Site icon ETHIO12.COM

በሳኡዲ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማስመለስ የተቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ባዘጋጃቸው ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሃገር ቤት ለማስመለስ የተቋቋመው ፈፃሚ ብሄራዊ ኮሚቴ ባዘጋጃቸው ዕቅድ ዙሪያ ሁለተኛው ዙር ውይይት ተካሂዷል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት እና በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ፀሃፊነት የተዋቀረው በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት ለማስመለስ የተቋቋመው ፈፃሚ ብሄራዊ ኮሚቴ አስራ ስድስት መንግሰታዊ ተቋማትን በአባልነት ያቀፈ ነው።

ብሄራዊ ኮሚቴው ዛሬ በካሄደው ውይይት እንደተገለፀው በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያሉ ከ102ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎችን በአጭር ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ግብ ተቀምጦ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱኳን አያኖ ኮሚቴ ዜጎችን መመለስ ብቻ ሳይሆን ድርሻ ያላቸው አካላትን በማሳተፍ መልሶ እስከ ማቋቋም የሚደርስ ስራን ለመስራት ሰፊ እንቅስቃሴን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

ዜጎቻችን ያሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ጊዜ የማይሰጥ መሆኑን የጠቀሱ አምባሳደር ብርቱካን ወገኖቻችንን ለመታደግ ሁሉም አካላት የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስገንዝበዋል። አያይዘውም ዜጎቻችንን በተቻለ ፍጥነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ለውይይት የተዘጋጀውን የተግባር ዕቅድ ያቀረቡት የኮሚቴው አባል የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ መስፍን ገብረማሪያም እንዳሉት እቅዱ ዜጎቻችን የሚገኙበትን እና የሃገራችንን ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ አድርጎ ተዘጋጅቷል።

የተዘጋጀው ረቂቂቅ እቅድ ዜጎችን ለማስመለስ ከሚሰሩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አንስቶ ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በፌደራል እና በክልል ደረጃ የሚሰሩ ስራዎችን ይዟል።

የተመላሾችን መረጃ በቅድሚያ በተሟላ መልኩ አጠናቅሮ መያዝ መሰረታዊ ጉዳይ እንደሆነ በውውይቱ ተጠቅሷል።

ተመላሾች ከመጡ በኋላ በመቆያ ማዕከላት መጨናነቅ እንዳይፈጠር፣ መሰረታዊ አቅርቦቶችን በሚያስፈልገው መጠን ለማቅረብ እንዲሁም አስፈላጊ የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝ በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል።

ለእቅዱ መተግበሪያ የሚያስፈልገው በጀት ዙሪያም ግብዐት የሆኑ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ እና በጂዳ የኢፌዴሪ ቆንስል ጄነራል አምባሳደር አብዱ ያሲን እየተደረጉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በተመለከተ ለኮሚቴው አባላት ማብራሪያ ተሰጥተዋል።

የብሄራዊ ኮሚቴው አባል መስሪያ ቤት ተወካዮች የተወያዩበት ዕቅድ በቀጣይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሚመሩት “በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል መከላከል እና መቆጣጠር ብሄራዊ ኮሚቴ” ጸድቆ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።

ኮሚቴው አባላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የጤና ሚኒስቴር ፣ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ፣ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ የዳያስፓራ ኤጀንሲ፣ የፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን፣ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሰኝ ኩነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ የማህበረሰበሰ ጤና ኢንስቲትዩት ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ፣ የኢትዮጵያ የስደት እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አገልግልት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኤርፖርቶች ድርጅት፣ የትራንስፓርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መሆናቸውን የቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ዘግቧል።

Exit mobile version