Site icon ETHIO12.COM

የእሽሙር ማህበር (JOINT VENTURE)

የእሽሙር ማህበር ምንነት – የእሸሙር ማህበር በአዲሱ የንግድ ህግ ከተካተቱ ሰባት የንግድ ማህበር አይነቶች አንዱ ሲሆን ማህበሩ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በመካከላቸው በሚያደርጉት ስምምነት መሠረት የሚያቋቁሙት በሦስተኛ ወገኖች የማይታወቅና የሕግ ሰውነት የሌለው የንግድ ማህበር እንደሆነ በንግድ ህጉ አንቀፅ 234 ስር ተደንግጓል፡፡ ይሁንና የማህበሩ መኖር በሦስተኛ ወገኖች ከታወቀ ጊዜ አንስቶ ማህበሩ ከእነዚህ ወገኖች ጋር በሚኖረው ግንኙነት እንደ ህብረት ሽርክና ማህበር ይቆጠራል፡፡ የእሽሙር ማህበር ከሌሎች የንግድ ማህበራት ከሚለዩት ባህርያት የንግድ ማህበሮች የማስመዝገብ ሥርዓቶች በዚህ ማህበር ላይ ተፈጻሚ የማይሆን መሆኑ ነው፡፡

የእሽሙር ማህበር ባህርያት

የእሽሙር ማህበር መመስረት አንደኛ ሸሪክ ያለው ነገር ግን ሌላኛው ሸሪክ የሌለውን ጠንካራ ጎን ለመጋራት ያስችላል፡፡ ለምሳሌ እውቅና እና መልካም ስም ያለው የንግድ ስም (Brand Name ) ካለው የንግድ ማህበር ጋር ሽርክና የገባ ካንፓኒ ከመልካም ስሙ ተጠቃሚ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ሁለት ሸሪኮች ያሏቸውን ጠንካራ ሀብት (የገንዘብ፣ የእውቀት፣ የቴክኖሎጂ እና የመሳሰሉትን) በማቀናጀት የተሻለ ውጤታማ የሆነ ማህበር ይመሰርታሉ፡፡ የሚከተሉት የእሽሙር ማኅበር ልዩ ባህሪያት ተብለው ሊወሰዱ ይችላሉ፡-

1. ህጋዊ ሰዉነት የሌለዉ ስለመሆኑ

የእሽሙር የሽርክና ማኅበር ህጋዊ ሰዉነት የለዉም ሲባል በሸሪኮች መካከል ያለዉ ግንኙነት ተራ ዉል ግንኙነት ነዉ ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም ሸሪኮቹ የአንድ ተቋም አባላት ሳይሆኑ ተራ ዉል ተዋዋይ ወገኖች ናቸዉ፡፡ ይልቁን ህጋዊ ሰዉነት ስለሌለዉ የንግዱ ስራ የሚሰራዉ በሸሪኮቹ ስም ነዉ፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ሸሪክ ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ሲዋዋል፣ ዉሉን ሲፈጽም ወዘተ… በራሱ ስም ነዉ፡፡ ይህም የሚሆነዉ የሽርክና ማኅበሩ ለሶስተኛ ወገኖች ስውር ስለሆነ ነዉ፡፡ የእሽሙር ማኅብር ህጋዊ ሰዉነት ስለሌለዉ ሸሪኮቹ የሚያዋጡት ገንዘብ እና ሀብት የማኅበሩ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም በንግድ ህጉ ቁጥር 236/2 ስር እንደተደነገገው ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር እያንዳንዱ ሸሪክ ያዋጣው ንብረት ባለቤት ነዉ፡፡

2. ለሶስተኛ ወገኖች የማይታወቅ መሆኑ

ለሶስተኛ ወገኖች አለመታወቁ (ድብቅ መሆኑ) ያለመመዝገቡ ውጤት ነዉ፡፡ የሕግ ሰዉነት ስለማይኖረዉ እንዲመዘገብ አይደረግም፡፡ ካልተመዘገበ ደግሞ ለህዝብ የሚታወቅበት መንገድ አይኖርም ማለት ነዉ፡፡ እዚህ ላይ የእሽሙር ሽርክና ማኅበር ድብቅነት የመመዝገብ ግዴታ ካለመኖሩ ብቻ የመነጨ ሳይሆን ይልቁንም በህጉ ታዉቆ እና ታስቦበት የተደነገገ ነዉ፡፡ አሰራሩም ያልተለመደ እና ግራ አጋቢ ቢመስልም በሌሎችም አገሮች የተለመደ እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ ያለ አይደለም፡፡

3. ቅንጅት መፍጠር (Creates Synergy)

የእሽሙር ማህበር በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ማህበራት መካከል ሲመሰረት አንደኛው ሸሪክ የሌላኛውን ባህርይ ለመጠቀም ያስችለዋል (extract the qualities of each other)፡፡ እንዲሁም አንዳቸው ያንዳቸውን ጥቅም ለመጋራት ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው ቅንጅት መፍጠር ይችላሉ ማለት ነው( a joint venture to generate synergies between them for a greater good)፡፡ይህም በተዘዋዋሪ ትልቅ ካፒታልን ለመፍጠር የሚያስችላቸው ሲሆን ወጪያቸውንም እንዲቀንሱ ይረዳቸዋል፡፡

4. ስጋት/አደጋን መጋራት (Risk and Rewards can be Shared)

የእሽሙር ማህበር በአንድ ሀገር ውስጥ ባሉ ድርጅቶች ወይም በተለያዩ ሀገሮች ባሉ ድርጅቶች መካከል ሊደረግ የሚችል ሽርክና በመሆኑ በእነዚህ ሀገሮች ሊኖሩ የሚችሉ የባህል ልዩነቶች (diversifications in culture)፣ የቴክኖሊጂ፣ የመልከዓ መድር አቀማመጥ ጥቅምና ጉዳት (geographical advantage and disadvantage)፣ የተደራሽ ደንበኝ (target audience) ሁኔታዎች በማህበሩ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ተፅዕኖ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡ በመሆኑም በሸሪኮች መካከል የሚደረግ ስምምነት የአደጋ ስጋቶችን እና ጥቅሞች ለመጋራት ያስችላቸዋል፡፡

5. የተለየ ህግ አለመኖር (No Separate Laws)

የእሽሙር ማህበር የሕግ ሰውነት የሌለው የንግድ ማህበር በመሆኑ ማህበሩን የሚያስተዳድር የተለየ ሕግ አይኖርም፡፡ እንዲሁም ይህን ማህበር በተለየ ሁኔታ የሚያስተዳድር አካልም የለም(no separate governing body which regulates the activities of the joint venture.)፡፡

የእሽሙር ማህበር ጥቅሞች (advantages of a Joint Venture)

1. የምጣኔ ሀብትን ማሳደግ (Economies of Scale)

የእሽሙር ማህበር ሸሪኮች ወይም ድርጅቶች ሀብታቸውን ወይም ካፒታላቸውን በማጣመር ስለሚቋቋሙ ህብረት መመስረታቸው ውስን አቅማቸውን ለማሳደግ ይረዳቸዋል፡፡

2. አዲስ ገበያ መድረስ እና የአውታረ መረቦችን ስርጭት (Access to New Markets and Distribution Networks)

አንድ ድርጅት ከሌላ ድርጅት ጋር የእሽሙር ማህበር ስምምነት ሲያደርግ አንደኛው የሌላኛውን የገበያ እድል የመጠቀም እና የማሳደግ አጋጣሚን ይፈጥርለታል፡፡ ለምሳሌ አንድ የአሜሪካ ካንፓኒ ከህንድ ካንፓኒ ጋር የእሽሙር ማህበር ስምምነት ቢያደርግ በህንድ ውስጥ የሚኖርን ሰፊ፣ የተለያየ የመግዛት ፍላጎት እና አቀም ያለውን ገበያ የመድረስ ጥቅም ያገኛል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የህንድ ካንፓኒም በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝን ጥሩ የመክፈል አቅም ያለውን ገበያ መቀላቀል ይችላል ማለት ነው፡፡

3. ፈጠራን ማሳደግ (Innovation)

የእሽሙር ማህበር ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ከቴክኖሎጂ አንጻር ለማሻሻል እድልን ይፈጥራል፡፡ በመሆኑም የቴክኖሎጂ መሻሻል እና የፈጠራ ስራዎች ማደግ የተሻሉ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ውጤታማ በሆነ ዋጋ( efficient cost) ለማቅረብ ያስችላል፡፡ አለም አቀፍ ድርጅቶች አዳዲስ ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ በተሻለ ጥራት እንዲያቀርቡ ያደርጋል ማለት ነው፡፡

4. የማምረቻ ወጪን ማሳነስ (Low Cost of Production)

ሁለት እና ከሁለት በላይ ሸሪኮች ሲጣመሩ ውጤታማ በሆነ ዋጋ ምርትን ለደንበኞች ማድረስ አንዱ አላማቸው ነው፡፡ ይህም የሚሆነው የማምረቻ ዋጋን መቀነስ ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም የማምረቻ ዋጋን በጋራ በመቀነስ የተሻለ ምርት እና አገልግሎትን ለደንበኞች ያቀርባሉ፡፡

የእሽሙር ማህበር ጉዳት (Disadvantages of a Joint Venture)

1. ግልፅ ያለሆነ አላማ፡- ሸሪኮች በእሽሙር ማኅበር ሲጣመሩ አላማቸውን በጣም ግልፅ በሆነ ሁኔታ የማያስቀምጡበት አጋጣሚ በርካታ ነው፡፡ እንዲሁም የማህበሩ አላማ ለሁሉም የማህበሩ አባላት በአግባቡ ላይገለፅላቸው ይችላል፡፡

2. ተለዋዋጭነት ሊገደብ ይችላል (Flexibility can be restricted)፡- እንደየሁኔታው መስራት ወይም ተለዋዋጭነት ሲገደብ አባላቱ የግል ቢዝነሳቸውን ቸል በማለት ወደ እሽሙር ማኅበሩ የበለጠ ትኩረት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የግል ቢዝነሳቸውን ሊጎዳው ስለሚችል ለማህበሩ የሚያበረክቱት አስተዋፆ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

3. እኩል ተሳትፎ ያለማድረግ፡- በመርህ ደረጃ የማህበሩ ሸሪኮች እኩል ሀላፊነት እና ደረሻ ያላቸው ቢሆንም በተግባር ግን ሁሉም አባለት እኩል አስተዋፆ ላያደርጉ ይችላሉ፡፡

4. ያለመመጣጠን፡- የአሽሙር ማህበር ሽርክና የሚመሰርቱት በተለያየ የባለሞያ ብቃት እና ብዛት፣ የሀብት እና የኢንቨስትመንት ደረጃ ባላቸው ሁለት እና ከሁለት በላይ ካንፓኒዎች ስለሆን ይህ ደግሞ ያለመመጣጠን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ በማህበሩ ውጤታማነት አሊታዊ ተፅኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

የእሽሙር ማህበር የመዋጮ ዓይነትና መጠን

የመዋጮ ዓይነትና መጠን በተመለከተ ለሽርክና ማህበር የተደነገገው ለእሽሙር ማኅበር ተፈጻሚ እንደሚሆን የንግድ ህጉ አንቀፅ 236 ያመለክታል፡፡ በዚሁ መሰረት በንግድ ህጉ አንቀፅ 186 ስር እንደተቀመጠው እያንዳንዱ ሸሪክ ጥሬ ገንዘብ፣ የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ የሞያ አገልግሎት፣ የንግድ ምልክት፣ መልካም ስም፣ ፓተንት፣ ኮፒ ራይት፣ የሊዝ መብት፣ የአላባ ጥቅም ወይም ሌላ የዓይነት መዋጮ መክፈል አለበት። መዋጮው የማህበሩ ሀብት እንዲሆን ወይም ማህበሩ እንዲጠቀምበት ሆኖ ሊከፈል ይችላል። ሸሪኮች ለማህበሩ የሚያስገቡት መዋጮ የማህበሩን ዓላማ ለማሳካት የሚያስፈልገው ዓይነትና መጠን እንዲሁም ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር መጠኑ እኩል መሆን አለበት።

የዓይነት መዋጮ ግምት በሸሪኮች ስምምነት የሚወሰን ሆኖ በዓይነት የተከፈለ መዋጮ ግምት የተጋነነ ሆኖ ከተገኘ ያዋጣው ሸሪክ በግምቱና በትክክለኛው ዋጋው መካከል ያለውን ልዩነት በጥሬ ገንዘብ መክፈል አለበት፡፡ ልዩነቱን በጥሬ ገንዘብ መክፈል ካልቻለ ድርሻው በትክክለኛው ግምት መሠረት ይሆናል፡፡በተጨማሪ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር እያንዳንዱ ሸሪክ ለከፈለው መዋጮ ባለቤትነቱን እንደያዘ ይቆያል፡፡ እንዲሁም ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር በማህበሩ ውስጥ ያለን ድርሻ ማስተላለፍ የሚቻለው ሁሉም ሸሪኮች ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡

የማህበሩ ሥራ አመራር

የእሽሙር ማህበር ሸሪክ ወይም ሸሪክ ባልሆነ በአንድ ወይም ከአንድ በላይ በሆኑ ሥራ አስኪያጆች ሊመራ የሚችል ሆኖ ሥራ አስኪያጅ ያልተሾመ እንደሆነ ሁሉም ሸሪኮች የሥራ አስኪያጅነት ሥልጣን ይኖራቸዋል፡፡ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር በማህበረተኞች መካከል በሚደረግ ስምምነት ይወሰናል፡፡ ሆኖም ይህ ስምምነት በሦስተኛ ወገኖች ላይ መቃወሚያ ሊሆን አይችልም።ሥራ አስኪያጁ የማህበሩን ሥራዎች ለሸሪኮቹ የማስረዳት ግዴታ ያለበት ሲሆን ይህን ግዴታ የሚያስቀር ማንኛውም ስምምነት ዋጋ አይኖረውም። የማህበሩ ሸሪኮች ደግሞ የሥራ አስኪያጁን ሥራ መቆጣጠር ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የማህበሩ ሸሪክ የሆነ ሥራ አስኪያጅ በበቂ ምክንያት ሊሻር ይችላል፡፡

ማህበሩ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ስላለው ግንኙነት

በንግድ ህጉ እንደተደነገገው የእሽሙር ማህበር ለሶስተኛ ወገኖች የማይታወቅ በመሆኑ ለሦስተኛ ወገኖች የሚታወቀው የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ብቻ ነው፡፡ ለማህበሩ ዕዳዎች እና ግዴታዎች ኃላፊና ተጠያቂ የሚሆነውም እሱ ብቻ ነው። የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ያልሆነ ሸሪክ ለማህበሩ ዕዳዎች ለሥራ አስኪያጁ ተጠያቂ የሚሆነው በማህበርተኞች መካከል በተደረገው የውል ጽሁፍ በተወሰነው መጠን ብቻ ነው። ሥራ አስኪያጅ ያልሆነ ሸሪክ በማህበሩ ሥራ አመራር ተካፊይ ከሆነ ለሦስተኛ ወገኖች ከሥራ አስኪያጁ ጋራ በአንድነት እና በተናጠል ኃላፊ ይሆናል። ማንኛውም የማህበሩ ሸሪክ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር ግንኙነት ማድረግ የሚችለው በራሱ ስም ብቻ ነው፡፡

ሸሪክን ከማህበሩ ስለማስወጣት

በአንድ ሸሪክ ጥፋት ምክንያት የእሽሙር ማህበር እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲቀርብና ሌሎች ሸሪኮች ማህበሩ እንዳይፈርስ ሲያመለክቱ ፍርድ ቤቱ ማህበሩ እንዲፈርስ በመወሰን ፈንታ ጥፋተኛ የሆነውን ሸሪክ ከማህበሩ እንዲወጣና ማህበሩ እንዲቀጥል ለማዘዝ ይችላል።ይሁንና ከማህበሩ እንዲወጣ የተደረገ ሸሪክ በወጣበት ጊዜ የነበረው ድርሻ እንዲከፈለው የመጠየቅ መብት አለው፡፡ በተጨማሪ አንድ ሸሪክ ከማህበሩ የሚወጣበት ምክንያት በማህበርተኞች መካከል በሚደረግ ውል ሊወሰን ይችላል።

የማህበሩ ማፍረሻ ምክንያቶች

የንግድ ማህበራት የሚፈርሱበትን ሁኔታ የሚመለከቱት ጠቅላላ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆኖ ማህበሩ የሚፈርሰው በሚከተሉት ምክንያቶች ሲሆን የእነዚህን ምክንያቶች ተፈፃሚነት የሚያስቀር ማንኛውም ስምምነት ተቀባይነት እንደማይኖረው የንግድ ህጉ አንቀፅ 242/2 ያስቀምጣል፡፡ምክንያቶቹም፡-

• ሸሪኮች ማህበሩ እንዲፈርስ በሙሉ ድምፅ ሲስማሙ፤

• ማህበሩ የተቋቋመው ላልተወሰነ ጊዜ ሲሆን ከሸሪኮች አንዱ እንዲፈርስ ለማህበሩ ጥያቄ ያቀረበ እንደ ሆነ፤

• ሁሉም የማህበሩ ድርሻዎች በአንድ አባል የተያዙ እንደሆነ፤

• ማህበሩ አንዲቀጥል የሚያደርግ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በስተቀር ከማህበሩ ሸሪኮች አንዱ የሞተ ወይም የከሠረ ወይም ችሎታ ያጣ እንደሆነ፤

• በማህበርተኞች መካከል በሚደረግ ውል ለሥራ አስኪያጁ ማህበሩን ለማፍረስ ሥልጣን ተስጥቶት ከሆነ ሥራ አስኪያጁ ማህበሩ እንዲፈርስ ሲወስን።

በመጨረሻ በንግድ ህጉ ስለእሽሙር ማህበር የተደነገጉት ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ስለህብረት ሽርክና ማህበር የወጡት ድንጋጌዎች እንደ አግባብነታቸው በእሽሙር ማህበር ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ በንግድ ህጉ አንቀፅ 244 ስር ሰፍሮ ይገኛል፡፡

ከፍትህ ሚኒስቴር የተወሰደ

Exit mobile version