ETHIO12.COM

እነሆ የድሉ ባለቤቶች

« እናት ከልጇ በላይ ምንም ስስት ነገር የለም። ትልቅ በጎ ምኞቷ የነገ ተስፋውን የማየት ጉጉቷ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። ይቺ እናት ልጄ ከሀገሬ አይበልጥም ብላ ከአንድም ሁለት ሦስትና አራት ልጆቿን መርቃ ሠራዊቱን እንዲቀላቀል ለፍትህና ለነፃነት እንዲታገል በድል እንዲመለስ ካልሆነም ደሙን ለእናት ሀገሩ እንዲያፈስ፤ ኢትዮጵያ ተሻግራ በትውልድ እንዲታዋስ ለመጪው ትውልድ ጀግንነት እንዲያወርስ የወሰነች እናት ድሏ የእሷ ነው»

By (ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ )

በጎም ሆነ መጥፎ ተግባር ባለቤት ሊኖረው ዘንድ ግድ ነው። በዚህ መሥፈርት የሠራ ይወደሳል። ያጠፋ ይወቀሳል። በታሪክ የክብር መዝገብ ላይ የሚሰፍር እንዲሁም እንዳይደገም እኩይ ተግባሩ ሲነገር የሚኖር ግለሰብ ቡድን ነበረ። ወደፊትም ይኖራል።

መፈተን ፈተናውን ማለፍ ለኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም የውስጥ ነቀርሳና አበሳ የውጭ ፣ የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን እንደዚህ ዘመን አብረው ተባብረው የተነሱብን ወቅት ስለመኖሩ ያጠራጥራል። ድል አድራጊነት ሌላው መገለጫችን በመሆኑ አሁንም የተፈራው ቀርቶ የተወራው ማሚቶ እዚህ ላይ ደርሰናል። ድልም ተጎናፅፈናል። ድሉ ደግሞ ባለቤት አለው። የድሉን ባለቤት መዘከር ድል አድራጊዎችን በየዘመኑ ለመፍጠር ያግዛልና እነሆ!

ኢትዮጵያ ከተደገሰላት ጥፋት ተርፋለች። እልፍ አድማጭ ፣ ተመልካችና አንባቢ ያላቸው የምዕራባውያን የሚዲያ ተቋማት ሐቋን ሸፍነው ከጉዳይ አስፈፃሚያቸው ጎን ቆመው እውነታችንን ከማጣመምም አልፎ ለመስበር ሞክረዋል።

በደረሰብን ግፍ ተሳልቀዋል። ለአሻባሪው መገለጫ የሌላቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ቡራኬ ሰጥተዋል። በማዕቀብ አስፈራርተውናል። ኢትዮጵያ አበቃላት ብለው የሽግግር መንግስት ሁሉ አቋቁመውልናል።

የሐሰት ፕሮፓጋንዳው በስመ ግብረሰናይ ተቋማት ጭምር የተደረገብን መልክና ዓይነት ብዙ ነው። በጫናዎች ውስጥ አልፈን ተከበበች ፣ ሠላሟን አጣች ፣ ዜጎቻችን ለቀዋት መውጣት አለባቸው የተባለችው መዲናችን አዲስ አበባ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ዲያስፖራ ልጆቿን እያስተናገደች ነው።

እጅ ሊጠመዝዝ ለሚሞክር ሁሉ እምቢተኝነታችን እንደ አድዋ ዘመን ለአፍሪካውያን ምሳሌ ብቻ ሳይሆን አርማም ሆነናል። #nomore ወይም በቃ የሚለው ንቅናቄ የኢትዮጵያ ብቻ መሆኑ እያበቃ ነው። የአህጉሪቱን ህዝቦች ቀስቅሶ በቃ እንዲሉ እያደረገ ነው። የአፍሪካ ልሳንና የጥቁሮች ኩራት የሆነችው ምድር በቃ ስትል የአህጉራችን ህዝቦች ቃሉን ማስተጋባት ከጀመሩ ውለው አድረዋል።

በህልውናው ዘመቻ እስከ መቀሌ የፅሞና ጊዜን ተከትሎ በተለያዩ የአማራ ክልሎች ግንባር የመገኘት ዕድል አግኝተናል። የሠራዊቱን አመራር አባላት የፀጥታ ሀይሎች ጥምረት በተለያዩ አደረጃጀቶች ለድጋፍ ግንባር ድረስ የሄዱትን ግለሰቦችን የመጠየቅ ዕድል ነበረን።

ኢትዮጵያን ለማዳን አርቲስቶች፣ የህክምና ባለሙያዎች፣ የዩኒቨርስቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የተቋምና የድርጅት አመራሮችና አባላት፣ በውጭና በውስጥ የሚገኙ ዜጎች ወዘተ በውጊያው ተሳትፎ ነበራቸው።የተደገሰልን ጥፋት ከፍተኛ ቢሆንም ይሄን መመከት ደግሞ በታሪካችን ከተከሰቱ ታላላቅ ድሎች ተርታ የሚመደብ ነው።

በርግጥ የድልን ግዙፍነት ለመረዳት የጁንታው የጥፋት ዝግጅት በህዝባችን እሴቶች ህይወትና ንብረት ላይ ያደረሰውን ጥፋት በጋሸናና ሐሙሲት ምሽጎች ላይ የተደረገውን ትንቅንቅና ጀግንነት የአፋር ምድር ላይ የተመዘገበውንና ደግሞ የተረጋገጠውን የህዝባችን ማንነት እንደተመለከተ ሰው ጎልቶ ላይታየን ይችላል።

ከዚህ በመነሳት አንድ ጥያቄ መጠየቅ ፈለግን። እሱም ኢትዮጵያን ያዳነው እንደ አድዋ የአልሸነፍ ባይነት ማሳያ የሆነው ቋምጠው የነበሩ የቅርብና የእሩቅ ጠላት ህልምን ቅዠት ያደረገው ይሄ ድል የማን ነው? የሚል ።

በፀሐፊው ግንዛቤ የድሉ ባለቤቶች አሉ። ያለቻቸውን አንዲት ዶሮ ለሠራዊቱ የለገሱት ሸጠው ከሚተዳደሩባት ቆሎ ላይ አብዛኛውን የሠፈሩትን ይመለከታል። ቤት ለኢትዮጵያውያን ምን ማለት እንደሆነ እናውቃለን። ቤት ለልጅና የልጅ ልጅ የሚቀመጥ ውርስ እንዲሁም የማንነት መገለጫ የሆነ ቅርስ ነው።ከነተረቱ “ኑሮ ኑሮ ከመሬት ዞሮ ዞሮ ከቤት “ይባል የለ። ይሄንን ለድርድር የማይቀርብ ሃብት ከኢትዮጵያ አይበልጥም ብለው ሸጠው ለዘመቻው የለገሱ ጡረተኛ እናት ባለድል ናቸው።

የተለየ ክፍያ ሳይጠይቁ በመንግስት ውክልና ሳይሰጣቸው ባገኙት የሚዲያ አማራጭ ተጠቅመው የሀገራቸውን እውነት የገለጡ፣ ሊያስቆማቸው የሚሞክረውን ሁሉ በድፍረት የተጋፈጡ የብዙሃንን አመለካከት የለውጡ በርካቶች ናቸው። እነዚህ ጊዜያቸውን፣ ዕውቀታቸውን እና ገንዘባቸውን ለሀገር ያዋሉ ፍትህ አልባውንና ሐሰተኛውን ዓለም ያጋለጡ እነሱ ባለድሎች ናቸው።

ከጉልት እስከ ትላልቅ ንግድ ላይ የተሠማሩ ከአንድ ብር እስከ ሚሊዮኖች የለገሱ ሳይጠሩ አሊያም በተጠሩበት ቦታ ፈጥነው የተገኙ እልፎች ናቸው። ብዕራቸውን አንስተው የደረሱ፣ የገጠሙ፣ ዜማ የቀመሩና ያዜሙ ባለድሎች ናቸው።

ኢትዮጵያዊነት ከነሙሉ ክብሩ እንዲነሳ፣ የላላውን ሀገራዊ አንድነት ወደ ጥንት ሥፍራው እንዲመለስ፣ እናጠፋዋለን ያሉት ማንነት የበለጠ እንዲታደስ የሠሩ እነዚህ ባለድሎች ናቸው። እነሱ ጋዜጠኞች ናቸው። እነሱ በማህበረሰብ አንቂነት ስምና ዝና ያላቸው ግለሰቦች ናቸው። እነሱ በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሠማሩ ምሁራንና የተግባቦት ባለሙያዎች ናቸው።

ደሃ አንድም እኛ በመረጥንለት አሻንጉሊት መንግስት ይመራል። አለበለዚያ በክንዳችን ይወገዳል። በምንም ተዓምር ከእኛ ጥቅምና ፍላጎት ውጭ አንዳች ስንዝር መጓዝ የለበትም የሚል ምዕራባዊ የሆነ ያልተፃፈ ህግ አለ። ይሄንን ህግ እንደ እነሱ በስውር ሳይሆን በግልፅ አይሆንም ያሉ ኢትዮጵያውያን በብዛት የታዩበት እና የተሳተፉበት ዘመቻ ነው።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ እና ሃብትና ንብረቴ ከኢትዮጵያ በታች ነው ያሉ ከሚጠበቅባቸው በላይ ገንዘባቸውን ለዘመቻው ያዋሉ፣ ግንባር ድረስ ተገኝተው ሠራዊቱን አይዞን አለንልህ ያሉ የታገሉ እና ያታገሉ ውለታቸው የማይረሳ በትውልድ ሁሉ የሚነሳ ባለድሎች ናቸው።

በውጭ ሀገራት እየኖሩ ጥረው ግረው ያፈሩትን ሃብት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው በመላክ አደባባይ ወጥተው ስለእውነት በመጮህ ያስተጋቡ አዲስ አበባ አደጋ ውስጥ ናት፤ በአስቸኳይ ዜጎቻችን መውጣት አለባቸው የሚል ውዥንብር ወቅት ከእናንተ ይልቅ በህዝብ የተመረጠውን መንግታችንን እናምናለን ከጎኑም እንሆናለን ብለው የጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ጥሪ ተቀብለው ዓለም እስኪደነቅ እና ጠላታችን እስኪሸማቀቅ በሚሊዮኖች ተጠራርተው ወደ ሀገራቸው የገቡ እነሱ ባለድሎች ናቸው።

በተፈጥሮ ሃብታችን እንዳንጠቀም ፣ የፀጥታ ጉዳይ ያልሆነውን የልማት ጉዳይ ወደ ፀጥቸው ምክር ቤት እያመጡ ኢ-ፍትሀዊ ውሳኔ ለማስወሰን ሲጥሩ ሐቅን ይዘው የሞገቱ ለእውነት በቆሙ ወዳጅ ሀገር ታግዘው በተደጋጋሚ የረቱ እነሱ ባለድል ካልሆኑ ማን ሊሆን ይችላል?

በዓለም ላይ ለእናት ከልጇ በላይ ምንም ስስት ነገር የለም። ትልቅ በጎ ምኞቷ የነገ ተስፋውን የማየት ጉጉቷ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። ይቺ እናት ልጄ ከሀገሬ አይበልጥም ብላ ከአንድም ሁለት ሦስትና አራት ልጆቿን መርቃ ሠራዊቱን እንዲቀላቀል ለፍትህና ለነፃነት እንዲታገል በድል እንዲመለስ ካልሆነም ደሙን ለእናት ሀገሩ እንዲያፈስ፤ ኢትዮጵያ ተሻግራ በትውልድ እንዲታዋስ ለመጪው ትውልድ ጀግንነት እንዲያወርስ የወሰነች እናት ድሏ የእሷ ነው።

ሻለቃ ፈይሳ ናኔቻ

Exit mobile version