Site icon ETHIO12.COM

ሦስቱ መሪዎቻችን!!

Ethiopia smoke flag

የኢትዮጵያዉ የተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቷል:: ጓድ መንግሥቱ ኀይለ ማርያም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ዋና ፀሐፊ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት፣ የጦር ኀይሎች ጠቅላይ አዛዥ እጅጌ ጉርድ የሆነዉን ወታደራዊ ልብስ ለብሰው እና መለዮዋቸዉን አድርገዉ በምክር ቤቱ ፊት ለፊት ተሰይመዋል::

“ወንበዴዎቹ የአረብ ምንዳ ተከፋዮችም ጭምር ናቸው!”
“እነኚህን ተላላኪ ሀገር አፍራሾች፣ ከሀገራችን ለማስወገድ አንድ ሰው እና አንድ ጥይት እስኪቀረን ድረስ እንዋጋለን!”
ኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለ ማርያም በተናገሩ ቁጥር ቁጣቸዉ ግንባራቸዉ ላይ ተጽፎ ይነበባል:: እልሃቸዉ እና የሀገር ተቆርቋሪነታቸዉም በቁጣ ከሚደመጡት ቃላት ውስጥ ጐልተዉ የታያሉ:: ተሰብሳቢው ንግግራቸዉን የሚያደምጠዉ በጽሞና እና በሙሉ ስሜት ነው::
“ትግራይ ክፍለ ሀገር ለኢትዮጵያ አንድ ቁና እህል አበርክታ አታውቅም:: እኛ ግን የትግራይ ሕዝብ እንዳይራብ እያልን በስንዴ ልመና የነጭ ፊት ይገርፈናል:: የትግራይ ገበሬ ደግሞ ወንበዴ ሆኖ ከቋጥኝ ቋጥኝ እየዘለለ ሀገሬን ይወጋል:: እኛ ለትግራይ ሕዝብ…”
ንግግራቸዉ በደማቅ ጭብጨባ ተቋረጠ:: ማን እንደጀመረዉ ባይታወቅም የአዳራሹ ተሰብሳቢ በሙሉ የግራ እጁን ጨብጦ ወደ ላይ ከፍ እያደረገ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” የሚል መፈክር ያስደምጣል::
“ኢትዮጵያ ትቅደም!”
“ኢትዮጵያ ትቅደም!”
በምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ውይይቱን በአንድ ቴሌቪዥን ብዙ ሆነዉ የሚመለከቱ እና የሚያደምጡ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም “ኢትዮጵያ ትቅደም!” የሚለውን መፈክር ተቀብለዉ እያስተጋቡት ነው::

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለ ማርያም በእልህ ጠረጴዛ እየደበደቡ እና እጃቸዉን እያወራጩ ያደረጉት ንግግራቸዉ ሲቋጭ ፊታቸዉ ላይ ከወረዛዉ ላብ የኢትዮጵያ ምስለ ካርታ ይታይ ነበር::

ሰውዬዉ በብሔራዊ ውትድርና ሰበብ በርካታ የደሀ ልጆችን ወደ ጦር ግንባር አሰልፈዋል ተብለዉ ቢታሙም ሀገራቸዉን በመውደዳቸዉ እና ዘረኛ ባለመሆናቸዉ ግን አንድም ሰው አያማቸዉም::

“አንድ ሰው እና አንድ ጥይት እስከሚቀረን ድረስ እንዋጋለን!” ያሉት ሰውዬ ብዙ ወታደሮች እና ብዙ ጥይቶች እየቀሯቸዉ በአሜሪካ ሴራ ከሀገር እንዲወጡ እና በዚንባቡዌ ጥገኛ ሆነዉ እንዲኖሩ ተገደዋል::

የኢሕአዴግ ዘመኑ የተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ቀጥሏል:: አቶ መለስ አንዳንዴ ከፊታቸዉ ላይ ስውር መሰል ፈገግታ ያሳያሉ:: አንዳንዴ ደግሞ ኮስተር ለማለት ይሞክራሉ:: በአጠቃላይ ገጽታቸዉን አይቶ ባህርያቸዉ አንዲህ ነው ለማለት አይቻልም:: ንግግራቸዉን ግን ቀጥለዋል፤
“አብዛኛዎቹ ኦሮሞዎች ውስጣቸዉ ቢፋቅ ኦነጐች ናቸው:: ይሄ የማይታበል ሀቅ ነው:: ኦነግ ደግሞ የተሰጠዉን ዕድል አልጠቀምም ያለ እና ፓርላማን ሳይሆን ጫካን የሚወድ ቡድን ነው!”

“እኛ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ፓርቲዎችን እስከ ግማሽ መንገድ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁዎች ነን!” “የስኳር እና የጨው መጠቅለያ በሆነ ጨርቅ ላይ ያን ያህልም መከራከር የለብንም:: ሰንደቅ ዓላማን መውደድ ሀገርን መውደድ ነው ብዬም አላምንም!”

“አንድ ሰው እጅ ከፍንጅ ሲሰርቅ እስካልተያዘ ድረስ ሌብነቱ እንደ ሥራ ሊቆጠርለት ይችላል!” “አንዳንድ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች እና ትክህተኞች አሁንም ድረስ በድሮ በሬ እንድናርስ ይፈልጋሉ፤ ይህ ግን ከአሁን በኋላ ህልማቸዉ እንጂ እውን አይሆንም!”

“ለኦሮሞ ሥልጣን መስጠት እና ለሕፃን ልጅ ብርጭቆ መስጠት አንድ ናቸው:: ሁለቱም በተሰጣቸዉ ነገር በአግባቡ መጠቀም ስለማይችሉበት ይሰብሩታል!”
“የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ምኑ ነው?”…
የመለስን የምክር ቤት ንግግር ከሚሰማዉ ተሰብሳቢ ይልቅ የተኛዉ ይበዛል:: ያልተኙትም ቢሆኑ እሳቸዉ ሲቆጡ ፊታቸዉ እየተቆጣ፣ እሳቸዉ ፈገግ ሲሉ ከትከት ብለዉ እየሳቁ፣ መሪዉ አድርጉ ያሏቸዉን የሚያደርጉ ገፀ -ባህሪዎች ይመስላሉ::
ከምክር ቤቱ ወጥተናል::

የካቲት 11 የትሕነግ የልደት በዓል ሆኖ ይከበራል:: አቶ መለስ ዜናዊም በመቀሌ ከብዙ የትግራይ ተወላጆች ጋር ተገናኝተዋል:: ፈገግታቸዉ ከምሥራቋ ጮራ ይበልጥ ፈንጥቋል:: ሕዝቡም ደስታዉን ከአለባበሱ ጀምሮ በተለያየ መንገድ እየገለፀ ነው::
“እንበር ተጋዳላይ!” ይዘፈናል::
“አጁሀ! አጁሀ!” ይደነሳል::
ከበሮዎችን እየዘለሉ የሚደልቁ ትግሬዎች በዝተዋል:: ክብ ሠርተዉ “እስክስ!” እያሉ የሚሽከረከሩትም ከልክ በላይ ናቸዉ:: በአጠቃላይ የመቀሌ ስታዲየም እና ራሷ መቀሌ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በሙሉ የነሱ የሆነች ያህል ፈንጠዚያዉ በዝቷል::

መለስ በትግርኛ ሲናገሩ ስታዲየም ሙሉ የሆነው ሕዝብ ጸጥ ረጭ ብሎ ያዳምጣቸዉ ጀምሯል:: “እናንተ ወርቅ የሆናችሁ ሕዝብ ናችሁ!” ሲሉ በስታዲየሙ የሞላዉ ሕዝብ ጩኸቱን አቀለጠዉ::

“ወርቅነታችሁ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር ነው:: ለምን? ብትሉኝ ያሸነፋችሁት በአፍሪካ በጦር ኀይል ብዛት አንደኛ ነኝ የሚለዉን ደርግን ነው:: ስለዚህ የትግራይ ሕዝብ በእሳት የተፈተነ ወርቅ እና ጀግና ሕዝብም ነው!”
እያንዳንዷን የመለስ ቃል ደስታ እና ሆታ ያቋርጣታል:: አቶ መለስም እጅግ ፈገግ ብለዉ የትግራይ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ እና ጀግና የሆነ ሕዝብ መሆኑን መናገራቸዉን ቀጥለዋል::
* * *
ከጀግና ሕዝብ ተወለድኩ ያሉት መለስ ዜናዊ በአሜሪካ በሚደረግ አንድ ጉባኤ ላይ አበበ ገላዉ ከሚባል አንድ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ተቃውሞ ደረሰባቸዉ:: አበበ ገላው በአዳራሹ ውስጥ ድምፁን ጐላ አድርጐ በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣
“መለስ አምባገነን ነው!”
“መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው!”
እያለ ደጋግሞ ጮኸ:: መለስም ይሄንን ንግግር ሲሰሙ ልባቸዉ ከዳቸዉ:: ዓይኖቻቸዉ ወደ ሽፋሎቻቸዉ ውስጥ ገቡ:: ፊታቸዉ ተቀያየረ:: ከዚያች ቀን በኋላ መለስ ታመሙ:: የሕክምና እርዳታ በተለያዩ ቦታዎች ሲደረግላቸዉ ቢቆይም እስከ ወዲያኛው ተሸኙ::

ዶ/ር ዐቢይ የገቡበት የአራት ኪሎዉ ቤተ መንግሥት ግን በምቾት አልተቀበላቸዉም:: ወርቅ ሕዝብ ነን ያሉት ትግራዮች እና ተረኛ መሪ መሆን እንፈልጋለን ያሉት ኦነጐች ለሰውዬዉ ከባድ ፈተና ሆነውባቸዋል::

የኢትዮጵያ አና የመሪዋ ፈተና በዝቶም በሰውዬዉ ላይ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራዎች ተካሄዱ:: የአማራ ብሔር ተወላጆች በየአቅጣጫዉ መሰደድ እና መገደል እጣ ፈንታቸዉ ሆነ:: የጐዳና ላይ ተቃውሞዎች በረከቱ:: ኮቪድ የዜጐች ሕይወት ስጋት ሆነ:: የትግራይ ክልል የዓቢይን መንግሥት አንቀበልም አለ:: ትግራዮች የራሳቸዉን ምርጫም አካሄዱ:: ትግራዮች በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጭፍጨፋ አደረጉ::

ኢትዮጵያ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ ገባች:: በማይካድራ ብዙ አማራዎች ተጨፈጨፉ:: በመጨረሻም ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ዘመቻዉ አሸነፈች:: በርካታ የትግራይ መሪዎች ተገደሉ፤ ታሰሩ፤ ተሰደዱ:: መቀሌም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ሆነች::

የመንግሥት ሠራዊት ከመቀሌ በተለያዩ ምክንያቶች ሲወጣ ጦርነቱ ዳግም አገረሸ:: የትግራይ ወራሪ ቡድንም በርካታ የአማራ አካባቢዎችን ወረረ:: ሕዝቡን በግፍ ጨፈጨፈ፣ ንብረቱን ዘረፈ፤ አወደመ፤ በርካታ ወንጀሎችን ፈፀመ:: ይህ ሁሉ ሲሆን የትግራይ አሸባሪ ቡድን እና ኦነግ ሸኔ (አሸባሪዎች) ተብለዉ በሀገሪቱ ምክር ቤት ተፈርጀዋል::
ሕግ ማስከበሩ በህልውና ማስከበር ዘመቻ ተተካ:: ዶ/ር ዐቢይም በምክር ቤት ውስጥ እና በተለያዩ ቦታዎች ባደረጓቸዉ ንግግሮች ኢትዮጵያ የማሸነፍ እንጂ የመሸነፍ ታሪክ የላትም!” አሉ::

“ስለ ሀገራችን አንገታችንን እንሰጣለን እንጂ ኢትዮጵያችን አትፈርስም!”
“ኢትዮጵያን ለማሸነፍ የሚፈልጉ ካሉ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ የማያውቁ ብቻ ናቸው!…”
ጦርነቱ እየሰፋ እና እየከፋ መጣ:: የትግራይ ወራሪ ቡድን መሪዎችም ኢትዮጵያውያን እጅ እንዲሰጡ ጠየቁ:: አዲስ አበባ ሊገቡ በመሆኑ ከመንግሥት ጋር ድርድር ማድረግ እንደማይፈልጉም ተናገሩ::

ዶ/ር ዐቢይ “እኔ በግንባር ሆኜ ጦሩን ልመራ ዘምቻለሁ እና ተከተሉኝ!” ሲሉ ለኢትዮጵያውያን መልዕክት አስተላለፉ:: የአማራ ሕዝብ ሆ! ብሎ ወደ ግንባር ዘመተ:: የኋላ ደጀኑም ስለ ሀገሩ ሲል በደጀንነት ተሰለፈ::

በአጭር ቀናት ውስጥ የትግራይ ወራሪ ቡድን በአማራም ሆነ በአፋር በወረራ ከያዛቸዉ ሁሉም ቦታዎች ውስጥ ተጠራርጐ ወጣ:: ድሉም የአፋሮች፣ የአማራዎች እና የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሆነ::

ትፈርሳለች የተባለችዉ ኢትዮጵያ አልፈረሰችም:: ነገስ ምን እናይ ይሆን?

(እሱባለው ይርጋ)
በኲር ታኅሣሥ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ዕትም
(አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን)

Exit mobile version