Site icon ETHIO12.COM

ባህላዊ የእርቅና ሽምግልና ሥርዓቶቻችን ለአገራዊ መግባባት…


በኢትዮጵያ የሚገኙ ባህላዊ የእርቅና ሽምግልና ሥርዓቶች ለአገራዊ መግባባትና አንድነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሠራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የቋንቋና ባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ እንደ ገለጹት ፣ ለዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎችና ብሔሮች መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ መፍቻ ቁልፍ እየሆኑ የሚያገለግሉትን የባህላዊ እርቅና ሽምግልና ሥርዓቶቻችን ለአገራዊ መግባባትና አንድነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተሠራ ነው፡፡

አብሮነታችንን ለማስቀጠል ባህላዊ ስርዓቶችና እሴቶች ያላቸው ፋይዳም ከፍተኛ ነው ያሉት ወይዘሮ ወርቅነሽ ፣ በተቋሙም እነዚህ ውድ ሃብቶች በእቅድ ተይዘው እየተሠራባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት ለአገራዊ እርቅ ያለው ሚናን በመረዳት በየክልሎቹ ያሉ ግጭቶችና አለመግባባቶች በህሎቹን በሚያወቁ ሽማግሌዎች እንዲፈቱ ለማስቻል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓታችን እርቅን የሚያርዱት ያለ አድሎና ለእውነት ጥብቅና በመቆም በዳይና ተበዳይ በእኩል የሚተይበት በመሆኑ በሁሉም ወገን እኩል ተቀባይነት አላቸው፡፡

ስለዚህም ብሄራዊ ውይይቱ ውጤታማ እንዲሆን እነዚህን እሴቶች መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፤፤

ባህላዊ ስርዓቶችና እሴቶች አካባቢያዊ ግጭቶች ስር ሳይሰዱ በአጭር እንዲቀጩ ሲያደርጉ እንደኖሩ ሚኒስትሯ ገልጸው፣ የማሕበረሰባችን የዕለት ተዕለት የሰላም ኑሮ የተሳለጠ እንዲሆንና ለአገራዊ መግባባትና እርቅ ባህላዊ የሽምግልና ሥርዓታቶች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡

በየክልሎቹ ከሚኖሩት ሌሎች ብሔሮች ጋር ተቻችሎ፣ ተፈቃቅሮና ተዋዶ እንዲኖርም ባህላዊ የእርቅና ሽምግልና ሥርዓቶቻችን የማይተካ ሚና አላቸው ሲሉ ተናገረው፣ ሥርዓቶቹ በቀጣይ በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

ሥርዓቶቹን በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለአገራዊ ሰላምና አንድነት ማምጫ ቁልፍ መንገድ አድርገን ልንጠቀምባቸው ይገበናል ሲሉም መክረዋል፡፡

የሽምግልና ሥርዓታችን እንደ ሕዝብ በሥርዓት እንድንመራ ያደረገ እና በሕዝብ ዘንድም ሰፊ ክብርና ተቀባይነት ያለው ሥርዓት ነው ያሉት ሚኒስትር ድኤታዋ ሥርዓቱ ክብሩ እንዲመለስ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እነዚህ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁ በማድረግ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በመጤ ባህል ወረራና መሸርሸር ምክንያትም ባህላዊ እሴቶቻችን ተቀባይነት እንዳይኖራቸውና ችግሮችን እንዳይፈቱ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርም የስርዓቱን ክብር ለመመለስና አገራዊ ፋይዳውን ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

እንደ ወይዘሮ ወርቅነሽ ገለፃ፣ በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ውስንነቶች ተወግደው ሥርዓቱ ለአገራዊ አንድነቱ መምጣት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ለማድረግ እንደ አገር ወይይቶች እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም ክልሎች የስርዓቶቹን አተገባበርና ልምዳቸውን ለማስፋትና የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር እና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማስቻል እየተሠራ ነው፡፡ ሥራውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ባሳለፍናቸው ዓመታትም የሰላም እናቶችም ለአገራዊ መግባባቱ ሁሉም ከራሱ ክብር ይልቅ ቅድሚያ ለሰላምና ለአገር እንዲሰጥ በመማጸን ያበረከቱትን አገራዊ የሰላም ጥሪንም ሚኒስትር ደኤታዋ በተሞክሮነት አውስተዋል፡፡

እንደ አገር በዘላቂነት በባህላዊ መንገድ ሲሰራባቸው የኖሩትን ሥርዓቶቻችን ለአብሮነትና ለአገራዊ መግባባት ጉልህ ሚና እንዲያበረክቱ ለማድረግ ተጨማሪ ጥናቶችም እንደሚደረጉ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ባህላዊ ሥርዓቶቹን ለአገራዊ መግባባት ጥቅም እንዳይኖረው በማድረግ አብሮነታችን እንዲሸረሸር ፣ በትንሽ በትልቁ አንድንበጣበጥ ተደርጎ ቀድሞ መሰራቱን የገለጹት ወይዘሮ ወርቅነሽ፣ ኢትዮጵያዊያን በክፉም በደጉም አብረን መቆም እንዳንችል ተደርገን ነበርም ብለዋል፡፡

በየትኛውም አካባቢ ኢትዮጵያዊያን በብሔርና አካባቢያዊ አስተሳሰብ ተከበንና ታጥረን አብሮነታችን እንዲሸረሸርና የህዝቦች ባህላዊ የእርቅና ሽምግልና ሥርዓቶችን ፋይዳ እንዳይኖራቸው ተደርጎ ለዓመታት ተሰርቶብናል ብለዋል፡፡

ሙሳ ሙሐመድ

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version