Site icon ETHIO12.COM

“ሚዲያዎች ፊቴን ይሸፍናሉ… እኔ አላፍርም ዓለም ግፋቸውን ይመልከት፣ እነሱ ይፈሩ” የ14 ዓመቷ ታዳጊ

‹‹እኔ የሚያሳፍር ነገር አልሰራሁም አልፈራም። እንዲያውም የእነርሱ ሀጢያት በዓለም ዓደባባይ ይታይላቸው። እኔ የሚያሸማቅቅ ነገር አላደረኩም፡፡ ፈልጌ አድርጌው ቢሆን እውነትም ላፍር ይገባኝ ነበር። ሚዲያዎች ሲቀርፁኝ ፊቴ ለእኔ በማሰብ እንዳይታይ ይፈልጋሉ፡፡ ያለፍላጎቴ እንዲህ ዓይነት ስቃይ ውስጥ የጣሉኝ እነርሱ ይፈሩ፤ ግፋቸውም ይታወቅ እኔ ምንም አይሰማኝም›› ትላለች በአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂዎች ተደፍራ የሰቀቀን ቀናትን እየገፋች ያለችው የ14 ዓመት የሸዋሮቢቷ ታዳጊ፡፡

የ14 ዓመቷ ታዳጊ ሀዊ ሲራጅ (ሥሟ የተቀየረ) በሸዋሮቢት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ አሸባሪው ሕወሓት ከተማዋን ሲወር ከእናቷ እና ከሦስት ዓመት ወንድሟ ጋር ህዳር 10 ቀን 2014 ዓ.ም በሸዋሮቢት አቅራቢያ ወደምትገኝ ቆቦ ወደተባለች የገጠር መንደር ሸሹ፡፡ ነገር ግን ታጣቂዎቹ የከተማዋን ነዋሪ አንነካም፤ ሴቶችና ሕፃናት ከቤታችው አይውጡ እኛ የምንፈልገው መሳሪያ የታጠቀ ሰው ብቻ ነው” በሚል ያስተላላፉት መልዕክት እውነት መስሏቸው ወደቤታቸው መመለሳቸውን ታዳጊዋ ትናገራለች።

ዳሩ ግን ነገሮችን የአሸባሪው ታጣቂዎች ታዳጊ ሴቶች ያሉባቸውን ቤቶች ሲለዩ ቆይተው፤ ህዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም አምስት ሆነው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት የእነሀዊን ቤት በር ሰብረው ገቡ።

ከታጣቂዎቹ መካከል አንደኛው፤ “አንቺን የመሰለ ቆንጆ ትግሬ መሆን አለብሽ ይዘንሽ ነው የምንሄደው›› ሲል አፍጥጦ ተመለከታት። የ14 ዓመቷ ታዳጊ በወቅቱ የሰጠቻቸው መልስ ዝምታን ቢሆንም እየደጋገሙ ይህንኑ ቃል ሲሰነዝሩባት፤ “በእናቴም በአባቴም አማራ፤ በደሜም በወኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ አትወስዱኝም” ስትል እንደመለሰችላቸው ትናገራለች።በምላሿ የተበሳጩት ታጣቂዎቹ ቤቱን ለቀው ሄዱ። ነገር ግን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲሆን አሁንም መሳሪያቸውን እንዳነገቡ ድንገት ቤት ውስጥ ሰተት ብለው ገቡ።

‹‹ተነሺ ተከተይን›› አሏት ታዳጊዋን። ቤት ውስጥ የነበሩት የታዳጊዋ አጎትና እናት “ለምን” ብለው ቢጠይቁም፤ ቢለምኑም የተሰጣቸው ምላሽ ድብደባ ነበር። የቻሉትን ያህል ደብድበው ሲያበቁ ሀዊን ወደሚፈልጉት ቦታ ይዘዋት ሄዱ። በዚያ ውድቅት ሌሊትም የማታውቀው ቤት ውስጥ አስገቧት። ቤቱ ውስጥ ግን ብቻዋን አልነበረችም፤ ልክ እንደርሷ ከየቤቱ ታፍነው የተወሰዱ በርካታ ህፃናትና ታዳጊዎችም ጭምር እንጂ።

ለቀናትም አሸባሪዎቹ በዚያ ቤት ውስጥ ያለ በቂ ምግብ እና ውሃ ሲያሰቃይዋቸው ሰነበቱ። በአንጻሩ እነሱ በዝርፊያ ከከተማ የሚያመጡትን ምግብና መጠጥ እየበሉና እየጠጡ ሲሰክሩ ደጋግመው የሚናገሩት፤ ‹‹አማራ አህያ ነው ሠራንለት፤ የአብይ አሽከሮች ናችሁ እንገላችኋለን፤ እናፈርሳችኋለን፤ ማንም አያድናችሁም›› እንደነበር ታዳጊዋ ትናገራለች።

ለቀናት በዚህ መልክ ሲያሰቃይዋቸው ቆይተው ታጣቂዎቹ ህዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም “አሁን በጦርነቱ እየተሸነፍን ስለሆነ የሚገባሽን ደመወዝ እንክፈልሽ” በሚል ይዘዋት ወደ ውስጥ እንደገቡ የምትናገረው ታዳጊዋ፤ “..ያለምንም አዘኔታ እየተፈራረቁ ደፈሩኝ፤ የሚፈሰው ደሜ ለእነሱ ምንም ነበር፤ አዘኔታ የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፤ የቻሉትን ያህል ማድረግ የሚፈልጉትን ሁሉ አደረጉ…” ስትልም ነው ሰውም አውሬም ሊያደርገው የማይችለውን ጭካኔ ለኢፕድ ዘጋቢዎች የተናገረችው።

‹‹እኔ እንደዚህ በመሆኑ ምንም አይሰማኝም፡፡ እንዲህ ያደረጉኝ አማራ በመሆኔ ነው፡፡ እኔን እንዲህ አድርገው አንገት ማስደፋት አይቻላቸውም። ይህ ነገር ለወገኔ የምከፍለው መስዋዕትነት ከሆነ ምንም አይሰማኝም። እነሱ ግን በጣም ጨካኞች ናቸው። ሰዎች አይደሉም፡፡ ማገናዘብና ማሰብ ቢችሉ ኖሮ የዘጠኝ፤ 10 እና 14 ዓመት ህፃናትን እና የ80 ዓመት አዛውንት እንዴት እንዲህ ያደርጋሉ›› ስትልም ነው የሞራል ከፍታዋን ያሳየችን።

“እኔ በትምህርት ጎበዝ ነኝ ወደፊት መሆን የምፈልገው ዶክተር ነው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ያለምኩትን አሳካለሁ። እነርሱ እንዲህ ስላደረጉኝ ከዓላማዬ ዝንፍ አልልም፡፡ ይህን የሚያደርጉት ዝቅ ብለን እንድንኖርና ሥነ-ልቦናችን እንዲጎዳ ነው፡፡ ተጨቁነን ከእነርሱ በታች ሆነን እንድንኖር ነው፡፡ ይህ ግን አይሳካላቸውም፤ እኛን ማንበርከክ ፈጽሞ አይቻልም” ነው ያለችን ብረቷ የሸዋሮቢቷ ታዳጊ።

ወይዘሮ ጠርሲዳ ያሲን (ሥም የተቀየረ) የታዳጊዋ ቢሊሌ እናት ናቸው፡፡ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ ‹‹እማዬ! በናትሽ አድኚኝ ሊገሉኝ ነው! እማዬ አድኚኝ! አድኚኝ! አድኚኝ! አድኚኝ!›› እያለች ልጄ የሲቃ ድምጽ ስታሰማ ሮጬ ከቤት ወጣሁ፤ እግራቸው ላይ ወድቄ ለመንኩኝ፡፡

እባካችሁ እንጀራ እየጋገርኩ፤ ልብስ እያጠብኩ ያሳደኳት ልጄ ናት፡፡ በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱትን ጋሽዬ እና እትዬ እያልኩ ነው የምኖረው፡፡ በናታችሁ ልጄን አትውሰዱብኝ በ15 ዓመቴ የወለድኳት ናት፡፡ ከእርሷ ውጭ ምንም ቤተሰብ የለኝም፡፡ ልጄም፤ ጓደኛም እህቴም እናቴም እርሷ ናት በናታችሁ›› ብዬ ተማፀንኩ ይላሉ፡፡

በናትህ አትበይኝ ‹‹እኔ ለአማራ አላዝንም፤ ለአንቺ አላዝንም›› ሲል በጫማ ሆዳቸውን ሦስት ጊዜ ረግጦ ከመሬት ዘረራቸው፡፡ ‹‹አንቺም አህያ! መሪሽም አህያ› ብሎ ሰደበኝ፡፡ እንዲህም ለምኜ ልጄንም ማስጣል አልቻልኩም። በዚህ ጊዜ ‹‹አህዮች እናንተ እንጂ የእኔ መሪ ጦር ግንባር ወርዶ ጠላትን እያርበደበደ፤ ጠላት እያረደና እያዋረደ ነው አልኳቸው፡፡›› በዚህ ጊዜ የዱላ ናዳ አወረዱብኝ፤ ደም በደም አደረጉኝ፤ መሬት ላይ እየጎተቱ ቤት ውስጥ አስገብተው ቆልፈውብኝ ሄዱ፡፡

‹‹ልጄን ወሰዷት፡፡ ሦስት ቀን ሙሉ ከተማ ውስጥ እየዞርኩ ፈለኩኝ ልጄን ማግኘት አልቻልኩም ግን በአራተኛ ቀን ተጫውተውባት ለከፋ የጤና እክል አጋልጠዋት አገኘኋት፡፡ አሁን ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ናት፡፡ ልጄ በቂ ሕክምና አላገኘችም፤ በሥነ ልቦናም ተጎድታለች። የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ያግዘኝ ሲሉም›› ይማፀናሉ፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር ከአዲስ ዘመን የተወሰደ


Exit mobile version