Site icon ETHIO12.COM

በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የመመርመርና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ተጠቆመ

የሚኒስትሮች ግብርኃይል በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የመመርመር፣ አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ እና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራ እንደሚሰራ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤትና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች በሰጠው ማብራሪያ ገልጿል፡፡

ግብርኃይሉ ያዘጋጀውን የተጠቃለለ ስትራቴጂና የድርጊት መረኃግብር አጽድቆ ኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የወንጀል ምርመራ የማካሄድና ክስ የመመስረት፣ የስደተኞችና ተፈናቃዮች ጉዳዮችን የማየት፣ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የማጣራት እንዲሁም ሀብት የማሰባሰብ ስራዎችን የሚያስተባብሩ በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመሩ አራት ኮሚቴዎች ስለመዋቀራቸው በማብራሪያው ተጠቅሷል፡፡

የግብርኃይሉን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለማድረስ እንዲያስችልም ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ወቅታዊ መረጃ የማድረስ ሥራም ይሰራል ተብሏል፡፡

የወንጀል ምርመራና የክስ ሂደቱ ዓለም ዐቀፍ በሆኑና ኢትዮጵያ በምትመራባቸው የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ህጎች፣ ከስደተኞችና ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ  የወጡ የሕግ ማዕቀፎችንና መመሪያዎችን አንዲሁም ጾታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የወጡ አዋጆችና ሕግች፣ በሲቪል ማኅበረሰብ የሚፈጸሙና የጦር ወንጀሎችን ባገናዘበ መልኩ የሚመራና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ የሚተገበር ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በስትራቴጂዉና በድርጊት መርኃግብሩ የተካተቱ ጉዳዮች በሚፈለገው መልኩ ተግባራዊ ይሆኑ ዘንድ ሥራዉን ለሚፈጽሙ አካላት የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጥና ድጋፋዊ ክትትል አንደሚደረግም ተጠቅሷል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የመጡ ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎችም መንግስት ምክረ ሀሳቦቹን ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እያሳየ ያለዉን ጥረት አድንቀዋል፡፡

በስትራቴጂውና በድርጊት መርኃግብሩ የተካተቱ ጉዳዮች ተጠያቂነት በተላበሰና ገለልተኛ በሆነ መልኩ እንዲሁም አለም አቀፍ ህግጋትን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እንዲተገበሩ በማሳሰብ አፈጻጸሙንም በቅርበት እንደሚከታሉ መግለጻቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

walta

Exit mobile version