Site icon ETHIO12.COM

በዳኝነት ስርአቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል ስትራቴጂ ይፋ ሆነ

Okay የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት ስርአቱ ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያሰችል ስትራቴጂ ይፋ አደረገ።

የስትራቴጂው ፋይዳ እና በቀጣይ አተገባበሩ ዙሪያ በማተኮር ከዳኞችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፤ በፍትህ አሰጣጥ ሂደት የትውውቅ አሰራር፣ ጉቦና የመሳሰሉት ብልሹ አሰራሮች ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የዳኞች አገልግሎት አሰጣጥ ከሙስና ተግባር የፀዳ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ አንዳንድ ዳኞች፣ የጉባኤ ተሿሚዎችና የፍርድ ቤት ሰራተኞች በሙስና ፍትሕ እንዲዛባ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዳኝነት ሥርዓቱ ውስጥ የሚፈጸም ሙስና በተገልጋዩ እና ፍትሕ ፈላጊው ላይ ተስፋ እያሳጣ ስለመሆኑ አንስተዋል።

የሙስና ወንጀል ለሕግ የበላይነት እንከን ሲሆን ለወንጀል መበራከትም ምክንያት ይሆናል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቷ።

በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ሕዝቡ በዳኝነት አካሉ ላይ ያለው አመኔታ 75 በመቶ ሲሆን የተገልጋዮችን ጉዳይ ጨርሶ የመመለስ 87 በመቶ ሆኗል።

በመሆኑም በዳኝነት ላይ የሚታዩ የሙስና ተግባራትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስትራቴጂ መቅረጽ አስፈልጓል ነው ያሉት።

በስትራቴጂው የሙስና ተግባር በፍርድ ቤቶች ያለበት ደረጃ፣ ለሙስና በር ሊከፍቱ የሚችሉ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጦችና መገለጫዎች፣ ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ የሚውሉ ስልቶች መካተታቸውን አብራርተዋል።

የዳኝነት አገልግሎቱ ከሙስና የፀዳ እንዲሆን የዳኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የድርሻቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

የዳኝነት አካሉን ተቋማዊ ነጻነት ለማረጋገጥና የሕዝብ አለኝታ የሆነ ፍርድ ቤት ለመገንባት ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።

የህግ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅድ በማውጣት፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ በማጽደቅ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጡ ቀልጣፋ፣ ተደራሽ፣ ፍትሃዊና ጥራት ያለው እንዲሆን ለማስቻል ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ዳኞች የዳኝነት ሙያ ከፍተኛ ስነ-ምግባርን መላበስ እና ለማኅበረሰቡም ተምሳሌት መሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ ለዚህ ልንዘጋጅ ይገባል ብለዋል።

ራስን ከማይገባ ፍላጎት በማራቅ ሙያው የሚጠይቀውን ቁጥብነትና ስነ-ምግባር በመላበስ የሕዝብ አመኔታ ያለው ጠንካራ የዳኝነት ተቋም መገንባት አስፈላጊ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለዚህም ስትራቴጂው ከሙስና የፀዳ የስነ-ምግባር እሴት የሚንጸባረቅበት የዳኝነት አካል ለመገንባት በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል።

ለስትራቴጂው ትግበራ አጋዥነት በሚቀጥሉት ሳምንታት በዳኞች ውይይት የሚደረግ እና ግብአቶች የሚሰበሰቡ ሲሆን በቀጣይም የስትራቴጂው ትግበራ የሚከናወን ይሆናል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version