Site icon ETHIO12.COM

ወገን ለወገኑ ደረሰ – ትህነግ ያወደማቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋም 50 ኮንቴነር የህክምና ቁሳቁስ ከካናዳ እየተጓጓዘ ነው

በካናዳ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት የተሳተፉበትና በአሸባሪው ህወሃት ለወደሙ የጤና ተቋማት ድጋፍ የሚውል 50 ኮንቴነር የህክምና ቁሳቁስ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ እንቅስቃሴ መጀመሩን በካናዳ የኢመርጀንሲ ሀኪምና የግሎባል ኤድ ኢትዮጵያ መስራች ዶክተር ጌታቸው ደመም ገለጹ።

ዶክተር ጌታቸው ደመም ከኢዜአ ጋር በበየነ-መረብ ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በካናዳ የሚኖሩ የዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የአገራቸውን ጉዳይ በንቃት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዳያስፖራው አባላት በኢትዮጵያ ያጋጠመውን ወቅታዊ ችግር ተከትሎም ለሀገራቸው አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጡ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።

አሸባሪው ህወሃት ቡድን በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች በርካታ የጤና ተቋማት እንዳወደመ ያስታወሱት ዶክተር ጌታቸው፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እየተሰባሰበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ከፕሮጀክት ኪዩር ጋር በመሆን 50 ኮንቴነር የሚሆን የህክምና ቁሳቁስ መሰብሰቡን ገልጸው፤ ወደ ሀገር ቤት ለመላክ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የተናገሩት፡፡ እስካሁን ባለው ሂደትም 5 ኮንቴነር የህክምና ቁሳቁስ ወደ ሀገር ቤት መላኩንም ገልጸዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያኑ የሚሳተፉበት የገቢ ማሰባሰቢያ ሁነቶችን በማዘጋጀት ቀሪ ኮንቴነሮችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ይሰራል ነው ያሉት።

ከድጋፉ ባሻገር ከካናዳ የመጡ የህክምና ቡድን አባላት በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በመደገፍ ረገድ አበረታች ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ተግባርም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዲያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ይበልጥ ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑንም ነው ጨምረው የገለጹት፡፡ “ለኢትዮጵያ ያለናት እኛ ልጆቿ ነን” ያሉት ዶክተር ጌታቸው፤ ከዚህ አኳያ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖር ዳያስፖራ ለአገሩ የሚያደርገውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህን በማድረግም ኢትዮጵያን በቀላሉ መለወጥ እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡ via ENA


Exit mobile version