Site icon ETHIO12.COM

ግማሽ ሚሊየን ብር በጥሬው ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ

መላኩ ሸዋረጋ የተባለው ተከሳሽ በገቢዎች ሚኒስቴር አዳማ ቅ/ፅ/ቤት የኦዲት ባለሙያ ሆኖ ሲሰራ አንድ ሚሊየን ብር በባንክ አካውንት እንዲገባለትና 5 መቶ ሺህ ብር ገንዘብ ሲቀበል የተገኘው ተከሳሽ በፈጸመው የሙስና ወንጀል በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ መወሰኑን የፍትህ ሚኒስቴር አሰታወቀ።

ተከሳሹ የስራ ኃላፊነቱን ተጠቅሞ ”ኽርበርግ ሮዝ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የተባለው ድርጅት የ2 ዓመት የንግድ ስራ ትርፍ ግብር ብር 66 ሚሊዮን 616 ሺህ 818 ብር አንዲከፍል ሲወሰንበት የድርጅቱ የአስተዳደር ሰራተኛ የሆነችው 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር በውሳኔው ላይ ለቅ/ፅ/ቤቱ ቅሬታ ታቀርባለች፡፡

ተከሳሹ በበኩሉ የቀረበውን ቅሬታ ውሳኔውን ዝቅተኛ በሆነ መልኩ መወሰን እንደሚቻልና ለዚህም አንድ ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ጉቦ ለመቀበል ተስማምቶ ግማሽ ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በሙስና ወንጀል በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዐቃቤ ህግ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 10(2) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበታል።

በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ በ1ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት የቀረበው ተከሳሽ መላኩ ሸዋረጋ የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ተከሳሽ በዐቃቤ ህግ ክስ ላይ የተጠቀሰውን የጉቦ መቀበል የሙስና ወንጀል አለመፈፀሙን ክዶ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ የሚያስረዱ 4 የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ የድርጊቱን መፈፀም በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሹም ክስና ማስረጃዎቹን ማስተባበል ባለመቻሉ ችሎቱ የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት ወንጀለኛዉ መላኩ ሸዋረጋ በፅኑ እሥራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኖበታል።

በጉቦ የተሰጠው ገንዘብ ለተበዳይ እንዲመለስ ዐቃቤ ህግ በጠየቀው መሰረት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ገንዘቡ ለተበዳይ እንዲመለስ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ በውሳኔው ላይ ይግባኝ ለመጠየቅ የሚያስችሉ ነጥቦች ላይ ለመወሰን እንዲያስችለው የፍርድ ቤቱን ሙሉ የውሳኔ ግልባጭ ጠይቆ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

Exit mobile version