ETHIO12.COM

ቱርክና ኢትዮጵያ በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈረሙ

በቱርክ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈረሙ፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት (Agreement on Extradition) እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ለማድረግ (Agreement on Mutual legal Assistance in criminal matters) የሚያስችሉ ሁለት ስምምነቶች በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደዉ እና በቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በክቡር ሚስተር ያኩፕ ሞጉል (Yakup Moğul) አማካኝነት ተፈርሟል።

በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ትብብር ለማድረግ በሀገራችን እና በቱርክ መንግስት መካከል ስምምነት ለመፈራረም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የፍትህ ሚኒስቴር የመንግስት ሕግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በክቡር አቶ አለምአንተ አግደዉ የተመራ የልዑካን ቡድን እ.ኤ.አ. ሜይ 9/2022 አንካራ ቱርክ የገባ ሲሆን እ.ኤ.አ. ሜይ 10/2022 የልዑካን ቡድኑ በቱርክ የፍትህ ሚኒስቴር በመገኘት በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡

በዉይይቱም የቱርክ ሪፐብሊክ መንግስት የፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ክቡር ያኩፕ ሞጉል (Yakup Moğul) በቱርክና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መሆኑ እና በፍትህ እና በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ትብብሮች አስፈላጊና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸዉ መሆኑን ፤ በሁለቱ አገራት መካከል የተለያዩ ትብብሮች ሲደረጉ የቆየ ቢሆንም በሁለቱ ሀገራት በዚህ ደረጃ የፍትህ ትብብሮች ሰነድ መፈረማቸዉ ግንኙነቱን የበለጠ ሕጋዊ መሰረት የሚሰጠዉ መሆኑን ጠቅሰዉ በሁለቱ አገራት የሚፈለጉ ወንጀለኞችም በማንኛዉም ጊዜ በፍጥነት ተላልፈው መሰጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

ክቡር አቶ አለምአንተ አግደዉ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ከብዙ ሀገራት ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደምትሰራ፣ ከቱርክ መንግስት ጋር በወንጀል ጉዳዮች ላይ የሚደረገው የጋራ ስምምነትም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግረዉ መሆኑን፣ ቱርክ በተለያዩ መንገዶች የኢትዮጵያ አጋር መሆኗን ማሳየቷን፤ በአቅም ግንባታ ዙሪያ ከቱርክ መንግስት ጋር በትብብር ለመስራት ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን፤ ቱርክ በሽብርተኛ ቡድኖች የደረሰባትን አሳዛኝ ጉዳቶች ኢትዮጵያ እንደምትገነዘብና በዚህም ከቱርክ መንግስትና ህዝብ ጎን እንደምትቆም፣ ሀገራችን ሽብርተኞችን እንደምታወግዝና ሽብርተኝነት እንዳይስፋፋ ጠንክራ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይ በጋራ በቅርበት በመስራት ትብብሩን በማጠናከር ረገድ ትኩረት እንደሚሰጥ የሁለቱም ሀገራት ተወካዮች ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም በሁለቱ ሀገራት መካከል በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠት (Agreement on Extradition) እና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የህግ ትብብር ለማድረግ (Agreement on Mutual legal Assistance in criminal matters) የሚያስችሉ ሁለት ስምምነቶች በፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደዉ እና በቱርክ ፍትህ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር በክቡር ሚስተር ያኩፕ ሞጉል (Yakup Moğul) አማካኝነት ተፈርሟል።

Via attorney general

Exit mobile version