Site icon ETHIO12.COM

የምህረተአብ “የተጋደሉ” አዋጅ – የ”እንወርሳለን” አዝማች

በአቢሲኒካ መዘገበ ቃላት “መመህር” ለሚለው ቃል የተለያዩ ትርጉሞችና ፍቺዎችችን አኑሯል። ከሁሉም ረቢ የሚለውን ብቻ ለይተን ስናይ “የከበሬታ ስም ጌታዬ፣ ጌታ አለቃ ሹም መምር ሊቅ ሽማግሌ” ሲል ትርጉሙ ይተነትነዋል። መዓልም፣ ሰንከሪስ ፣ መምህር ፣ ሊቅ ፣ ረቢ ፣ ረባን ፣ ሐዳፍ፣ በቁሙ ማሪ፣ መሪ ፣መካሪ አስተማሪ እያለ ይተነትነዋል። እንግዲህ አቶ የነበሩት ምህረተ አብ ” መምህር” የተባሉት ወይም ጌታችን የተሰየመበትን ረቢ የሚለውን ስም የያዙትና መምህር ምህረተ አብ የሆኑት ከላይ ያሉትን ማእረጎች ተሸክመው ነው።

ካሁን በሁዋላ መምህር ምህረተ አብ የምላቸው የሃይማኖት አንቂ፣ ትናንት ባሰራጩት የቪዲዮ መልዕከት ማሳረጊያ ላይ እንደ አሜሪካን ራፒስቶች አይነት የቡድን መፈክር ቢጤም ሲያሰሙ ተስተውሏል። ከላይ የዘርዘርኩትን ሁሉ ሃላፊነት የተሸከመ ሰው ( ማዕረጉ እንዴት እና በምን መስፈርትና ደረጃ እንደሚሰጥ ባላቅም) በዚህ ደረጃ “የተጋደሉ” ጥሪ ሲያቀርቡ መስማቴ ግራ አጋብቶኝ ሳለ ከስር ያለውን ጽሁፍ በማህበራዊ ገጽ ሲዛወር አየሁ። ገረመኝ። አሳቀኝ። ሐዋሪያው ጳውሎስ ” ከእኛም በላይ አዋቂ ለአሳር” ብሎ አምላኩን የወደደ መስሎት በጥፋት ሲዳክርና የኢይርሱስን ተከታዮች ሲያሳድድ ቆይቶ አንድ ቀን ሳኦልነቱ የተቀየረበት ዕለት ሲደርስና የጋረደው ቅርፊት ከአይኑ ሲወድቅ፣ የአምላኩ መንፈስ ሲገባውና ማስተዋልን ሲታደል ” ወንጌል በአፋችሁ ሳይሆን በህይወያችሁ ስበኩ” ማለቱ ታወሰኝ። ሲገለጥለት ከፈርሳዊ ትዕቢቱ ተስፈንጥሮ እንዴት እንደወጣ እንረዳለን። እስኪ አስገራሚውን ምስክርነት እንየው።

“ዛሬም መጡላቹህ!!” አስታውሳለው ከጥቂት ዓመታት በፊት መምህር ምህረተ አብ አሰፋ በቀራንዮ መዳሃኒዓለም ተግኝትው በማንቂያው ደውል እንዲ ብሎ ሰበኩን። ” ሙስሊሞቹ በሙሉ ካራቴ እየሰሩ ነው እናንተ ምንድን ነው የምትጠብቁት ….በቅርቡ መጥተው ይገድሉዋችዋል..ቁጭ ብላቹ አትጠብቁ ተዘጋጁ እየመጡ ነው ” የሚል ነበር ትምህርቱ።

ስብከቱ እንዳለቀ በፍጥነት ወጥተን ብረታችንን ተመዘገብን ( ክብደት ማንሳት መሆኑ ነው ) የቀረ የለም ማለት ይቻላል ሁላችንም ተመዘገብን። ።ብረታችንን ገፍተን ደረታችንን አስፍተን ጡንቻዎቻችንን አፈርጥመን፣ ካራቲስቶቹን ብንጠብቅ ብንጠብቅ አልመጣ አሉን። ግማሾቻችን “እነሱ ካልመጡ ለምን እኛ እንሄድባቸውም” አልን። “የሀይማኖት ሰው እንዲህ አያደርግም ጠብቆ ይገላል እንጂ እነሱ ድረስ አይሄድም” በሚለው ተስማምተን ጥበቃውን ቀጠልን አልመጡም።

…ጠላት የተባሉት ሲቀሩ የገፋነውን ብረት ላለማባከን ብለን እርስ በእርስ የጎሪጥ መተያየት ጀመርን። ከዛም ሰፈሩን ፀብ በፀብ አደረግነው። እኔም ከስንት ክርስቲያን ጓደኞቼ ተጣልቼ ነበር። ዕድሜ ለሙስሊም ጓደኞቼ እነሱ አስታረቁኝ። ለመጣያ ብዙ ምክንያት አለን። በሁሉም እንጣላበት ብንል ጊዜው አይበቃንም።እና ምን ለማለት ነው የፈጣሪን ስም እየጠራቹ የሴጣንን ተግባር አታስተምሩን። በሚል ጊዜ ቆጥረው ምንተስኖት ለገሰ (Mintesnot Legesse #respect #Ethiopia) የተባሉ ወጣት በፌስ ቡክ ገጻቸው የበተኑት መልዕክት ይህ ነው።

እንግዲህ መምህሩ በዚህ መልኩ ማዕረጋቸው ከሚፈቅደው ውጪ ማስተማራቸው ምን ይነግረናል? ምንስ ያስተምረናል? ይህ አካሄዳቸው እናትና አባቶቻችን የገነቡት አስተምህሮት ውጤት ነው ማለት ይቻላል? እነዚህ ልጆች በረት ተሽክመው፣ ጡንቻ አውጥተው ከሙስሊም ወንድሞቻቸው ጋር እንዲዋጉ መቀስቀስ አንም አምላካዊ. ከዛም ህጋዊስ ነው? ይህ ሲሆን ቤተክስርስቲያን ለምን አትገስጽም? ለምንስ አታግድም? ለምን እርምጃ አትወስድም? በአንድ ሉዓላዊ በኤተክርስቲያን ስምና አጸድ ውስጥ እንዲህ ያለ ትምህርት ሲሰጥ ሕዝበ ምዕመኑ ስለምን ዝም ይላል? ይህ ላቁም።

ትናንት ” መስቀል አደባባይ ሊወረስ ነው ዝመት” የሚል ቪዲዮ እኚሁ መመህር እሳት ጎርሰውና እንደ ትንታግ እየጮሁ “ተነስ” እያሉ ሲጣሩ የሚያሳይ ፊልም በማህበራዊ ገጾች ሲሰራጭ አየሁ። ከሁዋላቸው ታጅበዋል። አዋጁ ስለ መስቀል አደባባይ ነው። መስቀል አደባባይ ” የታጠነበት” የኦርቶዶክሳዊያን ንብረት መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ። ጉዳይ እጅግ እንቅልፍ ስለነሳኝ ” ላጣራ” አልኩና መረጃ ሰበሰብኩ።

ባጭሩ ዛሬ መስቀል አደባባይ የፕሮቲስታንት ሃይማኖት ተከታዮች የመዝሙርና የጸሎት ክፈል ጊዜ አላቸው። ለተፈናቀሉ ወገኖችም እርዳታ ያሰባስባሉ። መውሪው ቃል “እንውረስ” የሚል መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። በነገራችን ላይ እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሁሉም ነገር ትኩሳት በሚሆንባት አገር ውስጥ እንዲህ ያለ ቃል መመረጡን አልወደድኩትም።

እንግዲህ ምህረተ አብ የሚባሉት መምህር አንድ ሰው ቢያንስ ለአንድ ሺህ ሰው እንዲያሰራጨው፣ አለበለዚያ የአባቶቹ አጽም እሾህ ሆኖ እንደሚወጋው ያስጠነቀቁትበት የግጭትና የተጋደሉ ቪዲዮ ይፋ የሆነው አገሪቱ በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው። ለህግና መመሪያ ተገዢ በመሆን አርዓያ መሆን ያለበት ሰው በዚህ ደረጃ ” ሂድና ንብረትህን፣ የታተነበትን ቦታህን ተረከብ፣ ነገ ወደዛ ትመም፣ ይህ ካላደረክ ቃል ለምድር ለሰማይ…” እያለ ቡራ ከረዩ ሲያወርድ መንግስት የት ነው ያለው? በዚህ ጥሪ መሰረት ህይወት ቢያልፍ ማን ነው የሚጠየቀው? ምንስ ተፈልጎ ነው እንዲህ ያለ “የተፋጁ” ጥሪ በአደባባይ የተበተነው?

መንግስት ሆይ መስቀል አደባባይን አስመልክቶ ግልጽ አቋም ያዝ። አደባባዩ ዳንክራ፣ የወታደር ሰልፍ፣ ኮንሰርት፣ ኢሬቻ፣ ሩጫ፣ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የተቃውሞና የድጋፍ ስብሰባ የሚካሄደበት ቦታ ሙስሊምም ሆነ ፕሮቴስታንት ሊከለከሉበት የሚችሉበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለምና ይህንኑ በይፋ አስታውቅ። ሁሉም እኩል ዜጋ በሆነበት አገር የሕዝብ ንብረት ላይ ለማዘዝና የበላይ ለመሆን ማሰብ አንድም ህግንና የህግን የበላይነት በምስቀል ስም መፈታተን፣ ሲቀጥል አላማው ማተራመስ ነውና አስቸኳይ እልባትና እርምጃ ይወሰድ።

በመላው አገሪቱ ግብር ከፋይ ሕዝብ፣ በመላው አገሪቱ ስም የተዋበ የመስበሰቢያ ስፍራ “የግል ሃብቴ” በማለት በየቀኑ የሚሰማ ጩኸት መቆም አለበት። ታንክ በሰልፍ ሲንጋጋበት የነበረ፣ ዳንኪራ የሚሰራጭበትን አደባባይ መንፈሳዊና ቅዱስ ቦታ አድርጎ ማቅርብ ልክ ጳውሎስ ሲመጻደቅበት እንደነበረው የፈሪሳዊያን ትምክህት አይነት ነውና ልክ ጳውሎስ አውልቆ እንደጣለው ወደ መስቀሉ በመጠጋት በመንፈሳዊ ማደግ እንዲበረቱ መመህሩን እመክራለሁ። መንፈሳዊ እውቀት ሲያድግ ጩኸት ይከስማል፣ የተፋጁ አዋጅ ይሞታል። ችግር እንኳን ቢኖር ” ተግታችሁ ጸልዩ” እንደሚለው በጸሎትና እንደ ባለ አዕምሮ ሰው በመመካከር መፍትሄ ወደ መፈለጉ ልህቀት ያሸጋገራል። ጥሩ መመህረም ያደርጋል።

በ” ልንከለከል ነው” ፍርሃቻ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችም ጽንፍ የረገጠ አስተያየት በማህበራዊ ሚዲያ በማሰራጨት ጨዋ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወንድሞቻችሁን አታስከፉ። እምነት በስራ ይገለጻልና የክርስቶስ ከሆናችሁ አባትችሁን አታስወቅሱ። እናንተም መካካል መሻሻልና መስተካከል ያለበት በርካታ ጉዳይ አለና አስቡበት። ሳጠቃልል

ኢትዮጵያ ከጣቻቸው በሳል ሊቃውንቶች መካለል አለቃ አያሌው “ዛርን” ለዩ ሲሉ በአንድ ወቅት አስተምረው ነበር። ነብሳቸውን ይማረውና አለቃ አያሌው በቅዱስ ዮሃንስ ቤተክርስቲያን ይህን ሲያስተምሩ ” ዓነ ስውር ሆኜ በመፈጠሬ አምላክን አመስግናለሁ። ምክንያቱም የምሰማውን መሸከም አቅቶኛል። በዚህ ላይ ማየት ብችል ምን እሆን ነበር? በምሰማው ላይ መመልከትን ባክልበት መቋቋም እንደማልችል መድሃኔዓለም ያውቅ ነበር” ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ። ይህን ያሉት ደግሞ በዛን ሰሞን ባህታዊ ገብረምስቀል የሚባሉ ሰው ሕዝቡን በዛር መንፈስ እንዴት ይነዱት እንደነበር ለማስተማር ነበር። በታዛቢ ጋዜጣ ላይም አማኞች የዛር መንፈስ የሚያስለፈልፋቸውና የሚያስጓራቸውን መለለየት እይችሉ ዘንድ ውብ ቃለ ምልልስም ሰጥተው ነበር። እሳቸው እንዳሉ ብዙም ሳይቆይ ባህታዊው በቀጨኔ ማረፊያቸው የሰሩት ጉድ ወጣ። ዛሬም ጉዳዩ እንዲህ ነው። ባህታዊውን በጅምላ እየተነዳ ሲከተላቸው የነበረውም ሕዝብ ሲባንን ነቃና ተለያቸው። በሁሉም ዕምነት እያስጮሁ ሕዝቡን የሚያተራምሱና የሚዘርፉ ይስተዋላሉ። አጀንዳው ስላልሆነ እንጂ ንግዱ እዛም እዚህም በየቦታው ነው። መልካሞቹን አያካትትም። ለትምህርት እንዲሆን ከስር ያለውን አክያለሁ።

ሐዋርያው ጳውሎስ ስለህግ ብትጠይቁኝ ፈሪሳዊ ነበርኩ ፤ በህግ ስለሚገኝ ጽድቅ ያለነቀፋ ነበርኩ ሲል መናገሩን ወንጌል በ(ፊሊጲስዮስ 3፡8-9) ይነግረናል። ከገባውና ኢየሱስን ማወቅና መከተል እንዳለበት ሲገባው “… ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲፀድቅ እንጂ በህግ ስራ እንዳይሆን አውቀን ስጋን የለበሰ ሁሉ በህግ ስራ ስለማይፀድቅ እኛ ራሳችን በህግ ስራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንፀድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል (ገላትያ 2፤16) ሲል ልቡ ውስጥ የሞላውን መናገሩን አሁንም ቅዱስ መጽሃፍ ይመሰክራል። ጳውሎስ ይህን ሲጽፍ ለገሌ ወይም ለተወሰነ ቡድን አላለለም።

ሰብለ ወንጌል ዮሐንስ


Exit mobile version