ETHIO12.COM

አዲሱ አስደንጋጩ ብክለት

(ነጋሽ አበበ)

ከዛሬ ፕሎጊንጋችን ጋር አያይዤ አስደንጋጭ የጥናት ውጤቶችን በአጭሩ እነግራችኋለሁ። አንብባችሁ መልእክቱን በማጋራት (ገልብጣችሁ በመለጠፍ ወይም ‘ሼር’ በማድረግ) እንድትተባበሩ በአክብሮት እጠይቃለሁ !

ፕላስቲክ ከዕለት ሕይወታችን ጋር በእጅጉ ተቆራኝቷል። ከተጠቀምን በኋላ በአግባቡ የማስወገድ ልምዳችን ወደ ምንም የተጠጋ በመሆኑ፣ ሀገር ምድሩ በፕላስቲክ ቆሻሻዎች ተሸፍኗል። ስለ ጉዳቱ እምብዛም አልታሰበበትም።

ፕላስቲክ በብዛት መጠቀም ከጀመርን በኋላ በተለይም የደቃቅ ፕላስቲኮች ብክለት (microplastic contamination) በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፍ አዲስ አደጋ ደቅኗል። ‘ማይክሮፕላስቲክ’ የሚባሉት መጠናቸው ከ 5 ሚሊ ሜትር በታች የሆኑ የፕላስቲክ ድቃቂዎችን (ብናኞች) ነው። ባለፉት 3 ዓመታት በተሰሩ ጥናቶች፣ ፕላስቲክ ብናኞች በመላው ዓለም ከጥልቅ እና ሰፊ ውቂያኖሶች

እስከ’ምንተነፍሰው አየር እና ምድር ላይ በከፍተኛ መጠን እንደሚገኙ በሳይንቲስቶች ተረጋግጧል። ፕላስቲኮች ተሰባብረው ወደ ብናኝ ደቃቅነት ሲለወጡ፣ በጣም በቀላሉ በንፋስ ተሸካሚነት የትም ይሄዳሉ። ሌላው ቀርቶ ሰዎች የማይኖሩባቸው የምድር ጥጎች – በተራሮች እና የዓለማችን ሰሜንና ደቡብ ዋልታ የበረዶዎች ጭምር – በብዛት ተገኝተዋል። ብናኝ ፕላስቲኮቹ የምንተነፍሰው አየር ውስጥ፣ የምንመገባቸው ምግቦች እና በእንስሳት እና ሰዎች ሰውነት ውስጥ በከፍተኛ መጠን እየገቡ ነው።

የፕላስቲክ ቆሻሻ በብዛት በሚገኙባቸው አከባቢዎች በአንድ ሜትር ስኩዌር ውስጥ እስከ 1.9 ሚሊዮን ፕላስቲክ ብናኞች ሊገኙ ይችላሉ።

ቀደም ሲል በተሰሩ ጥናቶ፣ በ5.25 ትሪሊዮን የፕላስቲክ ብጥስጣሾች በውቂያኖሶች ላይ ይንሳፈፋሉ ተብሏል። ከፈረንጆቹ 2020 ወዲህ የተሰሩ ጥናቶች ግን፣ መጠናቸው ቀደም ሲል ከተገመተው በላይ ከ 3 እስከ 10 እጥፍ ሊደርስ ይችላል ይላሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ የተረጋገጠው አስደንጋጩ ነገር፣ ፕላስቲኮቹ ወደ ብናኝ ደቃቅነት ከተለወጡ በኋላ ወደ አየር የመግባታቸው ነገር ነው። በየዓመቱ 130,000 ቶን ፕላስቲኮች በባህር እና ውቂያኖሶች ትንፋሽ እየተገፉ ወደ አትሞስፌር ይገባሉ። ውሀዎች ሲተፏቸው እኛ ተቀብለን እንተነፍሳቸዋለን። ምን ማለት ነው? ለምሳሌ ከህንድ ውቂያኖስ ዝናብ እናገኛለን። ልክ እንደዚሁ ከህንድ ውቂያኖስ የተነሳ የፕላስቲክ ብናኝም ለመተንፈስ እንገደዳለን።

ሳይንቲስቶቹ በምርምር ያረጋገጠት ሌላው እጅግ በጣም አስደንጋጩ ነገር፣ የፕላስቲክ ብናኞች በመጠጥ ውሀ፣ የምንመገባቸው ፍራፍሬዎች እና አትክልቶች ውስጥ መገኘት ነው። በአጭር ቋንቋ እንጦጦ ላይ የሚጣሉ ፕላስቲኮች ወደ ብናኝነት ሲለወጡ በውሀ እና ንፋስ ግፊት አቃቂ ደርሰው በሽንኩርት፣ ቲማቲም እና ሌሎች አትክልቶች ውስጥ ተመለስው ይመጣሉ። እኛ የምናነሳቸው ፕላስቲኮች ከዓመታት በኋላ በወጥ፣ አትክልት እና ሌላው ቀርቶ በጥሬ ስጋ ልንመገባቸው የምንችላቸውን ማለትም ነው።

የፕላስቲክ ብናኞች ጤና ጠንቅነት?

ብናኞቹ በሰው ጤና ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ይቅርና አየር፣ ውሀ እና ምግባችን ውስጥም በዚህ ደረጃ መገኘታቸው የተረጋገጠው ባለፉት ሶስት ዓመታት ነው። የተለያዩ ነባር ጥናቶች ማይክሮፕላስቲኮች በሰዎች እና እንስሳት ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ግን በመጠኑም ቢሆን ለይተዋል።

በሳይንቲስቶቹ ግምት መሰረት፣ በአንድ ቀን ብቻ ከ 100’ዎች እስከ 100,000 የፕላስቲክ ብናኝ ወደ አካላችን በትንፋሽ ከአየር እና በምግባችን በኩል ወደ አካላችን ይገባል። ሌላው ይቅርና የምንለብሳቸው ‘ሲንቴቲክ’ ጨርቆች እንኳን የማይክሮፕላስቲክ ምንጮች እንደሆኑ ተረጋግጧል። በአንድ አንድ አከባቢዎችማ ‘ሴንቴቲክ’ ጨርቆች ዋነኛ የአየር ፕላስቲክ ብናኞች (airborne microplastics) ምንጭ ናቸው።

እስከ አሁን ድረስ በሰዎች ህዋሳት (human cells ans tissue) እና እንስሳት ላይ በተሰሩ ጥቂት ምርምሮች፣ ብናኝ ፕላስቲኮች በእንስሳት እና ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትሉ ተፅፏል። ቀዳሚ ጉዳታቸው ሳንባ ላይ ነው። ብናኝ ፕላስቲኮች ሳንባን ‘ኢሪቴት’ በማድረግ ለካንሰር ተጋላጭ ሊያደርጉ ይችላሉ። ፕላስቲክ ብናኞች በራሳቸው ከሚያደርሱት ጉዳት በተጨማሪ፣ ከሌሎች ደቃቅ ኬሚካሎችን እና ማይክሮኦርጋኒዝሞችን አጣብቀው የመያዝ ባህሪ ስላላቸው፣ ከእነሱ ውጪም ለሌሎች ኬሚካሎች እና ጎጂ ማይክሮኦርጋኒዝስ (ባክቴሪያ ለአብነት) አማካኝነት የጤና ጠንቅ ይሆናሉ። ደቃቅ ፕላስቲኮች የሜታቦሊዝምን ይረብሻሉ። በዚህ ምክንያት ከጨጓራ ጋር ለተያያዙ ልዩ ልዩ የጤና እክሎች የመዳረግ ዕድላቸው ሰፊ ነው። ብናኞቹ የኢንዶክሪን ስርዓት በማስተጓጎል ለከፍተኛ የክብደት መጨመር መንስኤ ይሆናሉ።

“Research has shown the potentiality for metabolic disturbance, neurotoxicity as well as carcinogenic effects. It has been shown that microplastics can act as endocrine disruptors, thus interfering with normal hormone function and potentially causing weight gain.”

አንድ አንድ የፕላስቲክ ብናኞች በተለይ የህፃናትን ጤናማ የአንጎል እድገት ሊጎዱ (can affect normal brain development in children) ይችላሉ።

ዛሬ

የዛሬ Plogging-Ethiopia ውሎችን 28 ሰዎች ተሳትፈዋል። 17 ኪሜ Entoto Natural Park ውስጥ ተጉዘን 23 ኪሎ ፕላስቲክ ቆሻሻ አንስተናል። በሰራሁት መጠነኛ ስሌት 23 ኪሎ ፕላስቲክ 5,750,000 ሚሊ ሜትር ይረዝማል። ምን ማለት ነው? በዛሬ ስራችን ብቻ ወደፊት በአየር እና ምግብ በኩል የሰው ገላ ወሰጥ ሊገቡ የሚችሉ ከ 5 ሚሊዮን በላይ ብናኝ ፕላስቲኮችን አስወግደናል! ፕሎጊንግ ከጀመርን ወዲህ ስለ ስራችን የበዛ ፋይዳ እንደ ዛሬ ተረድቼ አላውቅም! መጠነኛ ኩራት እየተሰማኝ አይደለም ብላችሁም እንዳታምኑኝ ?!

መውጫ

የፕላስቲክ ቆሻሻ መዘዙ እጅግ ብዙ ነው። እኛ ጋር ከተማ እና አውራ ጎዳናዎችን አጣቧል። በጊዜ መላ ልናበጅለት ይገባል! ጎረቤት ኬንያዎች ፕላስቲክ ካገዱ ቆዩ። ከሁለት ዓመት በፊት ፓርላማ እየረቀቀ የሚገኝ ህግ አለ የሚል ነገር ተሰምቶ ነበር። በተጨባጭ የታየ ነገር ግን የለም። አበቃሁ ! ሀሳብ ስጡበት !🙏

Exit mobile version