማ ያደረጋቸው ቢሆንም ዛሬ ላይ ግን ያ ስልት አገራቱ በአኅጉሪቱ ላይ አለን የሚሉትን ጥቅም ሊያስከብር አለመቻሉንም ጽሑፉ አስምሮበታል፡፡

በተለይ የአሜሪካ የመጫወቻ ካርዶች በቅኝ አገዛዝ ትጠቀማቸው የነበሩ ከመሆናቸውም ባሻገር አሁናዊውን የአፍሪካዊያን ስነልቦና ያለገናዘቡ ናቸው ያለው ይህ ሃተታ፤ እነዚህ ስልቶቿም ዴሞክራሲ እና የሰብኣዊ እርዳታ መሆናቸውን አስቀምጧል፡፡

ይህን ጊዜ ያለፈበት አካሄድ መቀየር አለመቻሏ በአፍሪካ ባለው የመጫወቻ ሜዳ የሚገዳደሯት አገራት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ኳታር ከተገዳዳሪዎቿ መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ለአብነትም ቻይና በማዕድን የበለጸጉ የአፍሪካ አገራት የማዕድን ሃብታቸውን ወደ ገንዘብ እንዲቀይሩ በማገዟ፤ አገራቱ ወታደራዊ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ በማድረጓ እና በዲፕሎማሲ እና በምጣኔሃብት ረገድ ራሳቸውን እንዲችሉ በምታደርገው መጠነ ሰፊ እገዛ ሳቢያ በአኅጉሪቱ ያላት ተፈላጊነት በእጅጉ ጨምሯል፡፡

ሌሎቹም አገራት በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የወታደራዊ ኃይል ማዘዣ ጣቢያ ከመገንባታቸውም ባሻገር በመንገድ፣ ሆስፒታል እና የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎችን ማከናወናቸው እና በሌሎችም ወታደራዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድጋፎች ማድረጋቸው ከአሜሪካ ይልቅ ተመራጮች አድርጓቸዋል፡፡

አዳጊ አገራት ያላቸውን የተፈጥሮ ሃብት በማውጣት ወደ ገንዘብ ሲቀይሩና ከስንዴ እርዳታ ሲላቀቁ ማየቱ ሳይሆን ማሰቡ የሚያጥወለውላት አሜሪካ ግን አገራት በራሳቸው መንገድ እና ጥረት የጀመሩትን የእድገት ጉዞ ለመግታት የማታሴረው የላትም፡፡

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ እና የአሜሪካ ምላሽ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

አዛኝ ቅቤ አንጓቿ አሜሪካ ግን በአንድ በኩል አገራት በራሳቸው ለመቆም የሚደርጉትን ጥረት በማደናቀፍ ስትጠመድ በሌላ በኩል ደግሞ እራሷ የማትተገብረውን የዴሞክራሲ ዲስኩር እና እርዳታ ይዛ ብቅ ትላለች፡፡

የትላንቱ የዘ ኒውዮርክ ታይምስ ትንታኔም ይህ ያረጀ እና ያፈጀ የአሜሪካ አካሄድ ዛሬ ላይ ሊሰራ አለመቻሉን በማንሳት ተችቷል፡፡

የተንሸዋረረው የውጭ ፖሊሲዋ የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን የነባር አጋሮቿን ድጋፍም እያሳጣት ስለመሆኑ ከሰሞኑ የተስተዋሉ ኩነቶች እያመላከቱ ነው፡፡ ሲኤንኤንንን በመሳሰሉ አንደበቶቿ ተቀናብረው በተሰራጩ ሃሰተኛ ዘገባዎቿ እና አዲስ አበባ ተከባለች በሚል ትርክቷ እንዲሁም ዜጎቼ እንዲወጡ የሚል ማስጠንቀቂያ በማስተላለፍ ሽብርን የነዛችው አሜሪካ፤ አገራት ተደናብረው ዜጎቻቸውን እንዲያስወጡ ያደረገችው ጫና እና ጉትጎታ ሊሳካላት አልቻለም፡፡

በተለይ ከልብ ወዳጇ ፈረንሳይ እና ከጀርመን የገጠማት እምቢተኝነት አጋሮቼ ከምትላቸው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየሻከረ ስለመምጣቱ አመላካች ነው፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶኒ ብሊንከንን የኬንያ ቆይታ በተመለከተ ለዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ ከጋዜጠኞች ከበድ ያሉ ጥያቄዎች ተነስተውላቸዋል፡፡

ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ ከአፍጋኒስታን ጋር ለማመሳሰል የሄዱበት አካሄድ በተለይ ከአሶሼትድ ፕረስ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ጸሐፊውና ጋዜጠኛው ማት ሊ ጠንከር ያለ ተቃውሞና ትችት እንዲነሳባቸው አድርጓል፡፡

ጋዜጠኛው አሜሪካ ዜጎቿን ለማስወጣት ምንድነው ያነሳሳት፣ እዚያ ያሉ ዜጎቻችሁ በአደጋ ተከበናል መውጣት አልቻልንም መንግስታችን ይድረስልን የሚል ጥያቄ አቅርበዋል ወይ ሲል ላነሳው ጥያቄ እንዲህ አይነት ጥያቄ እንዳልቀረበ ከመግለጻቸውም ባሻገር ለጋዜጠኛው ጥያቄዎች መልስ መስጠት ተቸግረው እንደነበር ታይቷል፡፡

እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር የአሜሪካ ሴራ ለሁሉም አካላት ግልጽ የወጣ ከመሆኑም በላይ ወዳጆቼ ከምትላቸው አገራት ብቻ ሳይሆን ለእውነት ከቆሙ መገናኛ ብዙኃንም ተቃውሞዎችና ትችቶች እየደረሱባት መሆኑ ነው፡፡

አሜሪካ በባይደን አስተዳደር የገጠማት ፈተና በዚህ ሳያበቃ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራትም “አሜሪካ በቃሽ” የሚል በሚመስል መልኩ አሜሪካን ኃያልነት ለመንጠቅ የሚያስችል የኃይል አሰላለፍ ውስጥ መገባት ጀምረዋል፡፡

አሜሪካ በእንደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ ስትዳክር በአሸባሪው ሕወሓትና ሸኔ መከበቧን ከ15 ቀናት በፊት የተናገሩላት አዲስ አበባ ግን ለነዋሪዎቿ ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካዊያን ዜጎች ሰላም፣ ምቹ እና አስተማማኝ ሆና ይኸው ዛሬም አለች፡፡

ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ ፍፁም ሰላም ናት የሚል ማጠቃለያን አይሰጥም ይልቁንም አሸባሪዎቹ ሕወሓትና ሸኔ ከውጭ አጋሮቻቸው ጋር ሆነው የከፈቱትን ጦርነት ኢትዮጵያ በቅርቡ አሸንፋ ሙሉ ግዛቷን ወደ ሰላማዊ አየር ትመልሳለች ማለታችን ነው፡፡

(ዋልታ) በነስረዲን ኑሩ

Exit mobile version