ETHIO12.COM

ምርት በህገ ወጥ መንገድ ባከማቹ 17 ስግብግብ የንግድ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ ተወሰደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትቱ ፍትሀዊ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ በማድረግ የንግዱ ማህበረሰብ እና መንግስት ህብረተሰቡ ከንግዱ ሥርዓት የሚጠብቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሕግና የአሠራር ሂደቶችን በመከተል የከተማችን የመሰረታዊ ፍጆታ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት እየሰራ ይገኛል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በከተማችን ለሚገኙ 148 ሽማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የተዘዋዋሪ ብድር በመስጠት አስቀድሞ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርት አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በማድረግ ሸማቹ ማህበረሰብ በኑሮ ውድነት እንዳይማረር ለማድረግ የመሰረታዊ ፍጆታ ምርት በማቅረብ ገበያውን የማረጋጋት ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ14 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ170 ሺ ኩንታል በላይ ስንዴ እና ከ717 ሺ ኩንታል በላይ ስኳር በማቅረብ በሽማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለሸማቹ ማህበረሰብ እንዲሰራጭም ተደርጓል፡፡

በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በኩል ከሚከፋፈለው መሰረታዊ ፍጆታ በተጨማሪ ሸማቹና አምራቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን ዕድል ለመፍጠር የሚያስችል የእሁድ ገበያ (Sunday market) በከተማችን በተመረጡ ቦታዎች ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ የእሁድ ገበያ ትኩስ የእርሻ ምርቶችን ለሸማቹ ለማቅረብ ከማስቻሉም በላይ የንግድ ሰንሰለቱን በማሳጠር የዋጋ ንሩቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡ እስካሁን ድረስ ለ19 ተከታታይ ሳምንታት የእሁድ ገበያ የተካሔደ ሲሆን ከ116 ሚሊዮን ብር በላይ ግብይትም ተፈጽሟል፡፡

ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ለሸገር ዳቦ ከ618 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ የተደረገ ሲሆን በተለያየ ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የሸገር ዳቦ ምርት በከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ስራ እንዲጀምር ተደርጓል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በንግድ ስርአቱ ላይ የሚታዩ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለማረም የተለያዩ ሕጋዊ እርምጃዎችም ተወስደዋል፡፡ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምርት በመጋዝን በህገ ወጥ በማከማቸት ያለአግባብ በአቋራጭ መበልፀግ በሚፈልጉ 17 ስግብግብ የንግድ ድርጅቶች ላይም ህጋዊ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

ሆኖም ከዚህ ድርጊታቸው መማር ያልቻሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ የዓለም የነዳጅ ዋጋን ጭማሪ ምክንያት በማድረግ የፍጆታ ምርቶችን በመጋዝን በማከማቸትና በመሰወር የዘይት አቅርቦት እጥረት እንዳለ እና የዋጋ ንረት እንደተፈጠረ አድርጎ አሉባልታ በማሰራጨት በአንድ በኩል በአቋራጭ ሃብት ለመሰብሰብና ለመበልጸግ በሌላ መልኩ ለድብቅ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ለማድረግ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ሲፈጽሙ ተስተውሏል፡፡

ከተማ አስተዳደሩም ይህን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ባጭር ጊዜ ውስጥ ለማስቆም ግብረ ሃይል በማቋቋም በተደረገው የክትትልና የቁጥጥር ስራ በከተማችን ከ454 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ በመገኘቱ ምርቱን ለከተማችን ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሰራጭ በማድርግ ህጋዊ እርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን ከዚህ ድርጊታቸው በማይቆጠቡ አቅራቢ ድርጅቶች ላይ የተጀመረውን ህግ የማስከበር እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎንም ከዘይት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች ግዢ በመፈጸም እንዲሁም በህገ ወጥ ክምችት የተገኘውንም ለህብረተሰቡ በማከፋፈል እስካሁን ከ2 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለሸማቹ እንዲሰራጭ የተደረገ ሲሆን በቂ የዘይት ምርት በማቅረብ የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለማረጋጋት ከኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ ከፌቤላ እና የሸሙ ድርጅቶች ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር በላይ የዘይት ምርት እንዲቀርብ ለማድረግ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ስጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሆን ብለው የዘይት ምርት ከገበያው እንዲጠፋ በማድረግ ህብረተሰቡን ለኑሮ ውድነት የሚዳርጉ ድርጊት ውስጥ በተገኙ ነጋዴዎች ላይ የሚወስደውን ህጋዊ እርምጃ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

በተመሳሳይ ለህገ ወጥ የምርት እንቅስቃሴ ተባባሪ የሆኑ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ የንግድ ስራ ባለሙያዎች እና ሰራተኞች ላይ አስተዳደሪዊ እርምጃዎችን ከተማ አስተዳደሩ የሚወስድ ይሆናል፡፡

እነዚህ ህገ ወጥ ነጋዴዎች የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶችን በማከማቸትና የዋጋ ንረት እንዲፈጠር በማድረግ የከተማችን ማህበረሰብ በኑሮ ውድነት እንዲማረርና በምስቅልቅል ህይወት ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ የማጭበርበር እና የስርቆት ወንጀሉን የሚፈጽሙት በማህበረሳባችን ላይ በመሆኑ እና ወንጀሉን ከፈጸሙ በኃላም የሚደበቁት በራሱ በማህበረሰቡ ጓዳ በመሆኑ የከተማችን ማህበረሰብ የከተማ አስተዳደሩ ህግን ለማስከበር በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ እነዚህን ወንጀለኞች በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የከተማችን ማህበረስብ አጠራጣሪ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሲያዩ በነጻ የስልክ መስመር 8588 መጠቆም ይቻላል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ኮሙንኬሽን ቢሮ

አዲስ አበባ

Exit mobile version