Site icon ETHIO12.COM

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተሳሳተ መረጃ ስሜ ጠፍቷል ሲል ማብራሪያ እንዲሰጠው ቢቢሲን ጠየቀ

በመማር ማስተማር፣ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እና በጥናትና ምርምር አንጋፋ ከሚባሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ነው-ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፡፡ ከመማር ማስተማር ሥራው ጎን ለጎንም በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላበረከተው አስተዋጽኦ “የሰላም ዩኒቨርሲቲ” በሚል መጠሪያ ይታወቃል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግንቦት 1/2014 ዓ.ም ተቀማጭነቱን ኬኒያ ናይሮቢ ላደረገው ብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) በጻፈው የቅሬታ ደብዳቤ ቢቢሲ በተዛባ መረጃ የዩኒቨርሲቲውን ዝና እና መልካም ስም አጉድፏል ብሏል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንዳስታወቀው ቢቢሲ ሚያዚያ 29/2014 ዓ.ም (ግንቦት 7/2022) “በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ የአማራ ሚሊሻ የትግራይ ብሔር ተወላጆችን እንደጨፈጨፈ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን አረጋግጧል”በማለት በድረ ገጹ ያወጣው ዘገባ ፍጹም የተሳሳተ እና መሠረተ ቢስ ነው፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይኽንን መሰል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋም የማይመጥን መሠረተ ቢስ ስም ማጥፋት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይቃወማል ያለው ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ ውስጥ በሥራዎቻቸው መልካም ስም እና ዝናን ካተረፉ የምርምር ተቋማት መካከል አንዱ ነው ብሏል፡፡

እንደማንኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ዩኒቨርሲቲው ያደረገው ነገር ቢኖር ሕዝብን ሊያስተምሩ እና ለሕዝብ መድረስ ያለባቸውን ያልተገለጡ ሐቆች የምርምርን መሠረታዊ መርህ በጠበቀ መልኩ አጥንቶ ለሕዝብ ማቅረብ መኾኑን ገልጿል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተሰጠው ተቋማዊ ኃላፊነት እና ግዴታ መሠረት የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ላለፉት በርካታ ዓመታት በወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ በመረጃ አጥንቶ አቅርቧል፡፡

የሰብዓዊ መብት ድርጅት እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምርምር መሠረታዊ ሂደትን በተከተለ መልኩ ባደረገው ጥናት በርካታ አማራዎች በሽብር ቡድኑ መጨፍጨፋቸውን አረጋግጧል ብሏል፡፡

የጥናት ቡድኑም ሚያዚያ 7/2022 የጥናት ውጤቱን አስመልክቶ ለብዙኀን መገናኛ ተቋማት ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱንም አስታውሷል፡፡

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የዳበረ ልምድ እና ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት ካለው ቢቢሲ ይኽን መሰል መረጃ አልባ እና የሐሰት ዘገባ መስማቱ እንዳሳዘነውም ገልጿል፡፡

የጥናት ቡድኑ ዓላማ በወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት አካባቢዎች ለዘመናት የተደረገውን የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ መርምሮ ማቅረብ መኾኑን ጠቅሷል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በቅሬታው እንዳለው ይህን መሰል የተሳሳተ ዘገባ የሚሠራው የሽብር ቡድኑን የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ለማገዝ፣ የጥናቱን ተዓማኒነት ጥርጣሬ ላይ ለመጣል፣ የዩኒቨርሲቲውን እና ሙያተኞቹን መልካም ስም ለማጠልሽት ታስቦ ነው፡፡ ዘገባው የጋዜጠኝነትን ሙያዊ መርህ የጣሰ እና የቢቢሲን የአሠራር መመሪያ ያልተከተለ ነው ያለው ዩኒቨርሲቲው ዘገባው ካለው ነባራዊ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የአካዳሚክ ነጻነትን የሚጋፋ መኾኑንም ጠቁሟል፡፡

ቢቢሲ ዘገባውን በተገቢው መንገድ በማጣራት እርምጃ እንዲወስድ እና እንዲያሳውቀው ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል፡፡

በታዘብ አራጋው – (አሚኮ)

Exit mobile version