Site icon ETHIO12.COM

የደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና ገንዘብ ተቀጣ

የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ በ15 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ ተወሰነበት

በሃሰት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት ሃሰተኛ ዲጂታል መታወቂያ እያሳየ የተለያዩ ወንጀሎችን ሲፈፅም የነበረው ተከሳሽ በ15 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት አንዲቀጣ ተወስኖበታል ።

የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ሙስና ወንጀል ችሎት ነው ።

ስንታየሁ ቤርጉ የተባለው ተከሳሽ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 19/2013 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው ወንጀሎችን የፈጸማቸው።

ተከሳሹ በቦሌ ክፍለ ከተማ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ መኖርያ ቤትን ብርበራ በሚያደርጉበት ወቅት በቦታው ተገኝቶ አብሮ ሁኔታውን ከተከታተለ በኋላ ተጠርጣሪው ሲታሰር በመመልከቱ ጉዳዩን ለእኔ ተውት እኔ የብሄራዊ መረጃና ደህነት ሰራተኛ ነኝ በማለት በሀሰት የተዘጋጀ ዲጂታል መታወቂያ በማሳየት አስፈታላችኋለው፤ ለዚሁም 2‚000‚000‚00 ( ሁለት ሚሊየን ብር ) ትከፍላላችሁ በማለት የጠየቀ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ ልዩ ቦታው ”መሪ“ ከሚባለው አካባቢ በሚገኘው ተክለ ብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ጊቢ ውስጥ በመገኘት የድርጅቱ ማሽኖች ለምርመራ ስለሚፈለጉ ወደ ሌላ ቦታ እንወስዳቸዋለን ብሎ ካስፈራራ በኋላ ማሽኖቹ ከድርጅቱ እንዳይወጡ ከፈለጋችሁ ግን መግባባት እንችላለን በማለት 500‚000 (አምስት መቶ ሺ) ብር የተቀበለ ሲሆን ተከሳሽ በፈፀማቸው ወንጀሎች በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ክስ እንደተመሰረተበት ይታወሳል ።

ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ ” እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ”ሲል ቃሉን ሰቷል ።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር የምስክሮች ቃል እና የሰነድ ማስረጃዎች በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ እና ተከሳሽ ዐቃቤ ህግ ያቀረበበትን ክስ መከላከልና ማስተባበል ባለመቻሉ ግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ሙስና ወንጀል ችሎት በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፏል ።

በዚህም መሰረት ተከሳሽ ያቀረባቸው የተለያዩ የቅጣት ማቅለያዎች በማስረጃ ያልተረጋገጡ በመሆኑ ውድቅ ያደረገበት ፍርድ ቤቱ ተከሳሽን ያርማል መሰል አጥፊዎችን ያስተምራል ሲል በ15 ዓመት ፅኑ እስራትና በ20 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ወስኗል።

በወንድም ሰማኽኝ attorney general

Exit mobile version