Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ የክምችት ኪሷ መራቆቱ ተገለጸ፤ ብቸኛው አማራጭ ሰላም ብቻ ነው

ኢትዮጵያ በምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነትና ጫና ሳቢያ የውጭ ምንዛሬ ቋቷ ተመናምኖ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ያላት አቅም በዛ ቢባል ለሁለት ወር የሚበቃ ብቻ እንደሆነ ይፋ ሆነ። ጦርነቱ ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ጋር ብቻ እንዳልሆነና በሳል አካሄድን መከተለ እንደሚገባ ባለሙያዎችና መንግስት በከፍተኛ አመራሩ ሲናገር የቆየው ይህንኑ ነበር።

“የምእራባዊያን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ጉዳዮችና ድህረ ግጭት” በሚል ርዕስ በቀረበ መረጃ ላይ የተደገፈ ጥናት ነው የአገሪቱ ካዝና በደቦ ዘመቻ መመናመኑ የተመለከተው።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ምሁር ፕሮፌሰር አለማየሁ ገዳ በዚሁ መድረክ ላይ እንዳስታወቁት ባሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ቢበዛ ለሁለት ወር የሚበቃ እንደሆነ ሳይሸፋፍኑ ተናግረዋል።

በብሄር ፖለቲካ እየታነከች ያለችው ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት ጀመሮ ዙሪያዋን አንድ መቶ አስራ ሶስት የግጭትና የትርምስ ቀጠናዎች እንደተዘጋጁላት፣ ይህም የተደረገው አገሪቱን ሲዘርፍ በነበረው ትህነግ አማክይነት እንደነበርና ዓላማውም የአገሪቱና አቅም በማናጋት በኑሮ ውድነት ህዝቡን ማደቀ እንደነበር መገለጹ ይታወሳል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል አሸባሪው ትህነግ ስራ ላይ የነበሩ ኢንዱስትሪዎችን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ወደ ስራ ለመግባት የተዘጋጁ ድርጅቶችን ጭምር ማውደሙን፣ ይህን ያደረገው የኢንዱስትሪ ልማቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እንዳይደግፍ ለማድረግ ሆነ ብሎ እንደሆነ ወረራው ከተቀለበሰ በሁዋላ ተናግረዋል። በኮምቦላቻ ብቻ 82 በማምረት ላይ የነበሩና 5 በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ላይ ውድመትና ዝርፊያ ቢፈጽምም በርብርብ ሃያ ሰባቱ ማምረት መጀመራቸውን አመልክተዋል። ቡድኑ የጅቡቲን መንገድ ዘግቶ የአገሪቱን አንገት ለማነቅ ተንቀሳቅሶ እንደነበረም ይታወሳል።

የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በኢትዮጵያ ጉዳዮችና ድህረ ግጭት ላይ ትኩረት የሰጠውው የፕሮፌሰሩ ጥናት አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከሌሎች ጎረቤት ሀገራት አንጻር ሲታይ በጣም ውስን እንደሆነ አመልክተዋል። ኬኒያን በምሳሌ አንስተው ለስድስት ወር የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዳላት ጠቁመዋል።

የውጭ ምንዛሬ ዕጥረቱ በጦርነቱና በምእራባዊያን ትጽእኖ ሳቢያ መከሰቱን ያመለከቱት ፕሮፌሰር፣ የውጭ ኢንቨስትመንት መቀነስ፣ የተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ አገራት ድጋፍ መቋረጥ የምንዛሬውን እጥረት ያባባሱ ሁነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ አመልክተዋል።

ትህነግ የአገሪቱን መሳሪያና ሎጂስቲክ ሙሉ በሙሉ ዘርፎ ውጊያ ሲከፍት ሃይል ለማመጣጠን አገሪቱ መሳሪያ መግዛቷ፣ ፈርሶ የነበረውን አየር ሃይል ለማዘመን ወጪ ማውጣቷ በየአጋጣሚው መገለጹ ይታወሳል። የአማራና የአፋር ክልልን ወሮ የነበረውን የትህነግ ሃይል ለመደምሰስ አገሪቱ ወደ ሙሉ ጦርነት መግባቷና በኦሮሚያ ትህነግ ይቀልበዋል የሚባለው ሸኔ እያደፈጠ በሚፈጽመው ጥቃት ኢንቨስትመንቱ ክፉኛ መጎዳቱ መገለጹ ይታወሳል።

በጫናና በውክልና በተሰማሩ ሃይሎች ተወትሮ ትህነግን ያስተነፈሰው መንግስት ወደ ድርድርና ሰላም ፊቱን ሲያዞር የሚጮሁ ረጋ ብለው ሊያስቡ እንደሚገባ፣ አገሪቱ ከዚህ በሁዋላ ጦርነት የመሸከም አቅሟ እጅግም መሆኑንን በመረዳት ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ለመመለስ በጦርነቱ ወቅት የታዩት ድጋፎች ዓይነት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አዋቂዎች እየጠቆሙ ነው። በዲፕሎማሲው መልካም ውጤት እየተመዘገበ በመሆኑ ትህነግ ይህን ለማበላሸት የጀመረውን ዘመቻና ፕሮፓጋንዳ በጥበብ ማስተናገድ እንደሚገባ፣ ከሁሉም በላይ ታግደው የነበሩ አገልግሎቶች መከፈታቸውን፣ ታስረው የነበሩ ተጠርጣሪዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ ስለሚመለሱ ሕዝብ በየአካባቢው ወታደር ሊሆን እንደሚገባ እየመከሩ ነው።

ከዚህ በዘለለ በበሬ ወለደና ውጤቱ በአገር ደረጃ ምን እንደሆነ በማይታወቅ አጉል የብሄር ውዝግብና ጥርጥር በመፍጠር የአገሪቱን ጣር ለማብዛት የሚሰሩ ለምስኪኑ ሕዝብ ሲሉ አጉል ሽፍጣቸውን በማቆም ሰላምን ሊያበረታቱ እንደሚገባ እነዚሁ ወገኖች አመልክተዋል።

Exit mobile version