Site icon ETHIO12.COM

ጂማ – ሰባት ሚሊዮን ዶላር ለቆጠቡ የዳያስፖራ አባላት የግንባታ ቦታ ተሰጠ

በጅማ ከተማ በማህበር ተደራጅተው ሪል ስቴት ለመገንባት 7 ሚሊዮን ዶላር የቆጠቡ የዳያስፖራ አባላት የግንባታ ቦታ ተረከቡ። የግንባታ ቦታው የተሰጠው በጅማ ከተማ ሪል ስቴት ለመገንባት ከስድስት ዓመታት በፊት በማህበር ተደራጅተው ለቆጠቡ 120 የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በጅማ ከተማ የተለያዩ ስፍራዎችን ከጎበኙ በኋላ ሪል ስቴት መኖሪያ ቤት የሚገነቡበትን ቦታ ተረክበዋል፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ነጂብ ራያ ሀገራችን ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትየጵያውያንና ትውልደ ኢትየጵያውያን ዳያስፖራዎች ለሀገራቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

አሁን ሀገራቸውን ለመገንባት የሚያደርጉት ስራ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ በሌሎች ዘርፎችም ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ገንዘብ በማሰባሰብ ለጅማ ከተማ ልማት የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህፃናት የሚማሩበት “ቡኡረ ቦሩ” የተሰኘ ትምህርት ቤትን በከተማዋ እያስገነቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የጅማ ዞን ምክትል አስተዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮ በበኩላቸው በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ሙአለ ነዋይ ማፍሰስ ለሚፈልጉ በጅማ የተመቻቸ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ምክትል አስተዳዳሪው አክለውም በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በግብርና እና በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች እድሉ ይመቻቻል ብለዋል፡፡

በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኦሮሞ ማህበር መስራች ፀሐፊ አቶ መሀመድ አባ ዋጂ በበኩላቸው የምእራባውያን ጫና ሀገራቸው ላይ ሲደርስ ሲቃወሙና ድምጻቸውን ሲያሰሙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት “ወደ ትውልድ ሀገራችን መጥተን ሀገራችንን የመጎብኘትና የማልማት እድሉን በማግኘታችን ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡

ከካይሮ የመጡት አቶ ማሜ ሁሴን በበኩላቸው በጅማ ከተማ የተደረገላቸው አቀባበል ዳያሰፖራውን ያስደሰተ መሆኑን በመግለጽ ሀገራችንን ለማልማት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

ወደ ሀገር ያልገቡ ዳያስፖራዎችና በኢትዮጵያ ተገኝተው እየጎበኙ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባላቸው ጥሪት ሀገራቸውን ለማልማት ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

ለዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት የከተማዋ ከንቲባ፣የጅማ ዞን ምክትል አስተዳደሪ፣የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ዜናው የኢዜአ ነው

Exit mobile version