Site icon ETHIO12.COM

ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ መግላጫ

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መጋቢት 20 ቀን 2014 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ቆርኬ/አውራ ጎዳና በሚባለው ልዩ ሥፍራ በምንጃር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች በጉዞ ላይ በነበሩት የህዝብ ሚሊሻና የፌዴራል ፖሊስ ላይ ባደረሱት ዘግናኝ ጥቃት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለጸ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ዘመዶቻቸው በሙሉ መጽጽናናትን ይመኛል፡፡

ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን ለማጠናከርና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ላይ በምንገኝበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ዉስጥ ይህን መሰል ዘግናኝ ድርጊት መፈጸሙ የጽንፈኞቸን እኩይ ዓላማና ተግባር ይበልጥ ያጋለጠ ነዉ፡፡

የነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች እኩይ ተግባርና ሴራ የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ዘላቂ አብሮነትና ሁለንተናዊ ብልጽግና ጉዞን ለማደናቀፍ የተወጠነ የጥፋት ዕቅድ አካል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

እነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች የኅብረ-ብሔራዊ አንድነትና የህዝቦች አብሮነት ጸር መሆናቸዉን በቅጡ ስለምንረዳ አምርረን የምንታገላቸውና ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጋር በመተባበር በህግ ፊት አቅርበን ተገቢና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማድረግ በቁርጠኝነት እንሠራለን፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን ጥቃቱ በደረሰበት ቦታ ላይ ተገቢውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ህግ ፊት ለማቅረብ እየተሠራ መሆኑን እየገለጽን፣ መላው ህዝብ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

Exit mobile version