Site icon ETHIO12.COM

ወረራ በተፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መውደማቸው ተገለጸ

አሸባሪው ሕወሓትና ግብረአበሮቹ ወረራ በፈፀሙባቸው አካባቢዎች ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት መዘረፋቸውንና መውደማቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ አንፃራዊ ሠላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 20 የጤና ተቋማትን በድጋሚ ስራ ማስጀመር የሚያስችል ግብዓት መላኩንም አስታውቋል።

የሽብር ቡድኑ ዓላማ ሕዝብን መጉዳት በመሆኑ እናቶች የሚወልዱባቸውን፣ ሕፃናት የሚታከሙባቸውን የጤና ተቋማት በማውደም ክፋቱን በተግባር አሳይቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አሸባሪ ቡድኑ በጤና ተቋማቱ ላይ ከፍተኛ ዝርፊያ በመፈጸሙና የሕክምና ቁሳቁስ በመውደማቸው በርካታ ዜጎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

በቡድኑ ወረራ ከተፈጸመባቸው የአማራና የአፋር ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በተጨማሪ የጸጥታ ችግር ባለባቸው የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።

በተደረገው ማጣራት በጤና ጣቢያ ደረጃ ብቻ ከ1 ሺሕ በላይ የጤና ተቋማት ተዘርፈዋል፤ ውድመትም ደርሶባቸዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version