Site icon ETHIO12.COM

በሳዑዲና ኢራን በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል

በሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን በሞት ፍርድ የሞት ቅጣት የሚፈጽምባቸው ሰዎች ቁጥር እአአ 2021 ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ በ18 አገራት 579 የሞት ቅጣቶች ተግባራዊ ሆነዋል ያለ ሲሆን፤ ይህም ከቀደመው ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የ20 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ብሏል።

ኢራን 314 ሰዎችን በሞት በመቅጣት ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበባት አገር ሆናለች። በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ደግሞ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ 65 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አምነስቲ በዚህ ሪፖርቱ ላይ ቻይና አለመካተቷን ገልጿል። ቻይና የሞት ፍርድን አገራዊ ምስጢር አድርጋ ስለምትይዝ በአገሪቱ በሞት የተቀጡ ሰዎች አሃዝን ማወቅ ባይቻልም ቤይጂንግ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በሞት እንደምትቀጣ ይገመታል።

አምነስቲ ከቻይና በተጨማሪ በሰሜን ኮሪያ እና ቬትናም በተመሳሳይ የሞት ፍርድ ምስጢራዊ ስለምታደረግ በቀጠናው በሞት የተቀጡ ሰዎችን ዝርዝር ማወቅ አዳጋች ነው ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ እንደ ኢራን ባሉ አገራት በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር ጭማሪ ያሳየው ከአደኛ እጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ ጥፋተኛ የሚባሉ ሰዎች ቁጥር ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ መሆኑን ገልጿል።

እአአ 2017 ላይ ኢራን 23 ሰዎችን በሞት የቀጣች ሲሆን እአአ 2020 ላይ ቁጥሩ በአምስት እጥፍ አድረጎ 132 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል።

በሳዑዲ አረቢያ ደግሞ በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በ140 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን አምነስቲ ገልጿል። በሳዑዲ በዚህ ዓመት መጋቢት ወር በአንድ ቀን ብቻ 81 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን ገልጿል።

ከእነዚህ ሁለት አገራት በተጨማሪ የኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት በሆኑት በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በየመን በሞት የሚቀጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ገልጸዋል።

ዘገባው የቢቢሲ ነው

Exit mobile version