Site icon ETHIO12.COM

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ወጪንግድ ከ894 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቡና ወጪ ንግድ ከ894 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ኡመር ዛሬ በሰጡት መግለጫ ÷ ባለስልጣኑ ከቡና ምርት ጀምሮ እስከ ኤክስፖርት ድረስ የተቀናጀ የቁጥጥር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

በተያዘው ዓመት ከ210 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጪ መላኩን ገልፀው ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ43 ነጥብ 66 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተናግረዋል።

በዚህም ከ894 ሚልየን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሪ መገኘቱንና ገቢው ከተያዘው እቅድ አንጻር 133 በመቶ አፈጻጸም እንደተመዘገበበት ገልፀዋል።

ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 74 ነጥብ 52 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረው በቀጣይም ባለስልጣኑ ገቢውን ወደ ቢሊየን ዶላር ለማሳደግ እንደሚተጋ ጠቁመዋል።

የምርት ጥራትን ማሳደግ፣ ግብይትን ማዘመን እና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስርዓቶች መዘርጋታቸው ለዕቅዱ መሳካት ወሳኝ ሚና ማበርከታቸውንም ነው የገለጹት፡፡

ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስርዓቱ የሚመራበት ሶፍት ዌር በማበልጸግ ተግባራዊ ማድረጉም ለዕቅዱ ስኬት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ እና በመጋዘን ተከማችተው በተገኙ እንዲሁም የምርት ግብይት በተላለፉ አካላት ላይ በተወሰደ እርምጃ ከ83 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም መጠቆማቸውን ከባለሥልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ FBC

Exit mobile version