Site icon ETHIO12.COM

“የትምህርት ጥራት ችግርን በመቅረፍ በህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያምን ዜጋ መፍጠር ይገባል”ቋሚ ኮሚቴው

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ሥምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የትምህርት ጥራት ችግርን በመቅረፍ በህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚያምን ፣ በጥሩ ሥነ-ምግባር የታነጸ፣ ተወዳዳሪ እና ሥራ ፈጣሪ ዜጋ መፍጠር ይገባል ሲል ገለጿል።

ይህ የተገለጸው ቋሚ ኮሚቴው የትምህርት ሚኒስቴርን የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ነጋሪ ሌንጮ(ዶ/ር) ብቁና ተወዳዳሪ፣ በስነ-ምግባር የተመሰገነ እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን የሚጠየፍ ትውልድ ከማፍራት አንፃር ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በጥናትና ምርምር የተገዛ እቅድ አዘጋጅቶ በትምህርት ተቋማት የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትንና አመራሮችን የሚያበቃ ስርዓት መዘርጋት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ።

የሀገሪቱን የወደፊት መጸዒ እድል መወሰን የሚችሉ ዜጎች የሚፈልቁባቸው የመንግሥት እና የግል የትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ ስርዓት ሊበጅላቸውም ይገባል ብለዋል ።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በቀጣይ በሁሉም ክልሎች በዓይነታቸው ልዩ የሆኑና የልህቀት ማዕከል የሚሆኑ 50 ትምህርት ቤቶች በሚገነቡበት ወቅት የቋንቋ ብዝሃነትን ማስተናገድ የሚችሉ እና አካታች እንዲሆኑ ከወዲሁ ሰፊ የሆና እንቅስቀሴ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ ብለዋል ።

በአጠቃላይ በትምህርት ዘርፉ ከቅድመ መደበኛ እሰከ አስራ ሁለተኛ ክፍል ያለውን የትምህርት ስርዓት ደረጃውን የጠበቀ ለማድረግ የተሄደበት ርቀት፣ የመምህራን የደረጃ እድገት የአፈጻጸም መመሪያና የደረጃ ምደባ አወሳሰን የማናበብ እና የማሻሻል ሥራ በማጠናቀቅ ለሲቪል ሰርቪስ ማቅረብ መቻሉ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአመራር ምልመላና ስምሪት ፍትሀዊ እንዲሆን የተዘረጋው የአሰራር ስርዓት ተግባራዊ እንዲሆን ለማስቻል የተደረገው ጥረት እንዲሁም ከሀብት ምንጭና አጠቃቀም አኳያ ነባሩን የድጎማ በጀት መመሪያን በማሻሻል በመጠለያ ጣቢያ ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለማካተት የተሰረው ስራ የሚበረታታ ነው ሲሉ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ ገልፀዋል ።

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሀገራችን የቀጣዩን ትውልድ ሞራል የሚያቀጭጩ የኩራጃ ልማዶችና የፈተናዎች መሰረቅ ተቋማዊ መሰረት ያለው በሚመስል መልኩ ፈተና ሆነዋል ያሉ ሲሆን ይህንንም ከምንጩ ለማድረቅ የትምህርት ስርዓቱን በቴክኖሎጂ ማስተሳሰር ቀደሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ሲሉ ገልፀዋል ።

በውይይቱም በአማራና በአፋር ክልል በአሸባሪዉ ኃይል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንዲሁም የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ተሳትፎ ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል ።

(ዜና ፓርላማ) ጥር 3ዐ/2014 ዓ.ም፤

Exit mobile version