Site icon ETHIO12.COM

ሁለት ህፃናትን ይዛ የተሰወረችው የቤት ሰራተኛ ከነግብረ-አበሮቿ በቁጥጥር ስር ዋለች

በኦሮሚያ ክልል በሰበታ ከተማ አስተዳደር በክፍለ ከተማ ሶስት ወለቴ ቀበሌ 03 በተለምዶ ስላሴ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ባለፈው ሰኞ ሁለት ህፃናትን ይዛ የተሰወረችው የቤት ሰራተኛ ከነግብረ-አበሮቿ በቁጥጥር ስር ውላለች።

በሰበታ ከተማ መስተዳድር የክፍለ ከተማ ሶስት ፖሊስ ጽ/ቤት ምርመራ ክፍል ኃላፊ ሳጅን ሀብታሙ ፀጋዬ እንደተናገሩት የቤት ሰራተኛዋ የ4 ዓመት ሴትና የ9 ወር ወንድ ህፃን ልጆችን ይዛ ነበር ባለፈው ሰኞ በባጃጅ ከቤት የጠፋችው።

የኦሮሚያ ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከህብረተሰቡ ጋር እጅና ጓንት በመሆን በሰሩት ስራ ግለሰቧን ጨምሮ አምስት ተጠርጣሪዎችን በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር አውለዋል።

ተጠርጣሪዋ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዘነበ ወርቅ አለርት ሆስፒታል አካባቢ ከአንድ ተባባሪዋ ጋር በአንድ ግለሰብ ቤት እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ስር መዋሏን ሳጅን ሀብታሙ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል።

የቤት ሰራተኛዋ አቶ ዘይኑ ሽኩር በተባሉ ግለሰብ ቤት በቤት ሰራተኝነት ተቀጥራ ስትሰራ ከሌሎች ሰዎች ጋር ለጥቅም በመመሳጠር የአሰሪዋን ልጆች ይዛ መሰወሯን እስካሁን በተደረገው ምርመራ መረጋገጡን ሳጅን ሀብታሙ ተናግረዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት ሁለቱም ህፃናት በተደረገላቸው የሕክምና ምርመራ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተረጋግጧል ብለዋል።

ህብረተሰቡ የቤት ሰራተኞችን ሲቀጥር ሕጋዊ ተያዥ (ዋስ) ያላቸውን ለይቶ መቅጠር እንዳለበትም ነው ሳጅን ሀብታሙ ያሳሰቡት።

አራቱ ተጠርጣሪዎች ከቤት ሰራተኛዋ ጋር ተመሳጥረው ሁለቱን ሕፃናት ያገቱት ከቤተሰባቸው የማስለቀቂያ ገንዘብ ለመጠየቅ እንደነበረ ነው ፖሊስ ያስታወቀው።

በላሉ ኢታላ EBC

Exit mobile version