“ዘረፉን፣ ጨፈጨፉን … ምንም የለንም”

አዛውንቱ ሙመሀድ  ዋሊሌ በአፋር ክልል የእዋ ወረዳ  አለሌ ሱብላ ከተማ ነዋሪ ናቸው።  የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች በከተማቸው ወረራ የፈጸመው በመንደሩ ያሉ ቤቶችን በከባድ መሰሪያ በመደብደብ እንደነበር ይናገራሉ።

“በእለቱ እኔ ቤት ውስጥ 18  ሆነን እየተጫወትን ነበር። ተኩሱን ስንሰማ ተደናግጠን ወጣን። ለሶስት ቀናትም የፍየል ግብይት በሚካሄድበት ገበያ ቦታ ላይ  ለመቆየት ተገደድን። እንደምንም በሰው ድጋፍ ወደጭፍራ ለመምጣት በቃሁ። መንገድ ላይ ግን እያለሁ ጆሮዩ መስማት አቁሞ ነበር። ቤት አቅራቢያ በወደቀው ከባድ መሳሪያ ጭስ ምክንያት በአፍንጫዬና በአፌ ደም ስተፋ ቆይቸለሁ። እዚህ ጭፍራ ከደረስኩ በኋላ  አራት ግዜ ሀኪም ቤት ሄጄ ታክሜያለሁ” ነው ያሉት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው አዛውንቱ ሙመድ ወለሌ።

አሁን ትንሽ ከተሻለኝ በኋላ ባደረኩት ማጣራት የማወቃቸውና እኔ አካባቢ ከነበሩት ሰዎች መካከል አራት ወጣቶች መገደላቸውን አውቄያለሁ፤ ያሉት አዛውንቱ ተፈናቃይ፤ የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሳይቀር ወጣት የተበለውን እየለዩ ገድለዋቸዋል ነው ያሉት። 

“ሩጦ ካመለጣቸው እንስሳ ውጪ  ሁሉንም እያረዱ በልተዋል፤ በመኪና ጭነውም ወስደዋል።  ከዚህ  በፊትም  ከመንግስት ጋር እየተታኮሱ በነበረበት ወቅት ለግጦች የተሰማሩ ፍየሎችን ሰርገው እየገቡ ሲሰርቁብን ነበር ነበር። አሁን ይባስ ብለው እኛንም አፈናቅለው ፍየሎቻችን ዘርፈው ሄዱ” ብለዋል አዛውንቱ።  

“ትናንት ለማንም የምንተርፍ የነበርን ብዙ ግመሎችና ፍየሎች የነበሩን ዛሬ በእነሱ የተረገመ ስራ ተመጽዋች አድርገውናል። እዚህም ቢሆን እየመጣልን ያለው ድጋፍ በቂ  አይደለም  ቢያንስ የምንበላው ነገር በበቂ ሁኔታ ሊቀርብልን ይገባል። ከጥይት አምልጠን በረሀብ ልንጎዳ አይገባንም ነገ እጣ ፈንታችን ምን እንደሆነ ባናውቅም  ዛረ ግን አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግልን ይገባል” ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እኛ በትግራይ ህዘብ ላይ የፈጸምነው በደል ባለመኖሩና ተጣልተንም ስለማናውቅ  አንዲህ አይነት ነገር ይፈጠራል ብለን አስበን አናውቅም። የሚሉት አዛውንቱ ሙሀመድ፤  አሁንም ሳናስበው  ስለመጡበን እንጂ እኛም ራሳችንን ለመከላከል አናንስም፤ አሁንም ቢሆን ወጣቶችን እየመረቅን ልከናቸዋል  በመጡበት እንደሚመልሷቸው አንጠራጠርም” ብለውናል።

ወጣት ሙሀመድ  ሙውሜ በአፋር ክልል ዞን አራት ኡዋ  ወረዳ   ነዋሪ ነው። እሱም እንደ አዛውንቱ ሁሉ  መኖሮያ ቤቱ በውድቅት ሌሊት ሲወድምበት ነበር ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን ይዞ ሽሽት ወደ ጫካ  የገባው። ሁለቱም ልጆቹ ህጻናት ስለነበሩ ብዙ ይዟቸው መጓዝ ባለመቻሉ  በቅርበት ያገኛት ቁጥቋጦ ውስጥ ተወሽቆ የቀረችውን ሌሊት አሳልፏል።

የአሸባሪው ታጣቂዎች መንደራቸውን ካወደሙ በሁዋላ ፍየሎቻቸውን እየነዱ መውሰዳቸውን ይናገራል። አንዳንድ ቢታዎች ላይ ደግሞ እያረዱ  ከነደዱት ጎጆዎች ደጅፋ  እየጠበሱ ሲበሉ ተመልክቷል።

ከሌሎች የመንደሩ ሰዎች ጋር በመሆን ጭፍራ መግባቱን የሚገልጸው ወጣቱ፤ “በተኛንበት ተጨፍጭፈናል ብዙ ሰው ሞቷል ያልወሰዱት ንብረት የለም  ሰላሳ በላይ ፍየልና ስድስት ግመሎች ነበሩኝ አንድ ላምም ነበረችኝ። አሁን ምንም የለኝም።   የቀረኝ እጄ ያለው  ጎራዴ ብቻ ነው። መንግስት ክላሽ ባይሰጠኝ እንኳን ይህንን ይዤ ገዳዮቻችንን ልገድላቸው እዘምታለሁ” ሲል ነው የነገረን።

በራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም

Leave a Reply