Site icon ETHIO12.COM

የእሳት አደጋ በእንግዳ ማረፊያ ተኝተው የነበሩ የጥንዶችን ህይወት ቀጠፈ

በእንግዳ ማረፍያ (ፔኒስዮን) የደረሰው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ለጊዜው ማንነታቸው ያልታወቀ የጥንዶችን ህይወት ቀጥፏል፡፡

በአቃቂ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ዛምባባ ጠጅ ቤት አካባቢ በሚገኙ የንግድ ቤቶች ላይ የካቲት 9/2014 ሌሊት 8:42 ገደማ የተነሳው የእሳት አደጋ በአንድ የመኝታ ክፍል ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሁለት ሰዎችን ህይወት አሳጥቷል፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ በአደጋው ህይወታቸው ያለፈውን የሁለቱን ግለሰቦች ማንነት እንዲሁም የአደጋውን መነሻ ምክንያት ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡

ሁለቱ ግለሰቦች ህይወታቸው ያለፈው “በፔኒሲዮን” ወይንም የእንግዳ ማረፊያ ክፍሉ ላይ ድንገተኛ እሳቱ በመከሰቱ ነው፡፡

እሳት አደጋው አራት በሚሆኑ የንግድ ሱቆች፣ የሸቀጣሸቀጥ መደብር፣ ምግብ ቤት፣ ፀጉር ቤት፤እንዲሁም ግሮሰሪን ጨምሮ የሁለቱን ጥንዶች ህይወት ያሳጣው የመኝታ ክፍል (ፔኒሲዮን) ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡

በአደጋው ምክንያት በአንድ መኝታ ክፍል ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሁለት ጥንዶች ህይወት ከማለፉም በተጨማሪ በአደጋው የሶስት ሰዎች ህይወትን ማትረፍ የተቻለ ሲሆን ሰባት መቶ ሺ ብር የሚገመት ንብረት ሊወድም እንደቻለ ኢትዮ ኤፍኤም ሰምቷል፡፡

የእሳት አደጋውን ለመቆጣጠር ሶስት የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች የተሰማሩ ሲሆን ሰላሳ በሚሆኑ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ እሳቱን ለመቆጣጠር መቻሉንም አቶ ንጋቱ ነግረውናል፡፡

በተጨማሪም የካቲት 9 /2014 ዓ/ም ምሽት 11:50 በኮልፌ ቀራንዮ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አየር ጤና አካባቢ በመኖሪያ ቤት ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ከ አንድ መቶ ሺ በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ከ ሁለት መቶ ሺ በላይ ንብረት ደግሞ ማትረፍ መቻሉንም አቶ ንጋቱ ነግረውናል፡፡

በዚህኛው አደጋ የሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የነገሩን አቶ ንጋቱ ህብረተሰቡ እንዲሁም የንግድ ድርጅቶች ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት የሚሆኑ ነገሮች ላይ የተለየ ጥንቃቄን በማድረግ እራሳቸውንና ንብረታቸውን እንዲጠብቁ ጠይቀዋል፡፡

የውልሰው ገዝሙ – Ethio FM 107.8
የካቲት 10 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version