Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ የጤናማ አመጋገብ መመሪያን ይፋ ልታደርግ ነው

በኢትዮጵያ የጤናማ አመጋገብ መመሪያ [dietary guideline] ከአንድ ወይም ከሁለት ወር በኋላ ይፋ እንደሚሆን በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የምግብ ስርዓት እና ስነ ምግብ ምርምር ዳይሬክተሩ ዶ/ር ማስረሻ ተሰማ ለቢቢሲ ገለጹ።

ሃላፊው ለሶስት ዓመታት ሲዘጋጅ የቆየው የጤናማ አመጋገብ መመሪያ ወደ መጠናቀቁ መደረሱን ገልጸው በጤና ሚኒስቴር እና በሌሎች ሚኒንስቴር መስሪያ ቤቶች የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዶ/ር ማስረሻ የመመሪያውን አስፈላጊነት ሲገልጹ “ህብረተሰቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንድን ነው መብላት ያለብኝ? በሚል ብዙ ሰው ይጠይቃል የተማረም ያልተማረም ሰው ስለዚህ ይህንን በዘላቂነት ለመመለስ” የተዘጋጀ መሆኑን አስረድተዋል።

መመሪያው ለማዘጋጀት ‘ሰፊ ጥናት’ እንደተደረገበትም ገልጸዋል። እድሜያቸው ከሁለት ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች የተዘጋጀ ሲሆን ምን አይነት ምግቦች እና አመጋገቦች ለጤናማ ህይወት እንደሚረዳ የሚያመላክት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም በሀገሪቱ ዙሪያ ያሉ ባህላዊ እሴቶችን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አክለዋል።

ጤናማ የአመጋገብ መመሪያ ምንድን ነው?

እንደ ዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት ትርጓሜ ጤናማ የአመጋገብ መመሪያ በሀገራት ውስጥ ጤናማ የአመጋገብ እና የኑሮ ዘይቤም ለመገንባት የሚወጡ ናቸው።

በውስጣቸውም ከስነ ምግብ አኳያ ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን እና አመጋገቦችን በተለያዩ የእድሜ ክልል ለሚገኙ ዜጎቻቸው በምክረ ሃሳብ መልክ የሚያቀርቡበት ነው። በተጨማሪም እርሻና የምግብ ዝግጅትን በተመለከተ የሚያትት ነው።

በሌላ በኩል ጤናን ለማጎልበት እና አሳሳቢ በሽታዎችን ለመከላከል የሚረዱ ንጥረ ነገርን ያዘሉ ምግቦች የአመጋገብ ዘይቤዎች ላይ ምክር ሃሳብ ይሰጣሉ።

እንደ ድርጅቱ መረጃ በዓለም ከአንድ መቶ በላይ ሀገራት የጤናማ አመጋገብ መመሪያ አላቸው።

በአፍሪካ ሰባት ሀገራት ይህ መመሪያ ያላቸው ሲሆን ከሌሎች አህጉራት አንጻር ዝቅተኛው ነው። በአህጉሪቱ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሲሼልስ፣ ናይጄሪያ፣ ቤኒን፣ ናሚቢያና ሴራሊዮን የአመጋገብ መመሪያ አላቸው።

ከሁለት ወር በታች በሆነ ጊዜ የጤናማ አመጋገብ መመሪያን ይፋ ለማድረግ ያቀደችው ኢትዮጵያ 8ኛዋ የአፍሪካ ሀገር እንደምትሆን ይጠበቃል።

ቢቢሲ አማርኛ ላይ ዋናውን ዜና ይመልከቱ

Exit mobile version